Connect with us

የኮሮና ወረርሽኝ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አመላከቱ

የኮሮና ወረርሽኝ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አመላከቱ

ኢኮኖሚ

የኮሮና ወረርሽኝ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አመላከቱ

~የኢኮኖሚው ዕድገት በ0.6 በመቶ ሊገደብ እንደሚችል ገምተዋል

የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋት የሚያስከትላቸውን ጫናዎች የተነተኑት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚያደርሰውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች በመንተራስ በሠሩት ጥናት መሠረት፣ በኮሮና ምክንያት ኢኮኖሚው ከ300 ቢሊዮን በላይ ጉዳት ሊያስተናግድ እንደሚችል አመለከቱ፡፡

አጥኚዎቹ ባወጡት ጥናት መሠረት፣ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል መንግሥት የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ114 ቢሊዮን ብር ኢኮኖሚያዊ ድጋፍና ማነቃቂያ በጀት ቢይዝም፣ በመለስተኛና በአስከፊ ደረጃ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመመከት በቂ እንዳልሆነ አስቀምጠዋል፡፡

በመሆኑም ቅደመ ኮሮና ከነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት በመነሳት፣ የበሽታው ሥርጭት ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ለተራዘመ ጊዜ ቢቆይ፣ ኢኮኖሚው እስከ 314 ቢሊዮን ብር የሚገመት ኪሳራ ለማስተናገድ የሚገደድበት ዕድል እንደሚኖር፣ ለተያዘው በጀት የተገመተው የዘጠኝ በመቶ የኢኮኖሚው ዕድገትም ወደ 0.6 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል ምሁራኑ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ሊከሰቱ የሚችሉት ጉዳቶች እንደ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ይዘታቸው የተለያየ ይዘት እንደሚኖራቸው ያመላከቱት የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ፣ በብሔራዊ ኢኮኖሚው ላይ ማለትም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያና ከፍጆታ እንዲሁም ከኢንቨስትመንት ጉዳት አንፃር፣ ከፊስካል ማዕቀፍ ወይም ከመንግሥት ገቢና ወጪ፣ ዕዳና በጀት ጉድለት አንፃር፣ ከውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ማለትም ከዓለም አቀፍ ንግድ፣ ከውጭ ኢንቨስትመንትና ተንቀሳቃሽ ሒሳብ አንፃር፣ ከሥራ ገበያ ማለትም ከሥራ ቅጥር እንዲሁም ደመወዝ አንፃር ብሎም ከቤተሰብ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ደኅንነት አንፃር ትንታኔ ያቀረቡበት ኮሮና አመጣሽ ጉዳትና የፖሊሲ ምላሾቹ ቀርበዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2010/11 እስከ አሁን ድረስ ያለውን ጊዜ መነሻ በማድረግ፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2029/30 ያለው ጊዜ ኢኮኖሚያዊ ግምታቸውን ያስቀመጡት ምሁራኑ፣ ወርኃዊ ደመወዝ ማግኘት ያልቻሉ አባወራዎች ሊደርስባቸው ከሚችለው የገቢ ዕጦትና ኪሳራ፣ በሥራ መቀዛቀዝ ምክንያት ሊከሰት ስለሚችለው ከሥራ የመሰናበት፣ የዓመት ዕረፍት ለመውጣት መገደድ፣ ለይቶ በመቆየት ብሎም በቤት የመቆየትና መሰል ጉዳዮች የሚያስከትሏቸውን ጫናዎችን ሁሉ በማመላከት፣ ሊደርስ የሚችለው ኢኮኖሚያ ጉዳት እስከ ምን ድረስ እንደሚሆን አጥንተዋል፡፡ የምርት፣ የአቅርቦትና የፍላጎት መዳከም በቀጥታ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃዎችን በማቀዛቀዝ በአገር ውስጥ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ጭምር የሚከሰተውን ተፅዕኖ አጣቅሰዋል፡፡

መንግሥት ጣልቃ በመግባት መሠረታዊና ወሳኝ የሚባሉ ድጋፎች አድርጎም፣ በመለስተኛና በከፍተኛ ደረጃ የሚደርሱ ጉዳቶችን ያመላከቱት ምሁራኑ፣ የሠራተኞች የምርታማነት ዕድገት በመለስተኛ ደረጃ እስከ 2.8 በመቶ ገደማ እንደሚቀንስ ሲጠበቅ፣ በከፍተኛ የጉዳት ደረጃ ከታየ ግን ከ6.4 በመቶ ያላነሰ ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

ካፒታል በመለስተኛ ትንበያ የ2.2 በመቶ፣ በከፍተኛ ደረጃ ትንበያ የ2.6 በመቶ ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡ ከፍተኛ ቅናሽ እንደሚያሳዩ ከተገመቱትና እያሳዩ ከሚገኙት መካከል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የውጭ ሐዋላ ገቢ ትልቅ ቦታ ይዘዋል፡፡ በመለስተኛ የጉዳት ግምት ከታየ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የ24 በመቶ ቅናሽ እንደሚያስመዘግብ ሲጠበቅ፣ በከፍተኛ የግምት ስሌት መሠረት የ70 በመቶ ቅናሽ እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡ በቅርቡ የወጣው የመንግሥት መረጃም የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን የ1.7 ቢሊዮን ዶላር በማስመዝገብ አፈጻጸም ማሳየቱን አጥኚዎቹ አጣቅሰዋል፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም በመለስተኛ ግምት የ25 በመቶ፣ በከፍተኛ የጉዳት ስሌት መጠን የ60 በመቶ ቅናሽ እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ እስከ 25 በመቶ ቅናሽ በመለስተኛ የጉዳት ስሌት ግምት መሠረት የተቀመጠ ሲሆን፣ በከፍተኛ የጉዳት ስሌት መጠን ሲቀመጥ ቅናሹ እስከ 50 በመቶ ሊሰፋ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና በውጭ ገዢዎች ዘንድ እስከ 25 በመቶ የፍላጎት ቅናሽ እንደሚያስተናግድ ሲገመት፣ በመለስተኛ የጉዳት ስሌት ዕይታ ግን ቡና ላይ የሚደርስ የገበያ መቀዛቀዝ እንደማይኖር ምሁራኑ ተንብየዋል፡፡ የገቢ ንግድ ላይም ከከፍተኛ የጉዳት ትንበያ አኳያ እስከ 25 በመቶ የሚደርስ የአገር ውስጥ የፍላጎት ቅናሽ እንደሚኖር ገምተዋል፡፡

እንዲህ ያሉ መላምቶችን ዋቢ ያደረገው የምሁራኑ የጥናት ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ. በ2019/20 እንዲሁም በ2020/21 በጀት ዓመት የአጭር ጊዜ የተፅዕኖ ስሌት መሠረት፣ የኮሮና ቫይረስ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ በሚኖረው ቆይታ፣ የኢኮኖሚው ዕድገት ቅድመ ኮሮና፣ እ.ኤ.አ. በ2019/2020 እንደሚኖረው ይታሰብ ከነበረው የዘጠኝ በመቶ ዕድገት ወደ 5.9 በመቶ እንዲሁም በ2020/2021 የ6.7 በመቶ ዕድገት እንደሚያሳይ ተገምቷል፡፡ ይህም በመለስተኛ የጉዳት መጠን የተቀመጠው ሲሆን፣ ሊደርስ የሚችለው የጉዳት መጠን በገንዘብ ሲተመን ከ127 ቢሊዮን ብር እስከ 159 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ተገምቷል፡፡

በከፍተኛ የጉዳት መጠን ሲሰላ የኢኮኖሚው ዕድገት ከሚጠበቀው የዘጠኝ በመቶ በ2020/2021 ወደ 0.6 በመቶ እንደሚያዘቀዝቅ፣ በዚህም እስከ 314 ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ይህም እስከ 13 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ እንደሚያስከትል ባለሙያዎቹ ተንትነዋል፡፡

እንዲህ ያሉ የኢኮኖሚ ጉዳቶች ሊሰከቱ እንደሚችሉ ባሰቡበት የፖሊሲ ጥናት፣ መንግሥት የኢኮኖሚውን 3.5 በመቶ የሚጠጋ ገንዘብ ለኢኮኖሚ ማነቃቂያና ለማኅበራዊ ጉዳት ማካካሻ ይሆን ዘንድ ቢመደብ በቂ እንደማይሆን አስረግጠዋል፡፡ ይህ በገንዘብ ሲገለጽ የ114 ቢሊዮን ብር ወይም የ3.5 ቢሊዮን ዶላር ድጎማና ማነቃቂያ ታክሎበትም፣ የኮሮና ቫይረስ በታችኛው የኑሮ ዕርከን ላይ የሚገኘውን 20 በመቶ ሕዝብ ህልውና ሊፈታተነው እንደሚችል የምሁራኑ ጥናት ያሳያል፡፡

የተቋሙን ሐሳብ ባይወክልም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ‹‹የኮሮና መጠነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት፣ ፖሊሲና የማገገሚያ አማራጮች›› በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገውን ጥናት የማኅበሩ ሦስት አባላት እንዳጠኑትም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ታደለ ፈረደ (ዶ/ር)፣ ማኅበሩን በቅርቡ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት መምራት የጀመሩትና የግብርና ሚኒስርቴር አማካሪው ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) ከዓለም ባንክ አማካሪዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ሞዴሊንግ ባለሙያዋ ሉሊት ምትክ ጋር የተጣመሩበት የፖሊሲ ጥናት ውጤት ለሙያዊ ግምገማ ቀርቦ እንደሚመከርበት ይጠበቃል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊትም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ትንታኔ በእነ ታደለ ፈረደ (ዶ/ር) ይፋ መደረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ እንዳሁኑ ባልተስፋፋበትና በበሽታው መያዛቸው ሪፖርት የተደረገባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ አሥር ሺሕ መጠጋት ባልጀመረበት ወቅት የወጣው የጥናት ሪፖርት፣ ኢኮኖሚው ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት እስከ 200 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ተተንብዮ ነበር፡፡(ሪፖርተር ~ ብርሃኑ ፈቃደ)

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top