Connect with us

መንግሥት የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ ወሰነ

መንግሥት የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ ወሰነ
Photo: Ethiopian Reporter

ኢኮኖሚ

መንግሥት የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ ወሰነ

በመካሄድ ላይ ባለው የቴሌኮም ዘርፍ የለውጥ ትግበራ፣ የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ መንግሥት እንደወሰነ ታወቀ፡፡

የቴሌኮም ዘርፍን ገበያ በመክፈት የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ ለመፍቀድ መንግሥት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የቴሌኮም ዘርፍ የለውጥ ትግበራ ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመርያው በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራው ለ126 ዓመታት በብቸኝነት የቴሌኮም አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው በአፍሪካ አንጋፋው ኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ፣ 40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ለውጭ ኩባንያ ለመሸጥ የሚደረገው ጥረት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ሁለት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው፣ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

የለውጥ ትግበራው ቀልባቸውን ከሳበው የውጭ ኩባንያዎች መካከል፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ገንብተው የሚያከራዩ ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡ እንደ ሞባይል ምሰሶዎች ያሉ መሠረት ልማቶች የሚያከራዩ ኩባንያዎች ኃላፊዎች ወደ አዲስ አበባ ሲመላለሱ ከርመዋል፡፡

ጉዳዩ ባለፉት ዓመታት በቢሊዮን ዶላሮች ወጪ በማውጣት የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች በመላ አገሪቱ ሲዘረጋ የቆየውን ኢትዮ ቴሌኮምን አስቆጥቷል፡፡ ‹በቂ መሠረተ ልማት ገንብተናል፣ ለሚገቡት ኩባንያዎች አከራይተን ከፍተኛ ገቢ ማስገባት እንችላለን› ያሉት የኢትዮ ቴሌኮም ማኔጅመንት አባላት ያቀረቡትን አቤቱታ መንግሥት ተቀብሎ፣ የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች ላለማስገባት እንደወሰነ ታውቋል፡፡

የ2012 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ እንደተወሰነ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የውጭ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኩባንያዎች እንዳይገቡ መንግሥት ወስኗል፣ አይገቡም፡፡ የሚገቡት ኦፕሬተሮች ወይ ከእኛ ይከራያሉ ወይም የራሳቸውን ይገነባሉ፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ኩባንያዎቹ የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ምሰሶዎችንና የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮችን መከራየት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በሊበራላይዜሽን ሒደቱ ላይ ያሉትን ሥጋቶችና ቅሬታዎች በጽሑፍ ለኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን አስገብቶ፣ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ባለሥልጣኑ የኢትዮ ቴሌኮምን ህልውና የሚጎዳ አካሄድ ይከተላል ብለን አናምንም፡፡ ነገር ግን ከስምምነት ላይ ያልደረስንባቸው ቀሪ ጉዳዮች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

ለውድድር እየተዘጋጀ ያለው ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 47.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ገቢው በታሪኩ ከፍተኛው እንደሆነና ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ31.4 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ኩባንያው አስታውቋል፡፡ አርባ አምስት ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ያቀደው ኢትዮ ቴሌኮም ከዕቅዱ በላይ 105.1 በመቶ ገቢ እንዳገኘ አስታውቋል፡፡

ከዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎቶች 147.7 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማስገባቱን፣ ይህም የ50 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በሁለተኛው ግማሽ ዓመት እንደ ሮሚንግ ያሉ አገልግሎቶችን መስጠት እንዳልቻለ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ጠቁመዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ የሆነ የዳታና የኢንተርኔት አገልግሎት ፍላጎት እንደፈጠረ፣ በሌላ በኩል እንደ ሮሚንግ ያሉ ገበያዎችን በከፍተኛ መጠን እንደቀነሰ ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ኢትዮ ቴሌኮም 11.3 ቢሊዮን ብር ለታክስ፣ ለመንግሥት ደግሞ አራት ቢሊዮን ብር ፈሰስ እንዳደረገ ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም 10.2 ቢሊዮን ብር (318 ሚሊዮን ዶላር) ለማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የተወሰደ ብድር ክፍያ እንደፈጸመ ተገልጿል፡፡ ይህም ከልማት አጋሮች ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት ለማሻሻል እንደረዳውና ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት በአገልግሎትና በገንዘብ 1.15 ቢሊዮን ብር ለተለያዩ አገራዊ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንደተደረገ ተገልጿል፡፡

‹‹ይህ አስገራሚና የሚያኮራ አፈጻጸም ሊመዘገብ የቻለው ማኔጅመንቱና ሠራተኞች ተናበው በቁርጠኝነት በመሥራታቸው ነው፤›› ብለዋል ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡፡ ነባር አገልግሎቶችን በማሻሻል፣ በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶችን በመጀመር፣ ከፍተኛ የታሪፍ ማሻሻያ በማድረግ የኩባንያውን ገቢ ማሳደግ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የተመዘገበው አስገራሚ ውጤት የቀረፅነው የቢዝነስ ስትራቴጂ ትክክለኛ እንደሆነ አመላካች ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ይህን ስኬት ያስመዘገበው በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡ ‹‹መንገዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም፣ የሚያንገዳግዱ ችግሮች ገጥመውናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የፀጥታ ችግር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የኮሮና ወረርሽኝና የቴሌኮም ማጭበርበር ዋና ዋና ችግሮች እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ በበጀት ዓመቱ በመሠረተ ልማት ላይ 1,161 ጉዳቶች መድረሳቸውን፣ ይህም የ33 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ አራት የድርጅቱ ተሽከርካሪዎች እንደ ወደሙ፣ ኩባንያው ያሰማራቸው አሥር የጥበቃ ሠራተኞች እንደተገደሉ፣ በአራቱ ላይ የአካል ጉዳት እንደ ደረሰ ጭምር ተገልጿል፡፡ አሥራ ሁለት ሠራተኞች መታገታቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም 36,000 ሠራተኞች እንዳሉት፣ ከ249,000 አከፋፋዮች ጋር አብሮ እንደሚሠራ፣ በአጠቃላይ ከ287,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ኩባንያ እንደሆነ የገለጹት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ለአገር አቀፍ የልማት ፕሮጀክቶች ትልቅ አስተዋጽኦ በሚያደርግ የልማት ድርጅት ላይ ጥቃት መፈጸም አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢትዮ ቴሌኮም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ንብረት ነው፡፡ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ኩባንያ ነው፡፡ በሰዎች ጉሮሮ ላይ መቆም የሚያሳዝን ድርጊት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ኩባንያው ንብረትነቱ የሁሉም ዜጋ መሆኑንና ለብዙኃን የዕለት እንጀራ የሚያቀርብ መሆኑን ተገንዝቦ ሊጠብቀው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮ ቴሌኮም የንብረት ትመና ሥራ በማከናወን ላይ የሚገኘው ኬፒኤምጂ (KPMG) የተሰኘው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት፣ ሥራውን በማጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የንብረት ትመና ሥራውን አጠናቆ ሁለት ዙር ሪፖርት ለኢትዮ ቴሌኮም ማኔጅመንት እንዳቀረበ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ አሠራር ሥርዓት ሪፖርት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡(ሪፖርተር ~ ቃለየሱስ በቀለ)

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top