Connect with us

ውድቀቶቹ የስኬቱ መሠረት የሆኑለት ሆንዳ

ውድቀቶቹ የስኬቱ መሠረት የሆኑለት ሆንዳ
Photo: Social Media

ሳይንስና ቴክኖሎጂ

ውድቀቶቹ የስኬቱ መሠረት የሆኑለት ሆንዳ

ውድቀቶቹ የስኬቱ መሠረት የሆኑለት ሆንዳ
አምኃየስ ታደሰ በድሬቲዩብ
amhayest@gmail.com

ለብዙዎቻችን ሆንዳ የጃፓንን የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ በሁለተኛነት የሚመራ ተሽከርካሪ ወይም የአምራቹ ኩባንያ መጠሪያ ነው፡፡ ዛሬ 22ዐ ሺ ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው እና በድምሩ ከ4ዐዐ ሚሊዮን በላይ ሞተር ብስክሌቶችን አምርቶ በማቅረብ በዓለማችን ተወዳዳሪ የሌለው ብሎም አመታዊ ገቢው እስከ 145 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ የቻለው የሆንዳ ኮርፖሬሽን አነሳስ እና ጉዞ ግን እንደምናስበው የስኬት ብቻ አይደለም፡፡

ጊዜው በአውሮፓውያኑ ቀመር በ1938 ሲሆን የተሽከርካሪ የፒስተን ቀለበት አምርቶ ለቶዮታ ኮርፖሬሽን የማቅረብ ውጥኑን ዕውን ለማድረግ የቆረጠው ወጣት አነስተኛ ወርክሾኘ የከፈተው መደበኛ ትምህርቱን እንኳ ሳያጠናቅቅ ነበር፡፡ ሰውነቱ በግራሶ እንደተጨማለቀ አዳሩን በስራ ተጠምዶ በሚውልበት ጋራዥ ውስጥ ለማድረግ የተገደደው ሶይቺሮ ሆንዳ ሁሌም ጥረቱ የማታ ማታ ውጤት እንደሚያስገኝለት እርግጠኛ ይኹን እንጂ መንገዱ ግን እንደገመተው አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡

ለአብነትም የገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ የባለቤቱን ጌጣ-ጌጦች ሳይቀር በዕዳ አስይዞ የፈበረካቸውን እና ለዓመታት የደከመባቸውን የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች እንደሚገዛው ቅንጣት ታህል ወዳልጠረጠረው ቶዮታ ኮርፖሬሽን ሲቀርብ ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሆነበት፡፡ የፒስተን ቀለበቶቹ ተፈላጊውን የጥራት ደረጃ ባለማሟላታቸው ተቀባይነት እንዳላገኙ የተረዳው ሆንዳ ተስፋ ሳይቆርጥ ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ ሲገደድ መምህራኑና ተማሪዎቹ የሙከራ ዲዛይኑ ምን ያህል እርባና ቢስ እንደሆነ በመግለጽ ሲሳለቁበት አስተውሏል፡፡

ይሁንና ሙሉ ትኩረቱን ዓላማውን በማሳካት ላይ ብቻ በማድረጉ ከሁለት ዓመታት የተማሪነት ቆይታው በኋላ ብዙ ደክሞ ባሻሻለው ምርቱ መነሻነት የቶዮታ ኮርፖሬሽን ሕልሙ ዕውን መሆኑን የሚያረጋግጥ የአቅርቦት ውለታ ሊፈርምለት ይብቃ እንጂ የሆንዳን ደስታ የሚሰርቅ ሌላ ደንቃራ ግን መከተሉ አልቀረም፡፡ የጃፓን መንግስት “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” ባለበት ወቅት የፒስተን ቀለበት ፋብሪካውን ለመገንባት የሚያስፈልጉትን የአርማታ ግብአቶች ማግኘት እንደማይችል ሲገለጽለት ሆንዳ አጋጣሚው የራዕዩ መጨንገፍ አመላካች እንደሆነ አምኖ አልተቀበለም፡፡

ይልቁንም ባልደረቦቹን በማስተባበር አማራጭ የኮንስትራክሽን ቁሳቁሶች ተጠቅሞ የገነባው የፒስተን ፋብሪካ ሁለት ጊዜ በቦምብ የወደመ ሲሆን እርሱ ግን እጅ ሊሰጥ ቀርቶ “የኘሬዝዳንት ትሩማን” ስጦታ ያላቸውን የአሜሪካ ወታደሮች ከአውሮኘላን ላይ የሚጥሏቸውን የብረት ጀሪካኖች ማሰባሰብን የተያያዘው ለምርቱ የሚያስፈልጉ ነገር ግን በጃፓን የማይገኙ ጥሬ እቃዎች መሆናቸውን በመገንዘቡ ነበር፡፡

ሆንዳ በርካታ መሰናክሎች በማለፍ ግንባታውን ያጠናቀቀው ፋብሪካ ስራ እንደጀመረ በርዕደ-መሬት ክፉኛ ሲመታ የፒስተን ፍብረካ ንግዱን ከነድርጅቱ ለቶዮታ ኮርፖሬሽን ለመሸጥ ተገደደ፡፡ ምን መሆን እንደሚፈልግ አስቀድሞ አውቆ እና የሚገጥመውን ውጣ ውረድ ተቋቁሞ ለውጥኑ መሣካት እስከመጨረሻው ከመጋደል ውጪ አማራጭ እንደሌለው በጽኑ ያመነው ሆንዳ የገጠሙት መሰናክሎች ይልቁንም ፊት ለፊቱ የተጋረጠበትን ሌላ ፈተና ለማለፍ ብቻ ሳይሆን ስኬታማ እንዲሆን አዘጋጅተውታል፡፡

ድህረ-ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጃፓን በገጠማት የነዳጅ እጥረት የተነሳ ሆንዳ መኪናውን እንኳ አንቀሳቅሶ ለቤተሰቡ ቀለብ መግዛት የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ በቀቢፀ ተስፋ ብስክሌቱ ላይ ትንሽ ሞተር በመግጠም ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እንዲያደርግ ምክንያት ሆነው፡፡ አጋጣሚው የመጀመሪያውን የሞተር ብስክሌት መፍጠር ያስቻለው ሆንዳ ዘግይቶ የተገነዘበው ጓደኞቹና ጐረቤቶቹም ተመሳሳይ ተሽከርካሪ እንዲሰራላቸው መፈለጋቸውን ነበር፡፡

ሆንዳ የግኝቱን ተፈላጊነት ተጠቅሞ ምርቱን በስፋት ለማቅረብ ይቁረጥ እንጂ ሞተሩን ለመፈብረክም ሆነ ብስክሌት ላይ ለመግጠም የሚያስፈልገውን ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችል በቂ ገንዘብ ግን አልነበረውም፡፡ የሚገጥመውን ደንቃራ ሁሉ መቋቋም እንደሚችል ጥርጥር ያልነበረው ሆንዳ ለገንዘብ ችግሩ መፍትሄ ይሆነው ዘንድ በጃፓን ለሚገኙ 18 ሺ የብስክሌት ነጋዴዎች በተናጠል ደብዳቤ በመፃፍ እርጥባን መጠየቅ ነበረበት፡፡

በደብዳቤው ፈጠራውን በማገዝ እንዴት አገሪቱን መልሶ በመገንባት ጭምር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በመወትወቱ 3 ሺ ከሚሆኑ ባለ-ሃብቶች ለስራው ማስጀመሪያ የሚያስፈልገውን መዋዕለ-ንዋይ ለማሰባሰብ ከመቻሉም በላይ በተጓዳኝም ግዙፍ የነበረውን የሞተር ብስክሌት ዲዛይን በማሻሻል ለገበያ ያበቃውን የአዲሱን ሞዴል ምርት በማስመረቅ ሆንዳ ከጃፓን ንጉስ ሽልማት ለመቀበል ባደረሰው የስኬት ማማ ላይ ተቀመጠ፡፡

በተጨማሪም ወደ አውሮፓና አሜሪካ የላካቸው የሞተር ብስክሌቶች ከፍተኛ ተወዳጅነት በማግኘታቸው ከ197ዐዎቹ አንስቶ በተሽከርካሪዎች አምራችነት በማሰቀጠልም አውሮኘላኖችን፣ ጄነሬተሮችን፣ የውሃ ፖምፖችን፣ የተለያዩ ሞተሮችን፣ ወዘተ በመፈብረክ ለገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡

ሶይቺሮ ሆንዳ ታድያ ከገዛ ተሞክሮው ተነስቶ “ስኬት 99 በመቶ ያህል ውድቀት” እንደሆነ ቢናገር አይፈረድበትም፡፡ በርግጥም የሆንዳ ብቻ ሳይሆን የበርካቶች ስመ-ጥር ግለሰቦች ተሞክሮዎች የሚያስረግጡት ምኞት ብቻ ሳይሆን ፍላጐትን ማሳካት የሚጠይቀውን ሁሉ ተግቶ መፈጸም እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አካሄድን ማሰተካከል የስኬት ቅድመ-ሁኔታዎች መሆናቸውን ናቸው፡፡ እኛስ ከሆንዳ ውድቀት እና ፅናት ምን ያህሉን የመካፈል ዝግጁነት ይኖረን ይኾን?

Click to comment

More in ሳይንስና ቴክኖሎጂ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top