የትምህርት ሚኒስቴር ውግንና ለጥቂት ባለሀብቶች ወይንስ ለሕዝብ?
(ጫሊ በላይነህ )
የፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር በተዋረድ የአዲስአበባ ትምህርት ቢሮ የ2013 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከዛሬ ነሐሴ 19 እና ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጀመር አውጀዋል። የሚገርመው የ2013 ዓ.ም ትምህርት መቼ እንደሚጀመር ግን ገና በመንግስት አልተወሰነም።
ይህ ምን ማለት ነው?
ትምህርት ሚኒስቴር እና የአዲስአበባ ትምህርት ቢሮ ያወጡት መግለጫ ገና የቀጣዩ ዓመት ትምህርት ትክክለኛ መጀመሪያ ጊዜ ባልታወቀበት ሁኔታ ወላጆች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ቤት ለተቀመጡ ልጆቻቸው ወርሀዊ ወይንም የተርም ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ነው።
ከወራት በፊት ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ በተለይ የግል የትምህርት ተቋማት ለቀጣይ ዓመት ምዝገባ የሚጀምሩት በያዝነው ነሐሴ ወር የመጨረሻ ሳምንት መሆኑና እና ከዚያ በፊት ምዝገባ ማካሄድ እንደማይቻል ክልከላ አስቀምጦ ነበር። በተጨማሪም ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል በተባለው ምዝገባ ት/ቤቶች የክፍያ ጭማሪ እንዳያደርጉም አሳስቧል። ግን ለቀጣይ ዓመት የት/ቤት ክፍያ መጠኑ ምን ያህል መቶኛ ነው የሚለውን በዝምታ አልፎታል። ይህ ማለት ወላጆች ትምህርት ባልተጀመረበት ሁኔታም የልጆቻቸውን መደበኛ ክፍያ መቶ በመቶ የመክፈል ግዴታ ተጥሎባቸዋል ማለት ነው።
ሚኒስቴሩ በያዝነው 2012 ዓ.ም ትምህርት ተቋርጦ በነበረበት ወቅት ወላጆች ከወርሀዊ የትምህርት ክፍያቸው 50 እስከ 75 በመቶ እንዲከፍሉ መመሪያ አውጥቶ ነበር። የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ባለው መረጃ አብዛኛዎቹ ት/ቤቶች ከፍተኛውን 75 በመቶ የክፍያ ጣሪያ በመምረጥ ወላጆችን አፍንጫቸውን ይዘው አስከፍለዋል። ይህ መመሪያ በት/ቤቶች እና በወላጆች መካከል ከፍተኛ ያለመግባባት መነሻ ሆኖም ቆይቷል። እኔ የማውቀው አንድ ወላጅ ለልጁ ከ50 በመቶ በላይ የት/ቤት ክፍያ ልጠየቅ አይገባም በማለቱ ይኸው እስካሁን የልጁ ት/ቤት ጉዳይ መቋጫ አላገኘም። የዚህ መነሻው ሚኒስቴሩ ሆን ብሎ ከ50 እስከ 75 የሚል አሻሚ መመሪያ በማስቀመጡ ነው። እንግዲህ 50 በመቶ ነው ልከፍል የሚገባው ያለው ወላጅም፣ የለም 75 በመቶ ነው የምትከፍለኝ ያለውም የት/ቤት አስተዳደርም አልተሳሳቱም። ዕድሜ ለትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ተቋማቱን ኪሳራ እንዲሸከም የተገደደው ምስኪኑ ወላጅ ነበር።
እናም አሁንም የቀጣዩ ዓመት ትምህርት በመስከረም ወር 2013 ይጀምር፣ አይጀምር ባልታወቀበት ሁኔታ የትምህርት ሚኒስቴር ለወላጆች ቅንጣት ርህራሄ ለሌላቸው የግል የትምህርት ተቋማት ብቻ የሚጠቅም መመሪያ ይዞ መምጣቱ አሳዛኝ ነው። ይህ ወላጅ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ልጆቹ ቤት በተቀመጡበት ሁኔታ ለትምህርት ቤት (መቶ በመቶ) እንዲከፍል የተፈረደበት መነሻ ምክንያቱ ምንድነው? የትምህርት ሚኒስቴርስ ውግንና ለህዝብ ነው ወይንስ ለጥቂት ባለሀብቶች ጥቅም?
የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ወደባለሀብቶች ያደሉ የሚኒስቴሩ መመሪያዎችን በማጤን ብቻ በሚኒስቴሩ በተዋረድ ባሉ የትምህርት ቢሮዎች የጥቅም ግጭት ያለባቸው አመራሮች አሉ የሚለውን የብዙዎች ግምት ለመጋራት ተገዷል። አዎ እሳት በሌለበት ጢስ የለም እንዲሉ በትምህርት ሚኒስቴር የስራ ሀላፊ የሆኑ ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የግል ትምህርት ቤት ባለቤት የሆኑ አመራሮች እንዲሁም ባለቤት ባይሆኑም ከግል የትምህርት ተቋማት ቀለብ የሚሰፈርላቸው አመራሮች አሉ የሚለው ጭምጭምታ የተሳሳተ አለመሆኑን ጠቋሚ ነው። ስለሆነም ሚኒስቴሩ በቅድሚያ ውስጡን ፈትሾ ሊያጠራ ይገባል።
በተጨማሪም የቀጣዩ ዓመት የትምህርት መጀመሪያ ትክክለኛ ጊዜ ባልታወቀበት ሁኔታ የተማሪዎች ምዝገባ በሚል የታወጀው ጊዜ የወላጆችን ጥቅም ግምት ውስጥ ያላስገባ እና የዘርፉን ባለሀብቶች ብቻ የሚጠቅም መሆኑን ተረድቶ ውሳኔውን እንደገና ሊያጤነው ይገባል።
ወላጆችም ይህን ፍርደ ገምድል ውሳኔ እንደወረደ ያለመቀበል መብት አላቸው። ይህን መብታቸውንም በመጠቀም ለጋራ ጥቅማቸውን በጋራ ሊንቀሳቀሱ ይገባል እላለሁ።