Connect with us

ስለቀድሞ የኢንሳ ምክትል ሀላፊ ቃለመጠይቅ

ስለቀድሞ የኢንሳ ምክትል ሀላፊ ቃለመጠይቅ
Photo: Social Media

ትንታኔ

ስለቀድሞ የኢንሳ ምክትል ሀላፊ ቃለመጠይቅ

ስለቀድሞ የኢንሳ ምክትል ሀላፊ ቃለመጠይቅ

(ነብዩ ስሁል ሚካኤል)
አጭር አስተያየታዊ ምልከታ በኮሎኔል ቢንያም ተወልደ ቃለ-መጠይቅ ላይ

በቅድምያ ይህ አጭር ፅሁፍ ለመፃፍ የፈለኩበት ምክንያት ግልፅ ላድርግ፤ ስለ ቃለ-መጠይቁ አጭር አስተያየት ለመስጠት የፈለኩት በሁለት ግላዊ ምክንያቶች ነው፤ አንደኛው ምክንያት የመማርና የማስተማር፤ የማንበብና የመፃፍ እንዲሁም የመመራመርና የመፍጠር ዝንባሌ ስላለኝ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪ ጥናቴ Structuralism እና Post-Structuralism ወይም ውቅራዊነት እና ድህረ-ውቅራዊነት የተሰኙ የፍልስፍናና የጥናት ዘዴዎች በመጠቀም ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ አገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ወይም Ethiopian nation building process ስላጠናሁ አካዳሚያዊ ውቃብዬ ስለተቀሰቀሰብኝ ነው። ይህ ጥናትም ለ12 አመት የዘለቀው የዩኒቨርሲቲ የአስተማሪነት ህይወቴና የስነ-ፅሁፍ ስራዎቼ ጨምሮ አብዛኛው የንቃት/የconsciousness ፍለጋየና ምርምሬ ወደ ተሻለ ደረጃ ያሳደገልኝ ወሳኝ ጥናት እንደነበር ለመጥቀስ እወዳለሁ።

ከዚህ በመቀጠል የኮለኔል ቢንያም ተወልደ የሰሞኑ ቃለ-መጠይቅ ወደ መዳሰስ ልግባ፤ ቃለ-መጠይቁ በአጠቃላይ ለመደበኛ አሳቢ (regular thinker) ከበድ ሊል በሚችል ሁኔታ ባነበበው ልክ ማለትም በጥራዝ-ነጠቅነት ደረጃ ልተንትን የሚል፤ ያልተለመዱ ቃላቶችና ሃሳቦች በመደጋጋም አድማጭ-ተመልካቶችን ለማወናበድ የሚሞክር እንዲሁም በስዉር አምባጓሮ የሰው ክቡር ስብእና ለመነካካት ያለመ የልክፍት ፕሮፖጋንዳ ከንቱ ጥረት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ቃለ-መጠይቁ በይዘት ደረጃ ንቃት ወይም consciousness በተባለ የፍልስፍናና የስነ-ልቦና የጥናት ዘርፍ ላይ በማተኮር በዋነኝነት የኮለኔል ቢንያም የራሱ ንቃት (self-consciousness) እንዲሁም የጠ/ሚንስትሩ የንቃትና የስነ-ልቦና ውቅር/physcho-structure ለመተንተን ሞኩሯል። በዚህ ሙከራ ኮለኔል ቢንያም እራሱን ያወቀው (self-conscious የሆነው) እስር ቤት ውስጥ ከገባና የተወሰኑ መፅሃፎች ካነበበ ቧሃላ መሆኑ፤ መታሰሩም እራሱን እንዲያውቅና ተግባሩ ዞር ብሎ እንዲመረምር እጅግ እንደጠቀመው በተደጋጋሚና እውነተኛ በሚመስል የአመስጋኝነት ስሜት ሲገልፅ ይታያል።

ለኛ ይህ ምስክርነት ባለፉት ሁለት አመታት አገራዊና የዴሞክራሲያ ተቋማት ለመገንባት የተደረገው ጥረት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መጀመሩ የሚያሳይ ትልቅ ምስክርነት ነው። ይህ ምስክርነት ኮለኔል ቢንያም ስለራሱና ስለአገሩ በቂ እውቀት ሳይኖሮው እንዲሁም በአጉል ድፍረትና በከፋ ድንቁርና አገራዊ ተቋም ለመምራት የሞከረበትና ለውድቀት የተዳረገበት ታሪክ ውጤት ሲሆን ሻገር ብሎም በብቃትና በፍትሃዊነት ሳይሆን በቤተ-ዘመድና በወንዜ-ልጅነት እንዲሁም በዘረኛ ፖለቲካና በሃላቀር ልግመኝነት የተገነባው ጠቅላላ የህወሓት ስርአት ታሪክና የማይቀር የውድቀት እጣ ፈንታ ምስክርነት አካል መሆኑ ግልፅ ነው።

ኮለኔል ቢንያም ‘በተሳሳተ የራስና የአገር ምልከታ ውስጥ ተዘፍቄ ነበርኩ፤ አሁን ግን አስራቹና የተወሰኑ መፅሃፎች እንዳነብ አድርጋቹ አነቃቹሁኝ’ ብሎ በራሱ በመሰከረበትና አሳሪዎቹና አሳሳሪዎቹ ባመሰገነበት የተሻለ የጤንነትና የስብእና ስርጓጉጥ ቀጥሎ ለመዳሰስ የሞከረው የዶ/ር አብይ አህመድ ባህሪ ወይም ስነ-ልቦናዊ ውቅር ነው። ሆኖም ግን ኮለኔል ቢንያም መንቃት ከጀመርኩ ገና ሁለት አመቴ ነው ባለበት አንደበቱ ጠቅላይ ሚንስትሩን ለመመዘንና ለመተንተን የሞከረበት ሂደት አሁንም ገና የመንቃትና የመተንተን ጨለማ ውስጥ እንዳለ ከማመላከቱ በዘለለ መፍጠር የተፈለገ የከንቱ ልክፍትና የቀቢፀ-ተስፋ ፕሮፖጋንዳ መኖሩ ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ቢሆንም በጀመርነው ቀጥለን ኮለኔል ቢንያም ንቃቴና ትንተናዬ እንካቹ ያለዉን ነገር እንዲያቀርብ እንፍቀድለት (ማን ያውቃል፤ እኛንም የስነ-ልቦና ውቅሬ እንዲስተካከል አገዛቹሁኝ ብሎ ባለውለታዎቹ እንደማያደርገን!)

ኮለኔል ቢንያም የጠ/ሚኒስትሩ ባህሪ ወይም ስነ-ልቦናዊ ውቅር ልተንትን ባለበት የቃለ-መጠይቁ ክፍል የታላቁ የስነ-ልቦና ጥናት አባት የሆነው የሲግመንድ ፍሮይድ የልጅነት ዘመን እድገት ፅንሰ-ሃሳብ/child development theory እንዲሁም የኢንያግራም የስነ-ልቦና መመዘኛ ስልት መጠቀሙ በመጠቆም ሃሳቡ ሳይንሳዊ ለማድረግ ይጥራል።

በመቀጠልም የዶ/ር አብይ ስነ-ልቦና በልጅነት ግዜ በተፈጠረ ትልቅ መሪ የመሆን ትንቢታዊ ፍላጎት፣ በዝናና ትኩረት መሻትና በደፋርነት ባህሪ የተዋቀረ መሆኑ ከገለፀ በሃላ እነዚህ ነገሮች የማንነት ቀውስ/personality disorder ማሳያዎች በሆነ ደረጃ ይገለፃሉ በማለት ያርፈዋል፤ አሁንም በመቀጠል እነዚህ ነገሮች ላለማጣት በሚደረግ የአእምሮ ውስጥ ግብግብ የከፍተኛ ፍርሃትና ጭንቀት/neurosis ችግር ተፈጥሯል በማለት ይደመድማል።

ኮለኔል ቢንያም የዶ/ር አብይ የአእምሮ ውቅር/psycho-structure መሰረቶች ናቸው የከፋ መገለጫም አላቸው ያሏቸው ነገሮች በጤናማ አይን ሲታዩ የፍፁም ጤናማነት አልፎም ተርፎም የልዩ ጀግንነት ምልክቶች መሆናቸው የሲግመንድ ፍሮይድ እሳቤዎች እስከመጥቀስና እስከመተንተን መሄድ ሳያስፈልገን በተገኘው ታላቅና ታሪካዊ ውጤት ለክተን መገንዘብ እንችላለን፤ በተለይ ደፋርነት/ቆራጥነት ትልቁ የንቃት/consciousness ምልክት መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው። አብዛኛው ግዜ የምንፈራውም ስለአንድ ጉዳይ ንቁ ስላልሆንን (ማለትም ስለጉዳዩ በቂ እውቀት ወይም በቂ እድል እንደሌለን ስናስብና ስናምን) ነው። በተለይ ማሰብ፣ መመራመርና መወሰን በሚጠይቁ ውስብስብ ጉዳዮች ላይ የሚተገበር ደፋርነት የከፍ ያለ ንቃትና የታላቅ ህይወት ግብ ምልክት ነው።

ከደፋርነት በተጨማሪ ትኩረትና ዝና መሻት መሪ ለመሆን የሚያስችል ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ነው፤ ምክንያቱም የህዝብ ትኩረት ካላገኘህና ዝና ከሌለህ መሪ ለመሆን ቁልፍ ሚስጢር አጥታሃል ማለት ነው። የልጅነት-ዘመን መልካም ትርክት፣ ተስፋ ወይም ትንቢትም ቢሆን የሰው ልጅ አእምሮ የሚነቃበትና የሚታነፅበት ወሳኝና ሁሉም ሰው በልጅነቱ ከቤተሰቡ ሊቀዳጀው የሚችለው የአእምሮና የስብእና ግንባታ እድሎች አንዱና ዋነኛው መሆኑ ግልፅ ነው፤ በዚህ ረገድም የዶ/ር አብይ ወላጅ እናት እናታዊ ብልሃት ከኮለኔል ቢንያም ጥራዝ-ነጠቅ እወቀትና በራስ የመሸነፍ ቀውስ (self-defeating disorder) የወለደው የፕሮፓጋንዳ ከንቱ ጥረት በላይ ታሪካዊ ውጤት ያመጣ አኩሪ ድል መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው።

የኮለኔል ቢንያም የሁለት አመት ቁንፅል ንቃትና ለካፊ ትንተናም በመውደቅና ለእስር በመዳረግ ብስጭት የተንገበገበ፤ የተሸናፊ ማንነት ቀውስ የወለደው እና የቁጭት ሲቃ ለመወጣት ያለመ የህወሓት የቀቢፀ-ተስፋ ፕሮፖጋንዳ አካል መሆኑ ያው ይሄም የአደባባይ ሚስጢር ነው።

ሲጀምርም ኮለኔል ቢንያም በዚህ ደረጃ የነ ሲግመንድ ፍሮይድ ፅንሰ-ሃሳቦች ላይ አትኩሮ የቆየው INSA ውስጥ የስለላና የደህንነት ስራ ሳይሆን እስረኞችን የመመርመርና ምናልባትም መረጃ ለማግኘትና የአገር ደህንነት ለመጠበቅ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ሳይሆን ሰዎችን በቀጥታ ይሁን አጠቃላይ ስምሪቱ በመምራት የማሰቃየትና አእምሯቸው የማኮላሸት ተግባር ውስጥ ተዘፍቆ የቆየ ወንጀለኛ ስለመሆኑ እራሱ እየጠቀሰው ባለው የምርምር ዘርፍ ብቻ መረዳት ይቻላል። ምክንያቱም የሲግመንድ ፍሮይድ ፅንሰ-ሃሳቦች የግለሰቦች የአእምሮ ጤንነትና ቀውስ ሁኔታ ላይ ያተኮሩ የምርምርና የህክምና ፅንሰ-ሃሳቦች እንጂ አገር ከቡዱኖችና ሃይሎች ጥቃት ለማዳን የሚጠቅም የደህንነትና የመከላከያ ዘርፍ አይደለም።

በመሆኑም የኮለኔል ቢንያም የእውቀትና የምርምር ትኩረት ከነበረበት ሃላፊነትና የግፈኛ ቡዱን አባልነት አንፃር ሲመረመር ጤናማ አይመስልም። ለዚህም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ተብለው እንኳን ቀን-ቀን ለይስሙላ ህገ-መንግስት እያጣቀሱ ሲፈርዱ ሌሊት-ሌሊት ደግሞ የሚስኪን እስረኞች ጥፍር ሲነቅሉ የሚያድሩ ወንጀለኞች በነበሩበት በዛ ግፈኛ ስርዓት ውስጥ፤ ትውልድ እንደ ትውልድ ተኮላሽቶ እንዲመክን በተደረገበት በዛ ግፈኛ ስርዓት ውስጥ፤ ህዝብ ደህይቶና ፈርቶ እንዲገዛ በተደረገበት በዛ ግፈኛ ስርዓት ውስጥ እነ ኮለኔል ቢንያም ለብቻቸው ትኩረት ያደረጉበት የሰው ልጅ ጭንቅላት ለክፋትና ለግፍ አልነበረም ብሎ ማሰብ ፍፁም የዋህነት ነው፤ ለዚህ ማረጋገጫም ብዙ ተጨባጭ ማስረጃዎች እንዳሉም ይታወቃል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የራስን አስከፊ ውድቀት የሚያስከትለው የስነ-ልቦና ቀውስ ለማከም ሲባል በአልባንያ ኮምኒዝም ልክፍት ተረሰቶና ተንቆ ወደቆየው የቀድሞ የአክሱም ገናናነት ትርክት ለመመለስ የቀረበ ሃሳብ ይገኛል። ሃሳቡ በመርህ ደረጃ የሚደገፍ ቢሆንም ጉዳዩ የሚታይበት የስሜት መሻገትና የመንደሬና የዘር ፖለቲካ መነፅር ግን ጉዳዩ በመጣበት ቅፅበት ተመልሶ አስቂኝ ያደርገዋል። በተለይ ትግራይ/አክሱም ሲባል በታሪክ የአንድ ዉሱን ቦታ መጠርያ ሆኖ ከመቆየቱ አንፃር በቁንፅል የመንደሬነት ስሜት ከሌላው ትግራዋይ ቀድሞ እንደ ጅብ-ብራ ከፊት ለመገተር የሚደረገው ሩጫ ሲታይ የቁንፅልነቱ ጥግ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

በመጨረሻ በቃለ-መጠይቁም ሳይቀር በተደጋጋሚ ተገልፆ ግርምት የፈጠረልኝ አንድ ነገር ላንሳና አስተያቴን ላገባድድ፤ ይህም ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚንስትር እንደሚሆኑ ለብዙ ሰዎች እየተናገሩ መቆየታቸው የሚገልፅ ነው፤ ይህ የልዩ ንቃት፣ የልዩ በራስ-መተማመንና የልዩ ድፋርነት ከፍታ የሆነ ተግባር እውነት ከሆነ (ማለትም የህወሓት መሪዎች ይህንን በተደጋጋሚ የሚመሰክሩት ሰውየው ከመጀመርያውም ስልጣን ፈላጊ ነበሩ በማለት ለመጫወት ያሰቡት አሮጌ ቁማር ከሌለ ማለቴ ነው) እና ይህ ተግባር እውነት ከሆነ የዶ/ር አብይ ስብእና በብዙ እጥፍ አስደናቂና አብረቅራቂ ያደርገዋል።

ይህ ለማለት የቻልኩት አይደለም ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን መፈለግ ይቅርና ሰው ለመሆን በማሰብህ እንኳን እንደ ወንጀለኛ በምትቆጠርበት የአገራችን ሃላቀር ፖለቲካ ውስጥ ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን እንደሚፈልጉና እንደሚችሉ ለብዙ ሰዎች እየተናገሩ (ማን ያውቃል፤ አንዳንዴም መናገር ሰልችቷቸው ዘና ብለው በፉጨት እየዘፈኑት!) ወደ አለሙት ከፍተኛ ሃላፊነት መገስገሳቸው፤ ያለሙትም ያሉትም ማሳካት መቻላቸው፤ አሳክተውም በመላ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘታቸው፤ ቀጥሎም ለማመን የሚከብዱ ፈጣን ለውጦች በአጭር ግዜ ማሳካታቸው ሲታይ ሰውየው ነብይ ወይም አንዳች መለኮታዊ ሃይል ያላቸው ልዩ ፍጥረት እንዳይሆኑ በእጅጉ ያስጠረጥራቸዋል እንጂ ማንም ተጠያቂነቱ ገና ያልጨረሰ መንደሬ፣ ዘግየቶ ነቂና ተንታኝ ነኝ ባይ ባንሸዋረረው ሸውራራ ትንተና ፍፁም አይሰፈሩም።

Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top