Connect with us

የአፈወርቅ ተክሌ መኖሪያ ቤት በመጪው ህዳር ወር ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል

የአፈወርቅ ተክሌ መኖሪያ ቤት በመጪው ህዳር ወር ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል
Photo: Social Media

ጥበብና ባህል

የአፈወርቅ ተክሌ መኖሪያ ቤት በመጪው ህዳር ወር ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል

የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ መኖሪያ ቤትን ለጉብኚዎች ክፍት ለማድረግ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

መኖሪያ ቤቱ ከኅዳር 2013 በኋላ የእድሳትና ጥገና ሥራ ተጠናቅቆ ለጉብኝት ክፍት ይሆናል።

በአስገራሚ የሥነ-ጥበብ ሙያቸው በዓለም ታዋቂና ስመ ገናና የነበሩት ሠዓሊ አፈወርቅ ተክሌ ትውልዳቸው በሰሜን ሸዋ በምትገኘውና ”የሸዋ ነገሥታት መናገሻ”በሚል ስያሜዋ በምትታወቀው አንኮበር ከተማ ጥቅምት 13 ቀን 1925 እንደሆነ ይነገራል።

ኢትዮጵያዊ የጥበብ ሰው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ፣ ባሕልና ሥልጣኔ የሚያወሱ የዕደ ጥበብ ውጤታቸውን በማስተዋወቅ አገሪቱን በዓለም መድረክ ያስጠሩና ትልቅ አሻራ የጣሉም ናቸው።

በሥራዎቻችውም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላምን፣ ለሰው ልጆች አንድነትና እኩልነትን በመስበካቸውም ከታላላቅ መሪዎችና ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ ሰዎችና የሃይማኖት አባቶች ዘንድ ዓለም አቀፋዊ ዝናና ክብርን ያተረፉ የሥነ ጥበብ ሰውም ነበሩ።

ታሪክ የማይረሳቸው ታላቅ የሥነ-ጥበብ ባለሙያ ልዩ በሆነ ኢትዮጵያዊ የሥነ ሕንጻ ጥበብ የተሰራውን “ቪላ አልፋ” መኖሪያቸውን ለጉብኝት ክፍት ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ባለስልጣኑ ገልጿል።


የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት የሎሬት አፈወርቅን መኖሪያ ቤትና የስነ-ጥበብ ስራዎቻቸውን ማስጎብኘት ታሪካቸውን ለመዘከርና ቅርሶቹንም አስጠብቆ በማቆየት ትውልዱ እንዲማርባቸው ለማድረግ ድርሻ አለው ።

ለዚህም የመኖሪያ ቤቱ የእድሳትና ጥገና ሥራ በአሁኑ ወቅት ተጠናቆ ሙዚየም ለማድረግ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።ከኅዳር 2013 ጀምሮ ለጉብኝት ክፍት እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በርካታ ጎብኚዎች እንደሚጎበኙት የሚጠበቀው ሙዚዬም፡ በኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት ውስጥም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰር አበባው ገለጻ፤ መኖሪያ ቤቱንና የስነ-ጥበብ ስራዎቹን ለማየት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች አምባሳደሮችና ሌሎች አካላት ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

እንዲሁም የስነ-ጥበብ ባለሙያው የሥራ ውጤቶች ታሪክ እንደመሆናቸው መጠን፤ ቅርስ እንዲሆኑና ሕዝብ እንዲማርባቸው ይደረጋል ሲሉ አብራርተዋል።

ሙዚየሙ የአርቲስቱን የሕይወት ታሪክ እንዲሁም በምስልና በፎቶ የተቀመጡ የስነ-ጥበብ ውጤቶቻቸው እንደሚኖሩም ጠቁመዋል።

ሜትር አርቲስት አፈወርቅ በስነ-ጥበብ ሙያቸው ከ90 በላይ ሜዳሊያዎችና ሽልማቶች እንዳገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ለአብነትም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2004 በአየርላንድ ደብሊን በተካሄደው የሳይንስ፣ የባህልና የጥበብ ጉባዔ ላይ ለሰው ልጆች ትምህርትና ለጥበብ ዕድገት ለዓለም ባበረከቱት መልካም ተግባር “የዳቪንቺ አልማዝ ሽልማት” ተቀብለዋል።

በጉባዔው ላይም በአሜሪካ ዩናይትድ ካልቸራል ኮንቬንሽን (United Cultural Convention) የተባለው ተቋም ለዓለም ጥበብ ዕድገት ላበረከቱት መልካም ሥራ የጀግና ክብር ኒሻንም ተሸልመዋል።

የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 በተወለዱ በ79 ዕድሜያቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።(ኢዜአ)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top