በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በ750 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ የተጠናቀቀው የፌዴራል ዳኞች የጋራ መኖሪያ ቤት ተመርቋል።
በምርቃት ስነ-ስርአቱ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የጋራ መኖሪያ ቤቱን ቁልፍ ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢ/ር አይሻ መሀመድ ተረክበዋል።
ሚንስትሯ በምርቃት ስነ-ስርአቱ ላይ እንደተናገሩት አገራችን የፍትህ ስርዓትን ሙሉ በሆነ መልኩ ለማስፈን ብሎም የዳኝነት አገልግሎቱን ቅልጥፍና ለማሻሻል፣ ጥራቱን ለማሳደግና ነፃነቱንም ለማስጠበቅ ብሎም ዳኞች ሙሉ አቅማቸውን በዳኝነት ስራ ላይ እንዲያውሉ በማድረግ በኩል የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ያለው ትርጉም እጅግ ታላቅ ነው።
የመኖሪያ ቤቶቹን የሚረከቡ የፌዴራል ዳኞች መንግስትና ህዝብ የጣለባችው ከባድ ኃላፊነት በመወጣት በኩል የመኖሪያ ቤት ችግሩ በዚህ ደረጃ መቃለሉ የሚኖረው ሚና የላቀ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ በቀጣይ የመንግስት ሠራተኞችን ያለባቸውን የመኖሪያ ቤት ዕጥረት ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በበኩላቸው ከአራት ዓመት በላይ ስራ ላይ የነበረው ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት ላይ በመዋሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቷ አክለውም ለዳኞች ምቹ መኖሪያ ቤት መሰራቱ የዳኝነት ስርዓቱን ቀልጣፋና ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ ዳኞች ህዝብ የሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተክለ ፃድቅ ተ/አረጋይ በበኩላቸው ተቋማቸው በአሁኑ ወቅት የ14 ህንጻዎችን ግንባታ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ እና የፌዴራል ዳኞች የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለት የተጀመረ ቢሆንም ከታሰበለት በታች 750 ሚሊዮን ብር ባልበለጠ በጀት ለማጠናቀቅ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ዕለት 80 ቤቶች እንደተላለፉ የገለፁት ስራ አኪያጁ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ ፕሮጀክት በልዩ ልዩ ምክንያቶች መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ ዘግይቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም በጥራትና በበጀት አፈፃፀም በኩል በስኬት የተጠናቀቀ ነው ማለታቸውን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በማህበራዊ ገጹ ዘግቧል፡፡(ETV)