ታከለ ኡማ፤ ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያን ይታደጉት ይሆን?
(ጫሊ በላይነህ)
ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ለ10 ከፍተኛ ባለስልጣናት ትላንት ሹመት ሰጥተዋል። በተለይ የአንዳንድ ባለስልጣናት ፕወዛ አሁንም አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።
ከአዲስአበባ ቁልፍ ሀላፊነታቸው ተነስተው ወደ ፌደራል ከተዛወሩት ባለስልጣናት መካከል ኢ/ር ታከለ ኡማ አንዱ ናቸው። ኢ/ር ታከለ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር በመሆን ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ን ተክተዋል።
ባለኝ መረጃ ዶ/ር ሳሙኤል ወደማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ተሹመው ከተመደቡ ሁለት አመት ሊደፍኑ ነው። በዚህ ጊዜ ያለበቂ ማስረጃ ስሙ ጠፍቶ እንዲታገድ የተደረገውን የለገደንቢውን ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ የእገዳ ጉዳይ እልባት መስጠት ሳይችሉ ቆይተዋል።
እነጀዋር መሐመድ ያደራጁዋቸው ጥቂት ወጣቶች የዛሬ ሁለት አመት ገደማ “ፋብሪካው በሰውና በአካባቢ ላይ ብክለት እያስከተለ ነው” በሚል ሁከት አስነሱ። እነሱው ከሳሽ፣ እነሱው ፈራጅ ሆኑናም በዚያው ሰሞን ወደ ፋብሪካው የሚሄድ የኤሌክትሪክ ሀይል መስመር አቋረጡ። መንግስት የእነሱኑ መንገድ በመከተል ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ ወይንም ያለምንም ተጨማሪ ጥናት ፋብሪካው ላልተወሰነ ጊዜ ከስራ አገደ። አገሪቱም በየአመቱ እስከ 400 ሚልየን ዶላር ታገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ቆመ።
በአካባቢው ፋብሪካውን ተገን አድርገው የተቋቋሙ አነስተኛና ጥቃቅን ንግዶች ከሰሙ። የአካባቢው አስተዳደርም ለተለያዩ ችግሮቹ ከፋብሪካው በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚያገኘው ድጋፍ ተስተጓጎለ። የኦሮሞ ልጆች የሆኑ በርካታ የፋብሪካው ሰራተኞች የስራ ዋስትና ስጋት ላይ ወደቀ። እነጀዋር መሐመድ አደናግረውና ግርግር ፈጥረው የለማውን ፋብሪካ ከሼህ አልአሙዲ እጅ ነጥቀው “የእኛ ነው” ለሚሉት ባለሃብት የማስተላለፍ ድብቅ አጀንዳ በቀላሉ የሚሳካ አልሆነም።
በወቅቱ በዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚመራው የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ማኔጅመንት ምንም እንኳን ፋብሪካው የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ (Impact Assessment) አስቀድሞ በማድረግ ደረጃውን በጠበቀ የወቅቱ ቴክኖሎጂ እየሰራ መሆኑን የሚታወቅ ቢሆንም ችግሩ በገለልተኛ ባለሙያዎች እንዲጠና የቀረበውን ሀሳብ በሙሉ ልብ ለመደገፍ አላመነታም። በዚህ መሰረት አንድ የካናዳ ኩባንያ ፋብሪካው በአካባቢ ላይ አደረሰ የተባለውን ተፅእኖ እንዲያጠና ተመርጦ አጠና። ውጤቱንም ለመንግስት አቀረበ።
እነሆ ይህ ከሆነ አንድ አመት ያለፈው ቢሆንም እነዶ/ር ሳሙኤል በጥናቱ መሰረት ሚድሮክ ወርቅ እንዲቀጥል ወይንም እንዲዘጋ ውሳኔ መስጠት ሳይችሉ ቀርተዋል። እነሆ ፋብሪካውን ለወራቶች ውሳኔ ነፍገው ለከባድ ኪሳራ ዳርገውታል። አገርና ወገንም ማግኘት የሚገባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አሳጥተዋል። አሁን ጥያቄው ሚኒስቴሩ በገለልተኛ ወገን ያስጠናውን ጥናት ቢያንስ ይፋ ለማድረግ እንኳን ለምን ፈራ የሚለው ነው። የመንግስት አስፈፃሚ አካል ስራውን በአግባቡ ባለመስራቱ ምክንያት ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ እስከመቼ ኪሳራ ተሸክሞ ይቀጥላል የሚለውም መመለስ ያለበት ጉዳይ ነው።
በዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ግምት የኢንጅነር ታከለ ኡማ ወደማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መምጣት እንዲህ አይነት ውሳኔ ያጡ እና የአገር የውጭ ምንዛሪ ገቢን ጭምር የጎዱ የኢንቨስትመንት ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲያገኙ ይረዳል።
የውሳኔ ሰው እነደሆኑ የሚነገርላቸው ኢንጅነር ታከለ ኡማ ሚኒስቴሩ ከፍሎ ባስጠናው ሳይንሳዊ የጥናት ውጤት መሰረት የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያን ተገዶ ከገባበት ቅርቃር ማውጣት የመጀመሪያ ስራቸው እንደሚያደርጉት አምናለሁ። በዚህ አጋጣሚ ለሚኒስትር ታከለ መልካም የስራ ጊዜ እመኛለሁ።