አሁን ባለችዋ ኢትዮጵያ ይኼን ማሰብና ማቀድ ብቻ ይደክማል፡፡ እርስዎ ግን አደረጉት፡፡
መልካም ልደት ብያለሁ፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ
ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሩትን ስራ ቤቴ ቁጭ ብዬ ጎበኘሁ፡፡ አጠገባቸው ያሉ ሰዎች ሊጥሏቸው የሚታገሉት መሪ አጠገባቸው ያለው ሰው ያልሰራውን ሰርተዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ መልካም ናቸው፡፡ የምጣኔ ሀብት ሊቅ ስላልሆንኩ “የቱ መቅደም ነበረበት?” በሚል ከዚህ የሚብስ ነበር ለማለት እቸገራለሁ፤ በዚያ ላይ የተፈጥሮ ሀብትና የቅርስ ተቆርቋሪ ስለሆንኩ የላቀ ስራ አድርጌ ብቆጥረው አያስፈርድብኝም፡፡
ብዙ ነገሮቹ ይገርማሉ፡፡ ምናልባት አስጎብኚው ጠቅላዩ ራሳቸው ባይሆኑ ደስ ይለኝ ነበር፤ ምክንያቱም እሳቸው እየተዟዟሩ ሲገልጹ ልቤ ቅጥ ወደ አጣው የፖለቲካችን ዓለም እየገባ ይረብሸኝ ስለነበር ነው፡፡
የእንጦጦ ፕሮጀክትን ጅማሬ መልካም ወዳጆቼ ወስደው አሳይተውኝ እጅግ ተደንቄያለሁ፤ እንጦጦ ለአዲስ አበባ ህዝብ የተፈጥሮ ሆስፒታል ነው፡፡ በዚህች ያለ ሳይንስ መስታወት የመለጠፍ ፉክክር ውስጥ በገባች ከተማ የነገው አየር ሁኔታ አሳሳቢ ነውና እንዲህ የዙሪያዋን ተራሮች ጠብቆ፣ አልምቶና ዳቦ አድርጎ ማኖር ዋስትናው ለመዲናዋ ነው፡፡
ቀድሞ በነበሩት አሮጌ መንደሮች መቃብር ላይ የተሰራው አዲሱ ፕሮጀክት መዲናዋን ምን ያህል እንዳሳመራት ከማታው ፕሮግራም አይቻለሁ፡፡ የሙዚየሙ ይዘትና የቅርስ ጥበቃው አዲስ መንፈስም ስፍራው መዳረሻ ብቻ ሳይሆን የሀገር ክብር ማኖሪያ ሆኖ መልማቱን አሳይቶኛል፡፡
እኔና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍልስፍና ደረጃ የማንግባባው በመካነ እንስሳቱ ጉዳይ ነው፡፡
የአሁኗ ኢትዮጵያ ሰው በብሔር ጠብ ሲያነሳ ዱር እንስሳ የሚጨርስባት፣ ነጻ አውጪ የዕለት ጉርሱን አድኖ የሚበላባት፣ ያኮረፈ መጥረቢያ ይዞ ደን አመድ የሚያደርግባት ሀገር ናት፡፡ ይሄ መጠበቁ ይልቃል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰው ሰራሽ መካነ እንስሳት የዱር እንስሳቱን ከማሰቃየት ያለፈ ትርጉም የለውም ባይ ነኝ፡፡ ያም ሆኖ ለዘመናት ከኖረው የአንበሳ ግቢ አይነት ጭካኔ የላቀ አያያዝ የታየበት መካነ እንስሳት መገንባታቸው አንድ እርምጃ ከፍታ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ጠቅላዮ የነገዋ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት ስማቸውን በክብር የሚያነሳቸው እንደሚሆኑ ግን አልጠራጠርም፤ ቅርስ አፍራሹ መዋቅራቸው አደብ ከገዛ ደግሞ የተመኟትን ኢትዮጵያ ለልጅ ልጆቻቸው ማውረስ ይችላሉ፡፡
ዛሬ ልደታቸው ነው፡፡ በዚሁ ደስ የተሰኘ ስሜት ውስጥ ሆኜ፤ እንኳን አደረስዎት፤ መልካም ልደት ስል ተመኝቻለሁ፡፡