ግብጽ ለዘመናት የአባይ ወንዝን ውሃ ፍትሃዊነት በጎደለው መንገድ ስትጠቀም ቆይታለች። ይህ ህልሟ ለዘለዓለሙ እንዲቀጥል ለማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትሰራው ግድብ የተፋሰሱን አገራትንና ቀጠናውን ክፉኛ እንደሚጎዳ ለማሳየት ደፋ ቀና ስትል ይታያል። የተዛባና ሽንገላ የተሞላበት ትርክት በማቅረብም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማሰናከል ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ሌት ተቀን እየጎተጎተች ትገኛለች።
የሥነፍሳሽ ኤክስፐርቶች ደግሞ ይህን መሰረት የሌለው ክስ ከማጣጣላቸውም ባሻገር የግብፅን ቅጥ ያጣ የውሃ አጠቃቀምም ሆነ ብክነት ሲተቹ ይደመጣል።
ኢንጂነር መቅደላዊት መሳይ ሲቪል ኢንጅነርና ተመራማሪ ስትሆን በአባይ ወንዝ የአየር ንብረት ላይ በግል ጥናት በማድረግ ትታወቃለች። በፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዲግሪ እጩ ነች።በአሁኑ ሰዓት 66 በመቶ የሚሆነው ውሃ ለዚህች አገር ሲደርስ 22 በመቶ የሚሆነው ወደ ሱዳን ይሄዳል ትላለች። ግብፅ ታሪካዊ መብት እንዳላት ቆጥራ አባይን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር መሞከሯ ምንም መሰረት የሌለው መሆኑንም ታነሳለች። የቅኝ ግዛት ስምምነቱ እስካሁን ድረስ መቆየቱ በራሱ ስህተት መሆኑን ትናገራለች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠ ማንኛውም ህግ ታሪካዊ መብት አለኝ የሚለውን ትርክት አይቀበለውም። ድንበር አቋርጦ የሚሄድ ማንኛውም ወንዝ ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሁሉም አገራት ሊጋሩት ይገባል›› የምትለው ኢንጂነር መቅደላዊት፤ ኢትዮጵያ ድርድሩን እያደረገች የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ማፋጠንና ዘላቂ ልማቷን መቀጠል እንዳለባት ትመክራለች። በማንኛውም መንገድ ድርድሩ እስኪጠናቀቅ በሚል በሀምሌ ውስጥ ሊካሄድ የታሰበው የውሃ ሙሌት መቆም እንደሌለበትም ምክረ ሃሳቧን ታስቀምጣለች።
የቅኝ ግዛት ዘመን ፍላጎት የተጫነው ክፍፍል ቀሪውን የአባይን ውሃ በዓለም እጅግ ሞቃታማ በሆነው የሰሃራ በረሃ በትነትና ስርገት ባክኖ እንዲቀር የፈረደ ከእውነት የተጣላ የፍትህ ሚዛን ነው የሚለው ደግሞ የስነ ፍሳሽ ኤክስፐርቱ ምንዬ ተማም ነው። እንደ ባለሙያው ገለፃ፤ ለረጅም ዘመናት ግብፅ ከአባይ ወንዝ ላይ ብቻ በምታገኘው ውሃ ጥገኛ የሆነች ምስኪን አገር እንደሆነች በፕሮፓጋንዳ እየተነዛ ቢቆይም እውነታው ግን ከዛ የራቀ ነው።
በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ድርጅት (ፋኦ) ባወጣው ሪፖርት ግብፅ ከዝናብ ብቻ 51 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ታገኛለች። ይህ ማለት ይገባኛል ብላ ከምትጠይቀው የአባይ ውሃ ጋር የሚስተካከል ነው። ይህን ውሃ በአግባቡ አለመጠቀሟን ተከትሎ በአገሪቷ መቀመጫውን ያደረገው አልሃራም ኦንላይን በተደጋጋሚ ትችት ሲሰነዝር መደመጡን መመልከት በቂ ነው።
‹‹የአስዋን ግድብን ተከትሎ የተፈጠረው ሰው ሰራሽ ሃይቅ በዓለም ላይ የመጀመሪያውና ትልቁ ነው። 479ኪ.ሜ ርዝማኔና 16 ኪ.ሜ ስፋት አለው። ሆኖም ግብፅ የአባይን ግድብ ግዝፈት በማጋነንና በቀጠናው ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በማጉላት የፕሮፓጋንዳ ስራ በከፍተኛ ሁኔታ ትሰራለች›› የሚለው የስነ ፍሳሽ ባለሙያው፤ የናስር ሃይቅ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሙቀትና ሃሩር ባለበት ክልል በመሰራቱ በዓመት ቢያንስ ከ10 እስከ 16 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዲባክን ያደርጋል ይላል። ይሄ በየዓመቱ ባክኖ የሚቀር ውሃ ደግሞ የታላቁ ህዳሴን ግድብ ሙሌት በአራትና አምስት ዓመት ለመሙላት የሚያስችል አቅም ያለው ነው። በአንፃሩ ደግሞ የህዳሴው ግድብ የሚይዘው ውሃ በትነትና ስርገት የመባከን እድሉ አንድ አምስተኛው ብቻ ነው። ይህ ማለት አንድ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የማይበልጥ ነው።
‹‹በናስር ሃይቅ ላይ 20 በመቶ የሚሆነውን የአባይ ውሃ በማባከን ቅጥ ያጣ አጠቃቀም የምትከተለው ግብፅ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ጥያቄ ውስጥ የመክተት የሞራል ልእልና አይኖራትም›› የሚለው ባለሙያው፤
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከግብ እንዳይደርስ እንቅፋት ከመሆን ይልቅ የውሃ አጠቃቀም ፖሊሲዋን መለስ ብላ ማየትና ማስተካከል ይገባታል ብሏል።
ከፍተኛ ባለሙያዎች በቅርቡ በግድቡ ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ላይ ተሳታፊ የነበሩት ዶክተር ዮናስ ብሩ እንደገለጹት፤ ግብፅ ትሪሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በከርሰ ምድር ውስጥ አላት። በውሃ ሀብት ክምችቷም ከኢትዮጵያ የተሻለች ነች። የሳይንስ መዘመንን ተከትሎም የውቅያኖስን ውሃ አክሞ መጠቀም የሚቻልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። በመሆኑም የቅኝ ግዛት ዘመን ትርክት ይዞ ‹‹እኔ ብቻ ልጠቀምበት፤ እናንተ ተራቡ›› የሚለውን ቀልድ ልታቆም ይገባል ይላሉ። ታላቁ ህዳሴ ግድብ 86 በመቶ የሚሆነውን ወደ ሱዳን የሚሄድ ደለል ማስቀረት ከመቻሉም በላይ በትነት የሚባክነውን ውሃ የሚያድን ፕሮጀክት መሆኑን ይገልፃል።
እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ግብፅ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ታባክናለች። በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚይዘው ውሃ ህልውናዬን ይፈታተናል በሚል ልማቱን ለማደናቀፍ ዓለም አቀፍ ፕሮፓጋንዳ ትነዛለች። የኢትዮጵያ መንግስት በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ይሄን አካሄድ ማጋለጥ ይገባዋል። የግድቡን ግንባታና የውሃ ሙሌት ለሰከንድ እንኳን ማራዘም ተገቢ አይደለም ሲሉ ሞግተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012 | ዳግም ከበደ