በሰው ልጆች የቀደመ ስልጣኔ ውስጥ ዓባይ ፊት መስመር ላይ ይመጣል:: ስልጣኔዎች ሁሉ በብዛት በውሀማ አካላት አካባቢ ነው የተጀመሩት፤ ከግሽ ዓባይ እስከ ሜዲትራኒያን በሚዘልቅ መንገዱ ውስጥም ዓባይ አይተኬ ሚና ተጫውቷል::
ዓባይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ 40 ከመቶውን የአፍሪካ ሀገራት በተለያየ መንገድ ሲያዋስን፤ 20 ከመቶው አፍሪካውያን ደግሞ በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ የሰፈሩ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: አስራ ሁለት ያህል የአፍሪካ ሀገራት በቀጥታ ዓባይን ቢጋሩትም፤ የሚጠቀሙበት ግብጽ እና ሱዳን ብቻ ናቸው:: ከሱዳንም በላይ ደግሞ ግብጽ የተፋሰሱ አለቃ ሆና የቆመች ይመስላል::
በዚህ ሂደት ውስጥ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት /ኬኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣…/ ዓባይ በመሬታቸው ላይ ያልፋል እንጂ አይጠቀሙበትም:: እስከ 1959 እ.ኤ.አ ባለው ዘመን ዓባይ በብቸኝነት የግብጽ ፀጋ ሆኖ በቅኝ ግዛት ውሎች ታቅፎ ነበር::
ሱዳን እንኳን በ1929 እ.ኤ.አ እንግሊዝ አርቅቃ ራሷ በፈረመችው ውል ተጠቃሚ አልነበረችም:: እንግሊዝ የቅኝ ግዛት ዱካዋን ስታሰምር ከስዊዝ ካናል ጀምራ ዓባይ ከምንጩ የሚጠናቀቅ ነበር:: ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና አረብ ሀገራት ለማለፍ ግብጽን እንደ ማለፊያ ለመጠቀም አውሮፓውያን ግብጽን ይመርጣሉ:: እንግሊዝም በቅኝ ግዛት ዘመኗ አባይን ለግብጽ በመስጠት በግብጽ በኩል የቅኝ ግዛት እጇን ለማርዘም ሞክራለች:: በታሪክ ፊትም አውሮፓውያን ግብጽን የናይል ስጦታ እያሉ ይጠሯት ስለነበር፤ በግብፃውያን በኩል የኔነት ስሜቱ አድጓል::
ግብጽ እና የሀይል አሰላለፏ
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ዘርፍ መምህር የሆኑት አቶ ጥሩነህ አበበ ግብጽ ከአሸነፈው ጋር የመሠለፍ ታሪካዊ አዝማሚያ አላት:: በቀደመው ዘመን በተለይም በ18ኛው እና 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመናት በወቅቱ ፈርጣማ ከነበረችው ከእንግሊዝ ጋር አብራ የቀጠናው ሀገራት ቅኝ እንዲገዙ አድርጋለች:: በዓባይ ወንዝ ላይም የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ውሀ እንዳይጠቀሙ አሳግዳለች::
በ2003 ዓ.ም ኢትዮጵያ በራሷ ጥረት ለመገንባት የወጠነችውን ግድብም እንዳይገነባ ከምዕራባውያን ጋር አብራ ብድር ማስከልከል ችላለች:: በ1950ዎቹ ገደማ የሶሻሊዝም አብዮት ዓለምን በሁለት ጐራ ከፍሎ በቀዝቃዛው ጦርነት ሲከታት፤ ግብጽ በታላቋ ሶቭየት ህብረት በኩል ተሰልፋ የአስዋን ግድብን አስገድባለች::
አሜሪካ በሩሲያ ተቃርኖ ላይ የቆመች ሀገር ስለሆነች የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ በወቅቱ ሞክራ ነበር:: ነገር ግን የዓለም የኃይል አሰላለፍ መቀያየሩ እና በሀገር ውስጥ ያለው ፖለቲካ መርጋት አለመቻሉ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የአባይ ፕሮጀክት እውን ሳይሆን እንደቀረ ጋዜጠኛ ስለአባት ማናየ የአባይ ጉዳይን በቃኘበት መጽሀፍ አትቷል:: ጋዜጠኛ ስለአባት ግብጽውያን በየትኛውም ዘመን እና ሁኔታ፣ በተለየ የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ይሁኑ የዓባይ ጉዳይ የመቼም አጀንዳቸው ነው ሲል የግብጽን አቋም ይገልፃል::
አቶ ጥሩነህ አበበ ደግሞ ‹‹ግብጽ የአረብ ሊግ ሲፋፋም የአረብ ሊግነቷን ታስቀድማለች:: የአፍሪካ ህብረት ከአረብ ሊግ በላይ የተሻለ ተቀባይነት ሲኖረው ደግሞ ወደ አፍሪካ ህብረት ታመራለች::›› የአሰላለፏን ሁኔታ ይተነትናሉ::
ፖለቲካዊ እግሯን በተለያየ አሰላለፍ መትከሏ ለድርድር እና ውሳኔ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል ይላሉ አቶ ጥሩነህ::አሁን ላይ ግን ድርድሩ በአፍሪካውያን መደረጉን ለተፋሰሱ አባል ሀገራት የራስን ችግር በራስ የመፍታት ልምድን የሚያዳብር ሁነት አድርገው ይወስዱታል::
አቶ ጥሩነህ ግብጽ ከቀይ ባህር እስከ ሜዲትራኒያን የመሰሉ ውሃማ አካላትን ብትዋሰንም፤ የከረሰ ምድር ውሀ ሁሉ ያላት ቢሆንም አባይ ላይ ብቻ ቆማ ሌላው እንዳይጠቀም መከልከሏን በኢ-ሞራላዊ ድርጊትነት ይወስዳሉ::
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ፀሀፊ የሆኑት አምባሳደር ሂሩት ገብረሰላሴ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ‹‹የኢትዮጵያ ምርኩዝ የአፍሪካ ህብረት ነው::›› ሲሉ በአፍሪካ የመዳኘትን አግባብነት ያወሳሉ:: በአፍሪካ ህብረት መዳኘት እና ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ማጠናከር የማሸነፊያ መንገዱ እንደሆነም አምባሳደሯ አብራርተዋል::
የዓባይ ፍላጎቷ
ግብጽ በቀዳሚነት በዓባይ ላይ ማንም መጠቀም የለበትም ብላ ታስባለች:: በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሀ ፖለቲካ ተመራማሪ እና የአባይ ጉዳይ ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ እንደሚያብራሩት “ግብጽ ኢትዮጵያ አባይን መገደብ ከጀመረች፤ ሌሎቹ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትም ናይልን የመገደብ ሞራል ያገኛሉ” ስትል ትስጋለች ይላሉ:: ይህ ስጋት ደግሞ ብቻየን ልጠቀም ከሚል የመነጨ ይሆናል::
ምንም እንኳን በግብጽ በበጎ ባይተረጎምም፤ 74 ከመቶ የተጠናቀቀው እና በቅርቡ ሙሌቱ የተጀመረው የዓባይ ግድብ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ማነቃቂያ እና ለቀጠናዊ ትስስርም አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል::
ግብጽ ግን የኢትዮጵያን፣ ዩጋንዳን፣ የኬኒያን ፣… ተጠቃሚነት ወደ ጐን ገፍታ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ እንዳይረጋጋ በተቻለበት ሁሉ ግጭት ለመፍጠር ትንቀሳቃሳለች::
ከ100 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ 65 ሚሊዮኑ መብራት አላገኘም:: ናይልን 86 ከመቶውን ኢትዮጵያ እያመነጨች ምንም አለመጠቀሟ ለግብጽ ግድ አልሰጣትም:: ግብጽ በአስዋን ግድብ አካባቢ ብቻ ከ10 ሚሊየን ኪዩቢክ በላይ ውሃ በትነት ታባክናለች:: ይህ የውሃ መጠን ከአዋሽ ወንዝ የውሃ ይዞታ በሶስት እጥፍ እንደሚበልጥም ፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ ያስረዳሉ:: ኢትዮጵያ ግብጽ በትነት የምታጠፋውን ውሃ ያህል እንኳ መጠቀም አልቻለችም:: ይሄን የተመለከቱ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ከጀመሩ በግድቡ ጉዳይ ኢትዮጵያ መደራደር አልነበረባትም:: ከራሷ የሚመነጭን ወንዝ ገድባ የመጠቀም መልካዓምድራዊ ፖለቲካ(ጂኦፖለቲካው) ይፈቅድለታል ይላሉ:: ኢትዮጵያ ግን ለአብሮነት እና ለቀጠናዊ ትብብር ስትል ውይይት እና ድርድር መርጣለች::
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አሁናዊ የኢትዮጵያ ድርድር ከሙሊቱ ጋር ቢሆንም፤ ግብጽ ግድቡን በአሳሪ ህጐች በማጠር እውን እንዳይሆን ትፈልጋለች ይላሉ:: ይህ የተለጠጠ ፍላጐቷ ለስምምነት ምቹ ባለመሆኑ የሰሞኑ ስብሰባ ያለ ውጤት ተበትኗል:: ግብጽ የግድቡን ሙሌት በማራዘም ኢትዮጵያን የማዳከም ፍላጎት ያላትም ይመስላል::
ግድቡ ከተገደበ በኋላ የአስዋን ሃይቅ በበረሃማ ወቅት ሲጎድል ኢትዮጵያ የመሙላት ግዴታ አለባት የሚል ፍላጎት አላት:: ይሄን ፍላጎቷን ደግሞ አንዴ ከጸጥታው ምክር ቤት ሌላ ጊዜ ከአሜሪካ ጋር፣ የሊጉ አውራ ነኝ ብላ ከምታስበው ከአረብ አባል ሀገራት ሆና ለማሳካት ደፋ ቀና ማለቷ አልቀረም::
ሚዲያዎቿም ኢትዮጵያ ለምትገድበው ግድብ መጥፎ ገጽታ በማላበስ እና የግብጽን የተለጠጠ ፍላጎት በማስተጋባት ዲፕሎማሲያዊ ትርፍ ለማጋበስ እየተንቀሳቀሰች ነው:: ይህ ጉዞዋ ግን ኢትዮጵያን ግድቡን ከመገደብ አልገታትም:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የሰላ ዲፕሎማሲ እና ሀገራዊ አንድነት ኢትዮጵያ በእጀጉ ያስፈልጋታል:: ይህ ገቢራዊ ሲሆን የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ባከበረ መንገድ ኢትዮጵያ ለምትገነባው ግድብ የተፋጠነ ውጤት ይገኝበታል::
(የሺሀሣብ አበራ)
በኩር ጋዜጣ ሐምሌ 13 ቀን 2012 ዓ.ም ዕትም