Connect with us

የዴክሳሜታሶን (Dexamethasone) ጉዳይ:

የዴክሳሜታሶን (Dexamethasone) ጉዳይ:
Photo: Social media

ጤና

የዴክሳሜታሶን (Dexamethasone) ጉዳይ:

የዴክሳሜታሶን (Dexamethasone) ጉዳይ:
‘(ዶ/ር ቴዎድሮስ ፀጋዬ ፤ የውስጥ ደዌ ሐኪም)

–ምንነት–
በዘመናዊ ህክምና ታሪክ ውስጥ ፋና ወጊ (Ground breaking) ከሚባሉ ግኝቶች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደበው ዴክሳሚታዞን (dexamethasone) ንን በአባልነት ያካተተው ኮርቲኮስቴሮይድ (Corticosteroids) ተብለው የሚጠሩ የመድሃኒቶች ስብስብ ወይም ቤተሰብ ጥቅም ላይ መዋል ነው። ይህ ስብስብ ሰፋ ሲል steroids ጠበብ ሲል ደግሞ glucocorticoids የሚል ስያሜ አለው። የመጀመርያው ህክምና ላይ የዋለው በላቦራቶሪ የተመረተ (synthetic) corticosteriod ኮርቲሶን (cortisone) ሲባል ተመርቶ ገበያ ላይ የዋለውም ከ60 አመታት በፊት ነበር።

በሰውነታችን ውስጥ የሁለቱም ኩላሊቶቻችን አናት ላይ ተፈናጥጠው የሚገኙ የአድሬናል እጢዎች (Adrenal glands) የሚባሉ ሆርሞን አመንጪዎች ይገኛሉ። እነዚህ እጢዎች ከሚያመርቷቸው ሆሮሞኖች መካከል Dexamethasoneንን ጨምሮ የሁሉም glucocorticoids አባት የሆነው ኮርቲሶል (cortisol) የተባለው ሆሮሞን ይገኝበታል። ዛሬ እንደ አዲስ ተአምራዊ ግኝት የአለም ዜና አውታሮች የተቀባበሉት dexamethasone በድንገት ኮሮናን ለማከም የተፈጠረ መድሃኒት ሳይሆን ለብዙ ሚሊዮን አመታት አብሮን የኖረ በእኛው ሰውነት የሚመረት ሆሮሞን ላይ መጠነኛ ማስተካከያ (modification) በማድረግ የተዘጋጀ መድሃኒት ነው።

–ታሪክ–
የመጀመርያው የcortisone ታካሚ Rheumatoid arthritis የሚባል የመገጣጠሚያ ችግር ተጠቂ ነበር። ይህ ታካሚ በወቅቱ በህክምናው ያሳየው ለውጥ እና መሻሻል ፈጣንና አስደናቂ ነበር። በዚህም የተነሳ በህክምናው ማህበረሰብ ዘንድ በጊዜው የተፈጠረው ጉጉት እና ተነሳሽነት ለሁሉም አይነት በሽታዎች መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል እስከከመተንበይ እና ሙከራ እስከማድረግ ዘለቀ። በቀጣይ አመታትም ለበርካታ የጤና ችግሮች አይነተኛ መፍትሔ ሊሆን ይችላል በሚል በሰፊው ጥቅም ላይ ዋለ። የአለም የዜና አውታሮችም በጊዜው “እውነተኛው ምትሀተኛው ፈዋሽ” በማለት አድናቆታቸውን ከጫፍ እስከ ጫፍ አስተጋቡ።

–የጎንዮሽ ጉዳት–
ጉድ እና ጅራት ወደኋላ እንዲሉ corticosteroids ላይ የተጣለው ተስፋ እና ግርግር ከጥቂት አመታት መዝለል አልቻለም። በቀጣዮቹ አመታት የመድሃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት እና መዘዝ በብዛት መስተዋል ጀመረ። ይሄው መድሃኒት ጥቅም ላይ መዋል በጀመረ በ10 አመት ጊዜ ውስጥ ተስፋው በስጋት ተተካ። ለሁሉም የሰው ልጅ ደዌዎች ፈውስ ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መድሃኒት ሁሉም የሰውነት ክፍሎች እና ስርዓቶች ላይ በሚያስብል ደረጃ መርገምቱን ያወርደው ጀመረ። ከመርገምቶቹ በጥቂቱ የስኳር በሽታ ፣ ደም ግፊት ፣ የዐይን መታወር ድረስ ሊያደርሱ የሚችሉ Glaucoma እና cataract ፣ ከፍተኛ ውፍረት እና ተያያዥ ጉዳቶቹ ፣ የበሽታ የመከላከል አቅም መቀነስ ፣ የስነ ልቦና ችግር (psychosis) ፣ የአጥንት መሳሳት ፣ ወዘተ ይገኙበታል። በተጨማሪም በጎንዮሽ ጉዳት ምክንያት ወይም በሌላ መድሀኒቱ በድንገት በሚቆምበት ጊዜ በመጀመርያ መሻሻል ያሳዩ ስሜቶች በብዙ እጥፍ ተባብሰው መታየት ጀመሩ። ይባስ ብሎም እነኚህን መድሀኒቶች የጤነኛውን የAdrenal gland ተግባር በማዛባታቸው ምክንያት መድሃኒቱ በድንገት ሲቆም እነዚሁ እጢዎች የሆርሞን ማመንጨት ስራቸውን በአግባቡ ማካሄድ ባለመቻላቸው ብዙዎችን ለህልፈት የዳርገ ጦስ (complication) እስከማስከተል ደረሰ።

በዓመታት ውስጥ በተገኘው የተሻለ ግንዛቤም በዚህ ዘመን dexamethasone ንን ጨምሮ ሌሎች Glucocorticoids ለበርካታ የበሽታ ዓይነቶች ህክምና ጥቅም ላይ በመዋል ይገኛሉ። አደጋ እና ጥቅማቸውን ባመዛዘነ መልኩ። ከነዚህም ውስጥ የአስም በሽታን ጨምሮ በርከት ያሉ የዓየር ቧንቧ እና የሳንባ በሽታዎች ይገኙበታል።

–ኮሮና እና ዴክሳሚታሶን–
ኮሮና እንደሌሎች በርካታ ተላላፊ በሽታ በሰውነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ሁለት እጥፍ (two fold) ነው ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ። ቀጥተኛው በቫይረሱ መራባት ሂደት ውስጥ የሚከሰተው ጉዳት ሲሆን ተዘዋዋሪው ደግሞ ሰውነታችን ራሱን ከበሽታ/ወራሪ ለመከላከል ብሎም ለማጥቃት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚፈጠር የጎንዮሽ ጉዳት ነው። ግርምት ሊያጭር በሚችል ሁኔታ አብዛኛው ጉዳት የሚደርሰው ከቀጥተኛው ይልቅ በሁለተኛው ተዘዋዋሪ መንገድ መሆኑ ነው። እጄን በእጄ እንዲሉ።

ከተከሰተ የመንፈቅ ዕድሜ ያስቆጠረው የዘመናችን ወረርሽኝ- ኮሮና ሚሊዮኖችን አዳርሶ መቶ ሺዎችን ወደመቃብር አውርዷል። በዚህ የጭንቅ ጊዜ ውስጥ ይሄ ነው የሚባል ፈዋሽ መድሃኒትም ሆነ መከላከያ ክትባት አልተገኘለትም። በአንዳንዶቹ ሲገለፅ እንደምንሰማውም Dexamethasone የኮሮና ፈዋሽ መድሃኒት አይደለም። በፅኑ የታመሙ የኮሮና ህሙማንን ሞት በመቀነስ ረገድ ግን ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ያልወጣው የጥናት ውጤት ማመላከት ችሏል።

—ማሳሰብያ—
ዴክሳሚታሶን በጥናት ላይ የዋለው የኮሮናን ቫይረስ ለማጥፋት እና በቫይረሱ ላይ ቀጥተኛ ካለው ተጽዕኖ ሳይሆን የመድሀኒቱን የፀረ-ብግነት ባህሪ ታሳቢ በማድረግ በኮቪደ-19 ላይ ያለውን አስተዋጽኦ ለማጥናት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ ይህ መድሀኒት ኦክስጅን በሚፈልጉ ታካሚዎች ላይ ይሞቱ ከነበሩት አምስት ሰዎች አንድ ሰው እንዲሁም በመተንፈሻ አካል መሳርያ ላይ ሆነው ከሚሞቱት ሶስት ሰዎች የአንድ ሰው ሞት መቀነሱ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል፡፡ ሆኖም ግን ዴክሳሜታዞን የኮቪድ-19 መድኃኒት ያለሆነ፣ ለመከላከል የማይጠቅም እና የራሱ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ከግንዛቤ ሕብረተሰቡ ያለሀኪም ትዕዛዝ መድኃኒቱን እንዳይወስድ እንዲሁም የፋርማሲ እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎችም የዴክሳሜታዞን መድኃኒትን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ለደንበኞቻቸው መሸጥ እንደሌለባቸው በአጽንኦት እናሳስባለን፡፡

(የኢት የኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት)

#COVID19Ethiopia

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top