ዜና
አረና ከህወሓት ምርጫ ራሱን አገለለ
አረና ከህወሓት ምርጫ ራሱን አገለለ
(ሙሉ መግለጫው እነሆ)
<><><><>
ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉኣላዊነት (ዓረና)
ነፃ፣ ፍትሓዊና ሕገ-መንግስታዊ ባልሆነ ምርጫ አይሳተፍም
1. ዓረና ከተመሰረተ 12 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ ዕድሜው በ2002 ዓ.ምና በ2007 ዓ.ም በተደረጉት ሁለት ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫዎች ዕጩዎቹን አስመርቶ ብርቱ ተፎካካሪ ለመሆን ሞክሯል፡፡ ዓረና በሕወሃት ሙሉ በሙሉ የታፈነውን የፖለቲካ ምህዳር ሰብሮ ለመወዳደር የሞከረው ምርጫው ነፃና ፍትሓዊ ይሆናል ከሚል ግምት ተነስቶ ሳይሆን በሰላማዊ ትግል ሂደት ሊከፈል የሚችለውን መስዋህት ከፍሎ ምህዳሩ ትንሽ ሰፋ እንዲል ለማድረግ ነበር፡፡ በእነዚህ ሁለት ምርጫዎች ሂደት በቅድመ ምርጫና ድህረ ምርጫ ወቅት አራት አባሎችን ሲገድሉ ብዙዎች ታስረዋል ተደብድበዋል ከሥራ ተባርረዋል እንዲሁም ከሀገር ተሰደዋል፡፡
ዓረና እነዚህ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ህዝቡ ዘንድ በመዝለቅ በርካታ የማንቃትና የማደራጀት ፖለቲካዊ ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን በኢትዮጵያ ለተደረገው ፀረ ኢህአዴግ ህዝባዊ ተቃውሞም የበኩሉን ድርሻ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ሂደት በየወቅቱ ብቅ ያሉት የህወሓት ሊቀመናብርትና የክልሉ አስተዳዳሪዎችን ዓረናን በቀንደኛ ጠላትነት በመፈረጅ ስሙንና ክቡሩን ለማጥፋት ብዙ ፓርት አድርገዋል፡፡ ዓረና የትምክህተኛነትና የጠባቦች ተላላኪ ነው፤ ዓረና የትግራይ ህዝብ ደመኛ ጠላት ነው፣ ዓረና አሜኬላና ዝቃጭ ነው፤ ወዘተ. በማለት የትግራይ ህዝብ በድርጅታችን ላይ ኃይል እንዲጠቀም ቀስቅሰዋል፡፡ ተግባራዊ ለማድረግም ሞክረዋል፣ ሆኖም የትግራይ ህዝብ እነሱ በፈለጉት ደረጃ ስላልተንቀሳቀሰ ህልማቸው ከንቱ ሆኖ ቀርቷል፡፡
ህወሓት/አህአዴግ በመላ ሀገራችን ምርጫውን 100% አሸንፌያለሁ ብሎ ካወጀ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ስላልተቀበለውና ይህን ያደረገው በማጭበርበርና በአፈና መሆኑን ስለተገነዘበ ከዳር እስከ ዳር አምጾ አልጋውን ስላነቃነቀው ሳይወድ በግድ ጥልቅ ተሃድሶ አደርጋለሁ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ስለበደልኩ ይቅርታ እጠይቃለሁ በማለት የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ ጥሯል፡፡ ሆኖም የኢህአዲግ አመራር ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ስላጋጠመው ከውስጡ ሹም ሽር ለማድረግ ተገዷል፡፡ በዚህ ሹም ሽርም የህወሓት አመራር ፍፁም ተሸንፎ ከፓርቲው ስለወጣ መቀሌ ሄዶ መሸገ፡፡
የህወሓት አመራር ወደ ትግራይ ማፈግፈግ እንደ ዓረና ላሉ ፓርቲዎች ይበልጥ አስቸጋሪ ምህዳር ተፈጥሮ የነበረው ለዓረና አባላት ጭቆና እንዲባባስና እንዲቀጥል በማድረግ መግቢያ መውጫ እንዲያጡ አድርጓቸዋል፡፡
ዓረና በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የነፈሰውን የለውጥ ነፋስ ተከትሎ ህወሓት መጠነኛ ለውጥ ያደርጋል በሚል ታሳቢ አብሮ ለመስራትና ሰላማዊ ውድድር ለማድረግ በወርሃ መስከረም 2011 ዓ.ም ደብዳቤ ቢፅፍም እስከ አሁን ድረስ ምንም ምላሽ አላገኘም፡፡ ይባስ ብሎ ከሀገሪቱ ሕግ እውቅና ያለውን ዓረና “ባንዳ” የሚል ስም ለጥፎበታል፡፡ ሲፈልግ ባንዳ ሲፈልግ ተላላኪ እያለ ሲያሸማቅቀው ይኖራል፡፡
ህወሓት በአንድ በኩል ሕገ-መንግስቱ ተሽሯል እያለ ቢለፍፍም በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመርገጥ በዓረና አባላትና ደጋፊዎች ላይ ጥቃቶችን እያጧጧፈ ይገኛል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህወሓት አመራር በሚያደርጋቸው ተነስ ታጠቅ የሚሉ ቅስቀሳዎች ሂደት ዓረናን ከምድረ ትግራይ መጥፋት አለበት እያሉ ይቀሰቅሳሉ፡፡ የአባላቱን የስም ዝርዝር ለተሰብሳቢዎች በማንበብ እነዚህን አግልሉ፣ አጥፉ በማለት አውጀዋል፡፡ የዓረና አመራር መኖሪያ ቤት እንዳይከራዩ እንኳ አከራዮችን በመወትወት እንዲያባርሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
እንግዲህ ህወሓት ምርጫ አደርጋለሁ እያለ
ያለው በዚህ የአፈና ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ፍፁም አፈና ማሳደር ባለበት ሁኔታ ሕገ-መንግስቱ መሠረት በማደረግ ምርጫ አካሂዳለው ማለት የምርጫ ዋና ቁምነገር አማራጭ ፖሊሲ በነፃነት ተደምጦ መራጩ እንዲወስን ማድረግ መሆኑን የዘነጋ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከህወሓት ቁጥጥር ውጪ የሆኑና በነፃነት የተደራጁ ሲቪክ ማህበራት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ሚዲያዎች በሌሉበት ነፃ ምርጫ ያካሂዳል ማለት ዘበት ነው፡፡
2. ምርጫና የኮረና ወረርሽኝ
አሁን በሀገራችን የኮረና ወረርሽኝ ገብቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ለህመም እየዳረገ ሲሆን የተወሰኑትን ህይወትም በመቅጠፍ ላይ ነው፡፡ የዚህ በሽታ አደገኛነት ተገንዝቤያለሁ በማለት በትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀድሞ የደነገገው ህወሓት ነበር፡፡ ድሮውንም በአስከፊ አፈና ስር የነበረውን ህዝብ ይህ አዋጅ ታክሎበት ፍፁም የማያላውስና በፀጥታ መዋቅሩ ስር የሚገባ አስከፊ ምህዳር ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ አዋጅ በኋላ በትግራይ የፀጥታ ኃይሎች ከስምንት በላይ ወጣቶችን በመቐለና በሌሎች ወረዳዎች ሲገድሉ ሌሎችንም በጥይት አቅስለዋል፡፡ ከክልሉ በዚህ ምክንያት ሲሰጥ የአስቸኳይ አዋጁን ተላልፈው በመገኘታቸው ነው ብሏል፡፡ የምርጫ ፉክክር በሌለበት በጥይት የሚቆላ መንግስት ለምርጫ በሚደረገው ውድድር ምን ሊያደርግ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ ከሳምንታት በኋላ የፌዴራል መንግስትም የአስቸኳይ አዋጅ አውጇል፡፡ በእኛ እይታ በሌላው የኢትዮጵያ አካልም ይሁን በትግራይ ከአራት ሰዎች በላይ መሰብሰብ በማይቻልበት ሁኔታ ምርጫ ይካሄድ ማለት የፌዝ ያህል እንመለከተዋለን፡፡ እንኳን በአስቸኳይ አዋጅ ስርና ከዛ ውጪም በነፃነት ምርጫ የሚካሄድበት ሁኔታ አልተመቻቸም እንላለን፡፡ ህወሓት ደጋግሞ እንደሚለው አንዳንድ ሀገሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እያለም ምርጫ እያካሄዱ ስለሆነ እኛም ማድረግ እንችላለን ነው፡፡ ህወሓት የሚነግረን በወረርሽኝ ስር እያሉ ምርጫ የሚያካሂዱ እጅግ የተወሰኑ ሀገሮች እንጂ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሀገሮች ግን ምርጫ ለሌላ ጊዜ ማዘዋወራቸውን በመደበቅ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእነዚህ ጥቂት ምርጫ የሚያካሂዱ ያለው የፖለቲካ ምህዳርና በሀገራችን በተለይም በትግራይ ላይ ያለው የፖለቲካ ምህዳር እጅግ አፋኝ መሆኑን በመካድ ነው፡፡ ስለዚህ በሀገራችን ከህወሓት ውጪ ሌላ በኮሮና ወረርሽን ስር ሆነን ምርጫ ይካሄድ የሚል ድርጅት የለም፡፡
3. ምርጫና የሕገ-መንግስት ጥሰት
ዓረና መድረክ በኮረና ወረርሽኝ ስር ሆኖ ምርጫ ይካሄድ የሚል አቋም የሚያራምድ ቢሆንም ምርጫውን ለማራዘም የፌዴራል መንግስት የሄደበት አግባብ ግን ትክክል ነው ብሎ አይቀበልም፡፡ የኤፌዲሪ ሕገ-መንግስት በአንቀጽ ሀ/54.1 ለ) 58.3፣ ሐ. 67.2፣ መ) 72.3 በግልጽ እንዳስቀመጠው የተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የሥራ ዘመን 5 ዓመት ብቻ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ይህ በግልፅ የተደነገገውን አንቀጽ ከሚለው ውጭ መተርጎም ከቶ አይቻልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሕገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄ ያቀረበውና ውሳኔ የሰጡት ተቋማት ራሳቸውን በሚመለከት ጉዳይ ላይ እየወሰኑ ስለሆነ የጥቅም ግጭት (conflict of interest) አስከትሏል ብለን እናምናለን፡፡
የኮቪድ ወረርሽን አስታክኮ የሰጠው ትርጉምም ቀነ ገደብ ስለሌለው ስልጣን የተቆጣጠረው መንግስት እንዳሻው ለመለጠጥ ያስችለዋል ብለን እናምናለን፡፡ በተለይ ደግሞ ሁኔታውን ገምግሞና አጣርቶ ምርጫው እንዲካሄድ እንዲወስኑ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት የአስፈፃሚ አካላት እንጂ ገለልተኛ አካላት ስላልሆኑ እዚህ ላይም የጥቅም ግጭት ይፈጠራል የሚል አቋም አለን፡፡ በመሆኑም ሕገ-መንግስቱ በመተርጎምና የምርጫው ጊዜ መቼ እንደሚሆን የመወሰን ስልጣን የጥቅም ግጭት ባላቸው አካላት የተወሰነና የሚወሰን በመሆኑ ዓረና አጥብቆ ይቃወመዋል፡፡
የሕገ-መንግስት ጥያቄ ከተነሳ ዘንድ ህወሓትም ሕገ-መንግስቱ ተጥሷል በማለት ሲቃወም ይደመጣል፡፡ ህወሓት በየአምስት ዓመቱ መካሄድ ያለበትን ምርጫ የፌዴራል መንግስት በማራዘሙ ተቀባይነት የለውም ሕገ-መንግስቱ ያጎናጸፈኝን መብት ተጠቅሜ በተናጠል ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ ወስኗል፡፡ ከዚያ አልፎም የራሱን የምርጫ ሕግ-አውጥቷል የምርጫ ቦርድም አቋቁሟል፡፡ አብዛኛዎችን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች በመጣል የለየለት አምባገነን መንግስት በኢትዮጵያና በትግራይ ያቋቋመ ድርጅት መልሶ ከሳሽ ሲሆን እጅግ ያስገርመናል፡፡ ያም ሆኖም መቃወም መብቱ ነው፡፡
የህወሓት መከራከሪያ ነጥብ ምርጫ ለዜጎችና ለክልሎች የተሰጠ መብት ስለሆነ ከምርጫ ቦርድም ይሁን በሌላ መንግስታዊ አካል ሊከለክል አይገባም የሚል ነው፡፡ ስለሆነም ይህን ሕገ-መንግስታዊ መብቴን ተጠቅሜ ምርጫ ማካሄድ ለዲሞክራሲ ባለኝ ቀናኢነት የፀና አቋም የተነሳ ነው ይላል፡፡ እኛም ምርጫ የዜጎች የማይገሰስ ዴሞክራሲያዊ መብት መሆኑን እናምናለን፡፡ ሆኖም ይህን ለማድረግ በማይቻልበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ተገቢ አይደለም፡፡ ለዚህ ንብረት የሚሆነውም በሀገራችን በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በየአምስት ዓመቱ መካሄድ እንዳለበት ቢደነግግም በትግራይ ጭምር የወረዳና የቀበሌ ምርጫዎች ሳይካሄዱ 7 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህም ተቀባይነት ያገኘ በአስገዳጅ ሁኔታ ምክንያት ነው፡፡
ሌላው ህወሓት የዘነጋው ጉዳይ ቢኖር በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 102.1 በግልፅ እንደተቀመጠው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው ለብሄራዊ ምርጭ ቦርድ ነው፡፡ ይህ አካል በሕገ-መንግስቱ መሠረት የተቋቋመ በመሆኑ የምርጫ አስተዳደር ይሁን የፓርቲዎች አስተዳደር የተሰጠው ለዚህ አካል ብቻ ነው፡፡ አንዷን የሕገ-መንግስት ድንጋጌ ተጥሷል ብለው እያወገዙ ሌላውን መልሶ መጣስ ትርፉ ትዝብት ነው፡፡ ሕገ-መንግስቱ የፌዴራል መንግስት ከጣሰው እኔም ልጥሰው እችላለው ብሎ ጨዋታ አይኖርም፡፡ ሕገ-መንግስቱ የጣሰውን አካል በጋራ ከመቃወምና ከመታገል ውጪ አማራጭ አይኖርም፡፡
4. የህወሃት የምርጫ ውሳኔ ሂደት ኢ-ሕገ-መንግስታዊና ኢ-ህጋዊነት
አስቀድሞ በትግራይ ምርጫ እንዲካሄድ የወሰነው የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ነው፡፡ የሥራ አስፈፃሚውን ውሳኔ ተከትሎ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል፡፡
ከዚያ በኋላ ጉዳዩን “ሕጋዊነት” ለማላበስ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውሳኔው ፀድቋል፡፡ በዚህ መሠረት የጉዳዩ ቀስቃሽ በትግራይ እንደሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁሉ ባለድርሻ የሆነ ፓርቲ እንጂ ገለልተኛ አካል አይደለም፡፡ ገዢ ፓርቲ ይሁን ተፎካካሪ ምርጫን በተመለከተ እኩል መብት ይኖራቸዋል እንጂ አንዱ ከሌላው የተለየ መብት የለውም፡፡ በመሆኑም የምርጫ ጉዳይ የህዝብና ህዝቡ በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የመረጠው መንግስት ጉዳይ ሆኖ እያለ ጉዳዩን አስቀድሞ የወሰነው የህወሓት አመራር ነው፡፡ ይህም አግባብነት የለውም፡፡
የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ቁም ነገር ገለልተኛ በሆነ አካል የሚዳኝ ሂደት መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ በሀገራችን ይህ ስልጣን የተሰጠው አካል ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ሕገ-መንግስታዊም ሕጋዊም ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ የቦርዱ ገለልተኝነትን በተመለከተ ህወሓት ይሁን ሌላ ጥያቄ ሊያቀርብና ሊከስ ይችላል፡፡ የምርጫ ቦርድንና የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትን ተክቶ ግን ሕግ ሊያወጣና ሌላ ምርጫ ቦርድ ሊያቋቁም አይችልም፡፡ ይህን ሊያደርግ የሚችለው በግላጭ ከኢፌዲሪ መንግስት ወጥቻለሁ ብሎ ሲያውጅ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም በምርጫ ቦርድ ላይ ሌላ ምርጫ ቦርድ ማቋቋም በሕግ ጭምር ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡
ህወሓት ራሱ የምርጫ ሕግ በመደንገግና የምርጫ ቦርድ በማቋቋም ምርጫ አካሂዳለው ሲል “ራሱ ተጫዋች ራሱ ዳኛ” እየሆነ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡ ዓረና በዚህ ምርጫ ላለመሳተፍ የወሰነበት አንዱ ምክንያትም ይህንን ሕግ ያወጣ ህወሓት ሕገ-መንግስቱን በግላጭ የሚፃረር የምርጫ አካሄድ በመምረጡ ነው፡፡
ከዚህ ሌላ ህወሓት አካሂደዋለሁ በሚለው ሕገ-ወጥ ምርጫ ከተቋቋመ 12 ዓመታትን ያስቆጠረውና በትግራይ ፖለቲካ ተፅዕኖ ያለውን ዓረናን አግልሎ ራሱ የመረጣቸው ፓርቲዎች አቅፎ ለመሄድ መወሰኑ ነው፡፡
ህወሓት ዓረና ቀርቶ በሀገራችን በቅርቡ በሕግ የተመዘገቡትን ብልጽግና፣ ትዴፓና ዓሲምባ ጭምር እንዲሳተፍ ማድረግ ነበረበት የማግለል ሕገ-መንግስታዊ ይሁን ሕጋዊ ስልጣን የለውም፡፡ የህወሓት ይሁን የሌሎች ፓርቲዎች ህልውና በሀገራዊው የፓርቲዎች ሕግ ላይ የተመሰረተ እንጂ በህወሓት በጎ ፈቃድ ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡ በዚህም ሕገ-መንግስቱንና የሀገራችን ሕጎችን እየጣሰ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ሌላው ህወሓት ሊያጤነው የሚገባ ጉዳይ ራሱ ያቋቋመው የፌዴሬሽን ምክር ቤት እስከሚቀበለው ምርጫ ሁሉም የፌዴራልና የክልል መንግስታት እንዲቀጥሉ መወሰኑን ነው ውሳኔው ኢ-ሕገመንግስታዊ ነው ሊባል ቢችልምይህን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን የተገለጸው እንጂ ማፈንገጥ ከቶ አይቻልም፡፡ ይህ ከሆነ ህወሓት በምርጫ የሚያቋቁመው መንግስት ሕገ-ወጥ ተብሎ የትግራይን ህዝብ መንግስት አልባ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ህወሓት ነጋ ጠባ የሚያንቀሳቅሰውን “የዲፋክቶ ሀገረ መንግስት” ህልም የማሟላት አንዱ እርምጃ አድርጎ ከመወሰዱም ይበልጥ አደገኛና ህዝቡን ለግጭት የሚዳርግ ይሆናል፡፡ ይህም ኃላፊነት ከጎደለው ፓርቲ ብቻ የሚመነጭ ይሆናል፡፡
5. መፍትሄዎች
5.1. ዓረና ህወሃት እየሄደበት ያለው የምርጫ እንቅስቃሴ ኢ ሕገመንግስታዊና ኢ-ሕጋዊ በመሆኑ ይህን ውሳኔውን በማጤን ሊቀለብሰው ይገባል፡፡ በዚህ ምትክ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆንና በተናጠል ከፌዴራሉ መንግስት ጋር የምር ድርድር እንዲያካሂድ ይመክራል፡፡
5.2. የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተቀጣጠለበትና አደጋው እየጨመረ በሄደበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ለስልጣን እንጂ ለህዝብ ደህንነት ደንታ ቢስነትን ስለሚያመለክት ዋና ትኩረት የክልሉን ህዝብ ነዋሪዎች ደህንነት በማስጠበቅ ላይ እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
5.3. ምርጫን በማሳበብ የተሻለ ሕጋዊ እውቅና ያገኘውን ምክር ቤት በትኖ ሌላ ኢ-ሕጋዊ ምክር ቤትና መንግስት ለማቋቋም የሚያደርገው ጥረት ራስን ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት በስልጣን ለማቆየት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ፋይዳ አይኖረውም የሚመረጠው ምክርቤት ይሁን መንግስት ያው አሁን ያለው የህወሓት ብቸኛ መንግስት ነው፡፡ ሆኖም ይህ ድርጊት ህገ-ወጥ በመሆኑ የሚያስከትለው የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና፣ የፀጥታ ችግር ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ይህን አላስፈላጊ ውጥረትና ግጭት ለማስቀረት ህወሓት ያቀደውን ምርጫ እንዲያስተላልፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
5.4. ህወሓት የፈለገው ምርጫ ይካሄድ እንኳ ቢባል በአንድ ወር እንቅስቃሴ የሚካሄድ በመሆኑ ከፍትሃዊነት አንፃር ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ምርጫ ሁሉም ተወዳዳሪዎች በቂ ጊዜ አግኝተው ደጋፊያቸውን አሳምነው የሚፎካከሩበት ሂደት እንጂ የአንድ ወቅት እርምጃ ባለመሆኑ ይህን ያላሟላ ኢ-ፍትሃዊ ምርጫ ከማካሄድ እንዲቆጠብ እናሳስባለን፡፡
5.5. ባለንበት ዘመን አነስተኛውን መስፈርት የሚያሟላ ምርጫ ለማካሄድ ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ የሆኑ የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ከተቻለም ገለልተኛ የሆኑ ዓለምአቀፍ ታዛቢዎች መገኘታቸው የግድ ይላል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ራሱ ህወሓት የመለመላቸው የምርጫ አስተዳዳሪዎች፣ በስሩ ያሉትን የብዙሃን ማህበራትን አሰማርቶና ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን አግልሎ የሚያደርገው ምርጫ ምንም ክልላዊ፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑ ባሻገር እጅግ አስፈሪም ስለሆነ ለህዝባችን ይመቻል አንልም፡፡ ስለሆነም በተለመደው ህወሓት ማለት የትግራይ ህዝብ ህወሓት ማለት መሪ ድርጅት ስለሆነ ያሻውን ሊያደርግ ይችላል በሚል እሳቤ የሚካሄድ ምርጫ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ አንድምታው አደገኛ ስለሆነ ሊቆም ይገባል እንላለን፡፡
5.6. ህወሓት ከአሁን በፊት ይጠቀምባቸው ከነበሩት ፀያፍና አግላይ የስድብ ውርጅብኞች እንዲቆጠብም እናሳስባለን፡፡ በተለይ በድርጅታችን በቅርቡ ያወጀውን ባንዳ የሚል ፍረጃ በሕግም ጭምር የሚያስጠይቀው ስለሆነ እንዲያቆም እናሳስባለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዓረናን አባላትና ደጋፊዎችን በህዝብ ስብሰባ ፊት በማጋለጥ እንዲወገሩና እንዲገለሉ እየተላለፈ ያለው መልዕክት ቶሎ እንዲቆም እናሳስባለን፡፡
5.7. በዓረና በኩል ምርጫ አካሂዳለሁ እያለ በሌላ በኩል ለጦርነት ተዘጋጁ የሚለው ቅስቀሳ ተገቢ ያልሆነና ህዝብ ለከፍተኛ ጉዳት የሚዳርግ አደገኛ አካሄድ ስለሆነ ህወሓት ከዚህ ተግባሩ እንዲቆጠብም እናሳስባለን፡፡ ከእንግዲህ በትግራይ ላይ የሚደርስ በደል ሁሉ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ አግባብ መታገል እንጂ በጦርነት ሊሆን ስማይገባው የጦርነት ቅስቀሳ እንዲቆም እናሳስባለን፡፡
5.8. ህወሓት የሚያደርገውን የምርጫና ራስን ከሌላው ኢትዮጵያዊ የማግለል ኢ-ሕጋዊ እንቅስቃሴ ተገቢ እንዳልሆነ እያሳሰብን የፌዴራል መንግስትም ከህወሃት ጋር ይሁን ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የምር ድርድር በማድረግ ያለውን የሀገራችንን የፖለቲካና የፀጥታ ቀውስ ማርገብ እንዳለበት አበክረን እንጠይቃለን፡፡
እስከአሁን ያለው ቀውስ መሰረታዊ መንስኤ የግለሰቦችና የተወሰኑ ፓርቲዎች ሴራ ውጤት ሳይሆን የገባንበት የፖለቲካ ቀውስ ጥልቀት በቅጡ ስላልተፈታ መሆኑ ስለምንገነዘብ አሁንም ከዋና ዋና ፓርቲዎች ጋር በወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ ድርድር እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡ በሀገራችን ችግር መፍትሄ ከድርድርና ሰጥቶ ከመቀበል ውጪ ሃይልና ጦርነት መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚያሻም እናሳስባለን፡፡
5.9. ህወሓት በዓረና አመራሮችንና አባላትን የሚያደርገውን ህገ ወጥ ጫናዎች ማለትም ከቤት ኪራይ የማባረር፤ስድብ፤በግድያ ማስፈራራት፤ማግለል፤ዛቻ፤ እስር፤ ድብደባና የመሳሰሉ ነገሮች በማቆም በቅርቡ ሰባት የዓረና አባላትና አመራሮች የዓረና ፓርቲ የቁጥጥር ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ የሆኑ አቶ ፅጋቡ ቖባዕ የሚገኙባቸውና ካሁን በፊትም በፈጠራ ወንጀል እስከ ለ20 አመት ፍርድ ሰለባ የሆኑ የፖለቲካ እስረኞችን ህወሓት እንዲፈታቸው በመጠየቅ ይህንን ለህወሓት ህገወጥ ምርጫም ቢሆን የማይጠቅምና የትግራይ የፖለቲካ ምህዳሩንም ለማስፋት አሉታዊ ተፅእኖ ስላለው ቶሎ እንዲፈፀም እናሳስባለን፡፡
ዓረና ሓምለ 17 ቀን 2012 ዓ/ም