Connect with us

«ኢትዮጵያውያንን ማሳቅ ከባድ ነው» ኮሜዲያን ደምሴ ፍቃዱ (ደምስ ዋኖስ)

«ኢትዮጵያውያንን ማሳቅ ከባድ ነው» ኮሜዲያን ደምሴ ፍቃዱ (ደምስ ዋኖስ)
Photo: Social Media

ጥበብና ባህል

«ኢትዮጵያውያንን ማሳቅ ከባድ ነው» ኮሜዲያን ደምሴ ፍቃዱ (ደምስ ዋኖስ)

ሳቅን ደግሰው በተሰናዱ ሁነቶችና መዝናናትን ሽተው በሚካፈሉባቸው ትልልቅ መድረኮች ላይ እርሱ መድረክ አድማቂ፣ የዝግጅቱ ማጣፈጫ ቅመም፣ የመርሀ ግብሩ መድረክ መሪና የድግሱ ፍካት ሆኖ ያገኙታል። የድምፅ ማጉያውን ጨብጦ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመመርኮዝ የሚያቀርባቸው ቁም ነገር አዘል ቀልዶቹ ታዳሚውን በሳቅ ያፈርሳሉ። በተለያዩ መድረኮች ላይ ለዝግጅቶቹ ከሚያሰናዳቸው ቀልዶች በተጨማሪ በተገኘበት አጋጣሚ ሁሉ ወዲያው ፈጥሮ አብሮት ያለን ሰው ቆይታ በሳቅ የታጀበ የደስታ ጊዜ እንዲሆንለት የማድረግ ልምዱ በብዙዎች ተወዳጅ አብረውት ሊሆኑ የሚመኙት አድርጎታል፤ዝነኛው ኮሜዲያን ደምሴ ፍቃዱ።
በዛሬው የዝነኞች የዕረፍት ውሎ አምዳችን በቁም ነገር አዘል ቀልዶቹ በአድማጭ ተመልካቾች ዘንድ እውቅናና ዝናን ያተረፈው ኮሜዲያን ደምሰው ፍቃዱ ጋር በነበረን ቆይታ ስለ ሕይወት ገጠመኙና ሥራው፣ ከእውቅናው ጋር የተያያዙ ገጠመኞቹና የመዝናኛ ምርጫው የተመለከቱ ጥያቄዎቹ አንስተን ከራሱ ያገኘነውን ምላሽ ለእረፍት ጊዜዎ በሚሆን መልኩ አሰናድተን አቅርበነዋል፤ መልካም ቆይታ።

መክሊትን ፍለጋ
ገና ልጅ ሆኖ ትምህርት ቤት ላይ ማታ እቤት ሆኖ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የሚሰማቸውን ዜናዎች ፅፎ ተማሪዎች ፊት በመቆም ማንበብ ያዘወትር ነበር። ለኪነ ጥበብ ቅርብ መሆኑን ተመልክተው በርታ ያሉት ተሰጥኦውን ተመልክተው እባክህ መልካም
ነገር ውስጥህ አለ፤ እሱን አሳድገው ያሉት የቀለም አባት መምህሮቹ ነበሩ። በተለይ እሱን መሳል ልዩ ክህሎት ለነበራቸው ተማሪዎች ድጋፍ የሚያደርጉት አማርኛ መምህሩ ደጋግመው በርታ እያሉ ያበረታቱት የነበረውን አይረሳም። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሚኒ ሚዲያ ላይ ያደርገው የነበረው ኪነ ጥበባዊ የጎላ ተሳትፎ ዛሬ ለሚገኝበት ሙያው መቃረቢያ መንገድ ሆነው።

ተማሪ ሆኖ በተደጋጋሚ የሰማውን ለተማሪዎች ያቀርበው የነበረውን ተለምዷዊ የጋዜጠኝነት ተግባሩ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማሳደግ በማሰብ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ትምህርትን አጥንቷል፣ኋላ ላይ በሥራ መደራረብ ምክንያት አቋረጥው እንጂ በቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ማጥናትም ጀምሮ ነበር።

አድናቂዎች እሱ የተሳተፈበት መድረክን የተገኘበት ሁነትን በጉጉት ይጠብቃሉ። በዝግጅቶች ላይ ኮሜዲያን ደምስ ካለ ሳቅና ደስታ አብሮ እዚያ ቦታ ላይ ይገኛል። በቁም ነገር አዘል ቀልዶቹ አስቆ፤ በአስተማሪ ሽሙጦቹ ብዙ አስተምሮ፣ እንደ ቀልድ የሚታለፉ ጉዳዮች በተለየ መነፅር ቃኝቶ በሳቅ ታጅበው ጎልተው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል። ብዙ ሥራዎችን በተለያየ መንገድ ለሕዝብ አቅርቧል። በተለያዩ መድረኮች በእስታንዳፕ ኮሜዲው ዘርፍ የሰራቸው ቁም ነገር አዘል ቀልዶቹ እና በዘፈን መልክ የሰራቸው ቀልዶችና ጭውውቶች በቪሲዲ በማዘጋጀት ለአድናቂዎች አድርሷል።

የእረፍት ጊዜ መዝናኛዎቹ
እርግጥ ሥራው ማዝናናት ለሰዎች ደስታ መፍጠር ነው። የኮሜዲያኑ ሥራ በራሱ ደስታን የሚፈጥርለት ዋነኛ ምርጫው መሆኑን ይናገራል። የመዝናኛዎች ሁሉ ከፍ ያለው መዝናኛ ለሰዎች ሳቅና ደስታን ፈጥሮ በዚያ ውስጥ የሚገኘው መሆኑን ያስረዳል። እኔም በሥራዬ ለሰዎች ሳቅ ፈጥሬ ያን ሳይ ውስጤ ደስታ ይፈጠራል በማለት አዝናንቶና አስቆ የሚያገኘውን ፍስሀ በልዩ ሁኔታ ይገልፃል።

አብዛኛው የሥራው ፀባይ ለሰዎች በማዝናናት ደስታን ፈጥሮ የነበሩበት ልዩ ልዩ የሕይወት ውጣ ውረድን አስረስቶ ከሕይወት አሰልቺነት እንዲላቀቁ መንገድ መክፈት ሳቅን መመገብ በመሆኑ ይናገራል። ተፈጥሮ ይደንቀዋል በተለይ በሚመለከተው ተፈጥሮዓዊ በሆነ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሁሌም ይደነቃል። ከሥራ ውጪ የሆኑ የዕረፍት ቀናት ተፈጥሮዓዊ ቦታዎች መጎብኘት፣ ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ወገኖች በመጠየቅ በልዩ ልዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ያስደስተዋል።

የዕረፍት ሰዓቱን ካኒቴራ አልያም እጀ ጉርድ ሸሚዞችን ለብሶ ፀጥታ የሰፈነባቸው ቦታዎች ላይ መገኘትን ይመርጣል። ቀርቦለት ከሚመገባቸው ምግቦች ጋር በገበታው ላይ ሁሌም ቢያገኘው የሚፈልገው ስንግ ቃሪያ ደምስ ከሚወዳቸው የምግብ ዓይነቶች ዋነኛው ነው። ኢትዮጵያውያን ቀልድ አዋቂና የዕረፍት ሰዓታቸው በጨዋታና በሳቅ እርስ በርስ በመጨዋወት የሚያሳልፉ በመሆናቸው ቀልዶ ማሳቅ ይከብዳል። ስለዚህም ለማሳቅና ለማዝናናት በቂ ዝግጅት ማድረግና አውዱን መለየት ለኮሜዲያን ወሳኝ ተግባር መሆኑን ያስረዳል።

መልዕክት ለኢትዮጵያውያን
ሁላችንም የምንወዳትና የምንሳሳላት አገር አለችን። ለዚህች ውድ አገር ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ መልካም መዋል፤ ለለውጧም መትጋት ይገባናል። ልዩነታችን ተፈጥሮዓዊ ነው። እንደ አገር አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች ግን ይበረክታልና የገጠሙንን ሀገራዊ ፈተናዎች መሻገር እንችል ዘንድ ትብብርና ህብረታችንን ማጠንከር ይገባናል።

አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012 | ተገኝ ብሩ

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top