Connect with us

የተማሪዎች ቀጣይ እጣ የሚወሰነው ት/ ሚር በሚያስተላልፈው መመሪያ መሰረት ነው

ሚኒስቴሩ በቀጣይ ዓመት የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ እንዳይደረግ አገደ
Photo Solomon Yemer

ዜና

የተማሪዎች ቀጣይ እጣ የሚወሰነው ት/ ሚር በሚያስተላልፈው መመሪያ መሰረት ነው

በኮቪድ 19 ምከንያት በተቋረጠው ትምህርት ዙሪያ የተማሪዎች ቀጣይ እጣ ፋንታ አገር አቀፉ ኮማንድ ፖስት በሚያስተላልፈውና ትምህርት ሚኒስቴር በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት የሚወሰን መሆኑ ተገለጸ። የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ሀረጓ ማሞ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በቤት ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት በሁሉም የአገሪቱ ክፍል በሚፈለገው ደረጃ ተደራሽ ነው ተብሎ ባይታመንም ብዙዎችን ከጭንቀት ለማላቀቅና ከትምህርት እርቀናል የሚል ስሜት እንዳይሰማቸው ለማድረግ አግዟል። ሆኖም ግን ትምህርቱና የቀጣይ ክፍል ዝውውር የሚወሰነው በኮሮና ወረርሽኝ መቆምና በመንግስት ውሳኔዎች መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን የትምህርት ስርጭት በተለይ ክልሎች ላይ ሰፊ መሰናክል እንደሚያጋጥም የጠቆሙት ወይዘሮ ሀረጓ፤ በመብራትና በስርጭት ጥራት የተፈለገውን ያህል ትምህርቱን ማዳረስ አለመቻሉን ገልጸዋል። አሁን እየተሰጠ ያለው ትምህርት በምንም መልኩ ከመደበኛ ትምህርቱ ጋር የሚገናኝ አይደለም ያሉት ወይዘሮ ሀረጓ መደበኛውን ትምህርትም አይተካም ብለዋል። እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ትምህርቱ ሁሉንም ተማሪ የሚያቅፍበትና በእኩል ደረጃ ግንዛቤው የሚያዝበት ሁኔታ አለ የሚያስብል ስላልሆነ ከውጤት ጋር አያይዞ ለማስኬድ ከባድ ነው። የጥራት ጉዳይንም አደጋ ውስጥ ሊከተው ይችላል ብለዋል።
ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የማያገኙ ተማሪዎችም ቀደም

ሲል የተማሩትን ትምህርት ከደብተራቸው እና እጃቸው ላይ ያለውን መጽሐፍ በፕሮግራም እንዲያነቡ በማድረግ ቤተሰብ ሰፊውን ድርሻ ይዞ እየሰራ መሆኑ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ አበበ ቸርነት በበኩላቸው እንዳሉት፤የተማሪዎች የቀጣይ እጣ ፋንታ አገር አቀፉ ኮማንድ ፖስት በሚያስተላልፈውና ትምህርት ሚኒስቴር በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት የሚወሰን ነው።

ተማሪዎች ከመምህራን ጋር ያላቸው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ በመቋረጡ ቤተሰብ ኃላፊነቱን ወስዶ ልጆቹን በተቻለ መጠን መደገፍ እንዳለበትም አሳስበዋል። በኮሮና ምክንያት ትምህርቱ ቢቋረጥም በሁለት የሬዲዮ ጣቢያዎችና በማህበራዊ ድረገጾች ተማሪዎች አቅማቸውን የሚያጎለብቱበትና ትምህርቱን አውቀው የሚሄዱበት ስርጭት እየተላለፈ ይገኛል።

ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች ሂሳብ፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስና ኬሚስትሪ ትምህርት በቴሌቪዥን ይሰጣል፤ በኤፍኤም 94 ነጥብ 7 የሬዲዮ ጣቢያ ደግሞ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። በተመሳሳይ በቴሌግራምና ማህበራዊ ሚዲያዎች የስምንተኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን እስከ መፈተን የደረሱ ሥራዎች ተሰርቷል። የትምህርት ስርጭቱ በቋሚነት ቢከናወንም ተማሪዎቹ ራሳቸውን እንዲፈትሹ እንዲሁም ከትምህርቱ እንዳይርቁ ለማድረግ እንጂ ወደቀጣዩ ክፍል ለማዛወር እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ አበበ፤ ለቀጣይ ትምህርት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ስለሚጠቅም በቀጣይም መሰጠቱ ይቀጥላል ብለዋል።

አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012 | ጽጌረዳ ጫንያለው

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top