ሃጫሉን ያነጋገረው ጋዜጠኛ ታሰረ
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦኤምኤን) ጋዜጠኛ ጉዮ ዋሪዮ ዛሬ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የቤተሰቡ አባላት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከመገደሉ ከአንድ ሳምንት በፊት በኦኤምኤን በተላለፈው ቃለ መጠይቅ ላይ ድምጻዊውን ቃለመጠይቅ ያደረገው ጉዮ መሆኑ ይታወሳል።
ቢቢሲ ከቤተሰቡ አባላት እንደሰማው ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም እኩለ ቀን ላይ “የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት ዩኒፎርም የለበሱ” ጉዮን ከመኖሪያ ቤቱ ይዘውት ሄደዋል።
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የአዲስ አበባ ቢሮ የተዘጋው የሃጫሉ መገደልን ተከትሎ በተፈጠረው ግርግር ሰኔ 24 ማክሰኞ ዕለት ነበር።
ለቢቢሲ በቁጥጥር ስር መዋሉን የተናገሩት አንድ የቤተሰቡ አባል እንዳሉት ከሆነ፤ የጸጥታ አባላቱ ጉዮን የት ይዘውት እንደሚሄዱ ለመናገር ፍቃደኛ አልነበሩም።
እኚህ የቤተሰቡ አባል እንደሚሉት “የጸጥታ ኃይሎቹ በመሳሪያ ስላስፈሯሯቸው” ተከትለውት መሄድ እንዳልቻሉ ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በሰጠው መግለጫ ላይ፣ ድምጻዊው ከኦኤም ኤን ጋር ያደረገው ቃለመጠይቅ የ1 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ርዝመት ቢኖረውም “ሆነ ተብሎ ብሎ አንዳንድ ክፍሎቹን ቆርጦ አውጥቷል” ሲል ተናግሮ ነበር።
በኦኤምኤን ላይ ተላለፈው የድምጻዊ ሃጫሉ ቃለ መጠይቅ ጠቅላላ ርዝመት 47 ደቂቃ ብቻ ነበር።
እንደ አቃቤ ሕግ መግለጫ ከሆነ ተቆርጦ የወጣው ቃለመጠይቅ ድምጻዊው” ከኦነግ ሸኔ የሚደርስበትን ዛቻ” የሚገልፀው ክፍል ነበር።
በአቃቤ ሕግ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክተሮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቃዱ ፀጋ በመግለጫው ወቅት ጠያቂው “ሆነ ብሎ አርቲሰቱን ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር የሚያጋጨውን ነገር እንዲናገር ለማድረግ ግፊት ሲያደርግ ነበር “ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ከዚህ ቀደምም ሌላኛው የኦኤምኤን ጋዜጠኛ የሆነው መለሰ ዲሪብሳ በቁጥጥር ስር መዋሉን ቢቢሲ አረጋግጧል።
የኦኤምኤን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ግርማ ጉተማ ሚዲያው ከተዘጋ በኋላ “ጋዜጠኞቹ በስጋት ስልካቸውን አጥፍተው ተደብቀው እንዳሉ” ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
አቶ ግርማ ጉተማ አክለውም የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ እንዲዘጋ መደረግ “ከዚህ ቀደም የነበረ ፍላጎት እና ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያለው ነው” ብለው ነበር።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከዚህ ቀደም ሃጫሉ ሁንዴሳን “ኦኤም ኤን አሳልፎ ሰጠው” ሲሉ ጠንከር ባለ ቃል መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ጉዮ ዋርዮ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለቢቢሲ ሰጥቶ በነበረው ቃለመጠይቅ እንደተናገረው “እኔ የእርሱን እውነታ ለማሳየት እንጂ አሳልፌ አልሰጠሁትም” ሲል ተናግሮ ነበር።(BBC)