Connect with us

ከገበያ ዋጋ በታች ምርት አከፋፍለዋል የተባሉ ውኃ አምራቾች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

ከገበያ ዋጋ በታች ምርት አከፋፍለዋል የተባሉ የታሸገ ውኃ አምራቾች በማኅበራቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

ኢኮኖሚ

ከገበያ ዋጋ በታች ምርት አከፋፍለዋል የተባሉ ውኃ አምራቾች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

ከገበያ ዋጋ በታች ምርት አከፋፍለዋል የተባሉ የታሸገ ውኃ አምራቾች በማኅበራቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

የኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ፣ ለስላሳ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ሦስት የታሸገ ውኃ አምራቾችን ከተቀመጠው የዋጋ ማዕቀፍ በታች ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ በመውቀስ አስጠነቀቀ፡፡

ማኅበሩ ለውኃ አምራቾቹ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ማኅበሩ ካስቀመጠው የዋጋ ማዕቀፍ በታች መሸጣቸውን በመመልከትና ከሌሎች አምራቾች የቀረቡለትን ጥያቄዎች በመንተራስ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ማኅበሩ አጣርቶና አረጋገጦ በደረሰበት ውጤት መሠረት ከተቀመጠው የመሸጫ ዋጋ በታች ሲሸጡ የተገኙ በመሆናቸውና እንዲያስተካክሉ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሊያስተካክሉ ባለመቻላቸው ነው ብሏል፡፡

የአምራቾቹ የጋራ ማኅበር ባሠራጨው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መሠረት፣ ውኃ አምራቾቹ የተስማሙበትና በየወሩ ለአምራቾቹ በሚሰጠው የዋጋ ማዕቀፍ መሠረት ምርቶቻቸውን አላከፋፈሉም፡፡ ይህንን እንዲያስተካክሉም ሦስቱ አምራቾች ተጠይቀው ነበር፡፡ አምራቾቹ የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ የአንድ ቀን ገደብ እንዳስቀመጠና ስለጉዳዩም ከማኅበሩ ጽሕፈት ቤትና ከቦርድ አመራሮች ጋር በስልክ ውይይት መደረጉን ለአምራቾቹ በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የዋጋ ማስተካከያ ስለማድረጋቸው አምራቾቹ ሊያስታወቁ ባለመቻላቸው፣ ማኅበሩ ግንቦት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በድጋሚ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው አድርጓል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት በተለይ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ፋብሪካዎች ምርታቸውን ለመሸጥ ገበያ ባጡበትና ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል አዳጋች በሆነበት ወቅት ድርጅታችሁ ገበያውን ጠቅልሎ ለመያዝ እያደረገ ያለው ጥረት በፍፁም ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት ማኅበሩ ለድርጅቶቹ በደብዳቤ ድርጊታቸው አግባብ እንዳልሆነ ገልጾላቸዋል፡፡

‹‹በነፃ ገበያ ሰበብ ምንም ዓይነት አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር ገበያውን ሆን ብለው በበላይነት በመያዝ ተጠቃሚው ጋር የማይደርስ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ከአማካይ የማምረቻ ዋጋ በታች እየሸጡ የአብዛኛዎቹን አምራቾች ገበያ እንዲቆጣጠሩ ከማስቻሉም በላይ ሌሎች ፋብሪካዎች ሥራ እንዲያቆሙ ምክንያት እየሆኑ ነው፤›› በማለት ማኅበሩ ኮንኗቸዋል፡፡ ውድድርን በማኮሰስና በማጥፋት ፋብሪካዎች እንዲዘጉ ያደርጋል በማለት ማኅበሩ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ከሕግ ባሻገር በሞራልም ተቀባይነት የሌለውና ባለቤቶችን በወንጀል ጭምር የሚያስጠይቅ እንደሆነ የሚገልጸው የማኅበሩ ደብዳቤ፣ የሥነ ምግባር ደንብ፣ የንግድ ውድድርና የሸማቾች መብት አዋጅ፣ የማኅበሩ አባል ለሆኑና ላልሆኑ አምራቾች በግልጽ የመቀመጠ መመርያ ጠቅሷል፡፡

እንደ ማኅበሩ አቋም የአምራቾቹ ድርጊት የተወዳዳሪን ወጪ ለማሳደግ ወይም ግብዓቶችን ወይም የሥርጭት መስመሮችን ቀድሞ በመቆጣጠር ተወዳዳሪዎች ላይ ያነጣጠረ ጎጂ አካሄድ ሆኖ በመገኘቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የታሸገ ውኃ አምራቾቹ ፍትሐዊ ካልሆነ የመሸጫ ዋጋ እንዲቆጠቡና ማኅበሩ በየወሩ በሚልከው የዋጋ ደረጃ ምርታቸውን እንዲሸጡ አሳስቧል፡፡ በአጭሩ ከገበያ ዋጋ በታች መሸጣችሁን አቁሙ እያለ ነው፡፡

ድርጅቶቹ ከዋጋ በታች ስለመሸጣቸውና ይህንንም በአንድ ቀን ውስጥ አስተካክለው ለማኅበሩ እንዲያሳውቁ በድጋሚ ጠይቋል፡፡ አምራቾቹ ይህንን ካላደረጉ ግን ማኅበሩ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ ለሌሎች አምራቾችና ለኅብረተሰቡ በማሳወቅ ዕርምጃ እንደሚወስድና አግባብ ያለው የመንግሥት አካል ውሳኔ እንዲሰጥበት እንደሚያደርግ አስጠንቅቋል፡፡

ስለዚሁ ጉዳይ ሪፖርተር ያገኛቸው ተጨማሪ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ማኅበሩ በአባላቱ መካከል የሚደረግ ጤናማ ውድድር እንዲስፋፋ፣ ሸማቹም ያልተገባ የመሸጫ ዋጋ እንዳይጠየቅ ለመቆጣጠር በየወሩ የዋጋ ማዕቀፍ መቆጣጠሪያ በማውጣት ግብይቱ በገበያ ዋጋ መካከል ጥቂት ከፍና ዝቅ በሚል አማካይ እንዲንቀሳቀስ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል፡፡

በዚሁ መሠረት ሁሉም የውኃ አምራቾች ስምምነት አድርገው ሲሠሩ መቆየታቸው ታውቋል፡፡ ማኅበራዊና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ ወርኃዊ የዋጋ ምጣኔውን የሚያወጣው ለእያንዳንዱ የታሸገ ውኃ በየመጠናቸው ከዚህ በታች መሸጥ አትችልምና ከዚያ በላይ ደግሞ መሸጥ አትችልም በማለት ጭምር ነው፡፡

እንደ ምሳሌ የሰኔ ወር የዋጋ ምጣኔ ተደርጎ የተጠናውና ለውኃ አምራቾች የተላከው ተመን አንድ ባለ ግማሽ ሌትር እሽግ ውኃን ማከፋፈል የሚችሉት ከ54 ብር በታች እንዲሁም ከ58 ብር በላይ መሸጥ የማይችሉ መሆኑን ነው፡፡

በተመሳሳይ ውኃ አምራቾች አንድ ሊትር ደርዘን ውኃ (ስድስት የፕላስቲክ ጠርሙስ የሚይዝ) በአማካይ ዋጋው ከ40 ብር በታች መሸጥ እንደማይችሉና ከ42 ብር በላይ ምርቱን ማከፋፈል እንደማይቻል ይገልጻል፡፡ ለባለ ሁለት ሌትር ደርዘን ውኃም በተመሳሳይ ከ54 እስከ 58 ብር ያለው ዋጋ የወጣ ሲሆን፣ ከዚህ በላይ ሆነ በታች መሸጥ የማይችሉ መሆኑን የሰኔ ወር የዋጋ ምጣኔ ያመለክታል፡፡ አሁን ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የታሸገ ውኃ አምራቾች ግን ከዚህ ምጣኔ በታች መሸጣቸው በመታወቁ ማስጠንቀቂያው ደርሷቸዋል ተብሏል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በመንግሥት የሚታወቅ ስለመሆኑ የሚያመለክተው መረጃ፣ የማኅበሩ አባላትም ተስማምተው የሚፈጽሙት ነው፡፡

ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ሌሎች ቢዝነሶች የታሸገ ውኃ ገበያ በመቀዛቀዙ አንዳንዶች ከምጣኔው በታች ምርታቸውን ማከፋፈላቸው ደግሞ አጠቃላይ የውኃ ገበያውን የበለጠ አደጋ ውስጥ የሚከት በመሆኑ በአባላት ጥያቄ መሠረት ማኅበሩ ዕርምጃ ለመውሰድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት የውኃ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ገበያው ለመመታቱ ደግሞ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያለው ገበያ ከመመታቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከወቅታዊው ጉዳይ አንፃር በከፍተኛ ደረጃ ውኃ የሚቀርብባቸው ስብሰባዎችና ተያያዥ ዝግጅቶች ከመታገዳቸው ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ገበያው ቀዝቅዟል፡፡

በዚህ ላይ የዋጋ ምጣኔ በማውጣት ሲሠራበት የቆየው አሠራር እንዲህ ባለ ሁኔታ የሚበረዝ ከሆነ ደግሞ በአግባቡ የሚሠሩ የውኃ አምራቾች ገበያ ተበላሽቶ ህልውናቸውን እንዳይፈታተን ጭምር በመሠጋቱ እንደሆነም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ105 በላይ የታሸገ ውኃ አምራቾች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡(ሪፖርተር)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top