የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስራ ሃላፊዎች ሹም ሽር እና የመዋቅር ለውጥ አደረገ
-ባሳለፍነው በጀት አመት ደካማ አፈፃፀም ማስመዝገቡም ታውቋል፡፡
ግዙፉ የፋይናንስ ተቋም መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (ኢንባ) ደካማ አፈፃፀም ማስመዝገቡን ተከትሎ የመዋቅር እና ሃላፊዎች ለውጥ አድርጓል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገው የምደባ መዋቅር ማሻሻያ 9 የቺፍ ኦፊሰርነት ቦታዎች በሙሉ እንዳይኖሩ ተደርጓል፡፡ በምትኩ በምክትል ፕሬዝደንትነት ደረጃ ብቻ የመዋቅር ለውጥ የተደረገ ሲሆን፡፡ የምክትል ፕሬዝደንቶች ብዛትም ከቀድሞው 24 ወደ 18 እንዲወርድ ተደርጓል፡፡
ባንኩ የሚጠበቀውን ውጤት ባለማስመዝገቡ መንግስት የቀድሞው ፕሬዝደንት አቶ ባጫ ጊናን በመጋቢት ወር በማሰናበተ የቀድሞውን መሪ አቶ አቤ ሳኖን መመለሱ ይታወሳል፡፡
በአቶ ባጫ አስተዳደር የአመራር መዋቅር መብዛት እና ወደ ጎን ያለቅጥ መለጠጥ ለአስተዳደር አመቺ ያልነበረ ነው የሚሉት የካፒታል ምንጮች የአሁኑ ለውጥ ተቋሙን በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚረዳ ነው በማለት ደግፈውታል፡፡
በመዋቅር ለውጡም አንዳንድ ሃላፊዎች መነሳታቸው ታውቋል፡፡ በቀድሞው መዋቅር መሰረት ምክትል ፕሬዝደንቶች ለቺፍ ኦፊሰሮች ተጠሪ የነበሩ ሲሆን ቺፍ ኦፊሰሮች ለፕሬዝደንቱ ተጠሪ ነበሩ፡፡
በአዲሱ ለውጥ ምክትል ፕሬዝደንቶቹን በቀጥታ ፕሬዝደንቱ ይከታተላቸዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በውስጥ ኢሜል አቶ አቤ ‘ምን ይሆን ምክንያቱ? መድኃኒቱስ?’ በሚል ርእስ በ2012 የፋይናንስ አመት ስለነበረው ደካማ አፈፃፀም ለሰራተኞች በደብዳቤ ሁኔታውን አሳይተዋል፡፡
የስራ አፈፃፀሙን ካወቅን ቆይተናል ያሉት አቶ አቤ ውጤቱን የምገልፅበት ቃላት ፈልጌ በማጣቴ ውጤቱን ከመግለፅ ስለዘገየሁ ይቅርታ ይደረግልኝ ብለዋል ለሰራተኞቻቸው በፃፉት የውስጥ ደብዳቤ፡፡
ይህን አይነት ሪፖርት አድርጌ ስለማላውቅ ቢተናነቀኝም ምክንያቱን እንደምትረዱኝ ተስፋ አደርጋለው ይላል ካፒታል ያገኘችው የደብባቤው ቅጅ፡፡
ውጤቱ በምንም መስፈርት ተቀባይነት እንደሌለው ያስረዱት አቶ አቤ ሁላችንም እንደ እየድርሻችን ሃለፉነት መውሰድ አለብን ብለው፤ ሰራተኛው ለተሻለ ውጤት ተግቶ ለመስራት እንዲዘጋጅ አሳስበዋል፡፡
በበጀት አመቱ ባንኩ ከፍተኛ ወጪ በማስተናገዱ የትርፍ መጠኑ ከእቅዱም ሆነ ከቀዳሚው አመት ጭምር ያነሰ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ለወጪ መናር ባለፈው አመት የተደረገው ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ መሆኑን ምንጮች ጠቅሰው ጭማሪውም እስከ እጥፍ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አቶ አቤም በደብዳቤያቸው እንዳሉት ሠራተኛው በደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጭማሪ ብቻ ውጤታማ ይሆናል ተብሎ ባያታመንም ባንኩ ባለፈው ዓመት ለተወሰኑ አመታት የሠራተኛው ጥያቄ ለነበረው የደሞዝ ማሻሻያ ትርጉም ያለው ምላሽ የሰጠበትና በምትኩ የተሸለ ውጤት የሚጠበቅበት ዓመት ነበር ሲሉ ፅፈዋል፡፡
ላለፈው ውጤት ያሳፈሩንን ተጠያቂ ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ወደፊት ግን ለስንፍናና ውድቀት ቦታ የሌለን መሆኑን መላው የባንካችን ሰራተኛ በጥሞና በመገንዘብ በሁሉም መስክ ጠንክሮ እንዲሰራ አሳስባለው ብለዋል፡፡
ኢንባ በ2012 ፋይናንስ ዓመት 64.3 ቢሊየን ገቢ ለማግኘት አቅዶ ወደ 69 ቢሊየን ብር ወይም ተጨማሪ 4.4 ቢሊየን ገቢ ማስገባቱ ብቻ መልካም ውጤት ይመስላል፡፡
ሆኖም ስለዚሁ ውጤት አቶ አቤ ሲገልፁ የተሻለ ውጤት የሚመስለው የገቢ እድገትና ከእቅድም በ 4.4 ቢሊየን መብለጥ ብቻ ሲሆን እሱም ቢሆን ባልተመጣጠነ የ3 እጥፍ ወጪ ንረት ዋጋ ያጣ ከመሆኑም በላይ የገቢ ዕድገቱም የተገኘው በወጪ ባንክ አገልግሎት ላይ በተደረገ የዋጋ ጭማሪ መሆኑ ደግሞ አንድም የመጽናኛ ስኬት እንዳናወሳ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በ2012 የፋይናንስ አመት ባንኩ 14 ቢሊየን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን ከእቅዱ የ36 በመቶ ቅናሽ የታየበት ነው፡፡ ይህ ትርፍ ከቀዳሚው አመት ትርፍም ከ10.3 በመቶ ያንሳል፡፡
የተቀማጭ ጭማሪም 100 ቢሊየን እንዲሆን የታቀደ ቢሆንም ማሳካት የተቻለው 54 ቢሊየን ብቻ ነው፡፡ የ2011 እና 2010 የተቀማጭ ጭማሪ እንደ ቅደም ተከተላቸው 89 ቢሊየን እ 87 ቢሊየን የነበረ ሲሆን የ2012 አፈፃፀም ከሁለቱም ያነሰ መሆኑ ይታያል፡፡
በወጪ ረገድ በአመቱ 42.5 ቢሊየን ብር ይወጣል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም የወጣው ግን ከእቅዱ በ29 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ 55 ቢሊየን ብር ግድም ሆኖ አመቱ ተጠናቋል፡፡
ይህም የባንኩን የትርፍ መጠን ክፉኛ እንደጎዳው ነው የምንጮቻችን ገለፃ የሚያሣየው፡፡
ባንኩ ላለፉት አስር አመታት ግድም ፈጣን እድገት ያስመዘገበ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ ለዚህ ውጤቱ መሰረት በመጣል አቶ አቤ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ይጠቀሳል፡፡ ሆኖም በወቅቱ በአቶ አባይ ፀሃዬ ከሚመራው ቦርድ ጋር ስምምነት ባለመኖሩ አቶ አቤ እንዲነሱ መደረጉን ምንጮች ያስታውሳሉ፡፡
በፋይናንስ ዘርፍ ውጤታማ እና ለውጥን በተግባር በማሳየት የሚሞገሱት አቶ አቤ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክን ከምስረታው አንስቶ በመምራት በአጭር አመታት ውስጥ ባንኩን በአገሪቱ ግንባር ቀደም ከሆኑት የግል ባንኮች እኩል ማድረሳቸው ይታወሳል፡፡
ወደ ንግድ ባንክም ተመልሰው ሲመጡ ከወጣትነት ግዜያቸው አንስቶ እስከ መሪነት ያገለገሉትን ባንክ እንዲታደጉ ተስፋ ተጥሎባቸው ነው፡፡ በተሾሙበት ወቅት በ30ዎች የመጀሪያ እድሜ ውስጥ ሆነው ግዙፉን ባንክ በመምራትም በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ቀዳሚው ወጣት መሪ እነደነበሩ ይታወሳል፡፡(ካፒታል)