Connect with us

መፍራትስ ከፖሊስ ዱላ እንጂ ከቫይረስ የማያስጥለውን ማስክ ነው

መፍራትስ ከፖሊስ ዱላ እንጂ ከቫይረስ የማያስጥለውን ማስክ ነው
A surgical mask, left, and an N95 mask, right.

ጤና

መፍራትስ ከፖሊስ ዱላ እንጂ ከቫይረስ የማያስጥለውን ማስክ ነው

መፍራትስ ከፖሊስ ዱላ እንጂ ከቫይረስ የማያስጥለውን ማስክ ነው
(አምኃየስ ታደሰ amhyest@gmail.com)

በርካታ የዓለማችን መንግስታት ከወረርሽኝ ለፈረጁት የኮቪድ-19 በሽታ እየሰጡት ያለው ምላሽ የችግሩን ዓይነተኛ መንስኤ ያላገናዘበ በመሆኑ በደመ-ነፍስ የሚወሰዱት የዘመቻ እርምጃዎችም የጨዋታውን ሕግጋት ተከትሎ ኳሷን አስተካክሎ ከመምታት ይልቅ የጐሉን ቋሚ በማንቀሳቀስ ግብ ለማስቆጠር ከሚደረግ ሙከራ ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው፡፡

ለአብነትም መሪቻቻችን በቅርቡ አስገዳጅ ያደረጉት ማስክ ያለውን ጀርም የመመከት ብቃት እንዴት አስቀድመው እንዳልተገነዘቡት የማስረዳት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ብዬም ሆነ በርግጥም ጭምብል እንደታሰበው የኤስሲ-2 ቫይረስን መዛመት እንደሚያስቆም ከታመነበት ቢያንስ የአካላዊ መራራቁ ውሣኔ አሁንም ለምን እንዲፀና እንደተፈለገ የሚሰጡን አሳማኝ ምክንያት ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡

በበኩሌ ለበርካታ ዓመታት ከሕክምና እና ጤና ነክ መረጃዎች ጋር ከነበረኝ ቅርበት በመነሳት ማስክ በጤናማ ሰዎች ሲደረግ የኦክስጂን አቅርቦትን በመገደብ ሰውነት መደበኛ ተግባሩን እንዳያከናወን እንደሚያደርግ (hypoxia) የሚገልጸውን በሕክምና ዶክተር የተዘጋጀ ጽሁፍ ለሚመለከታቸው የጤና አጠባበቅ እና የፖለቲካ ሹመኞች በትዊተር አማካይነት ለማድረስ መሞከሬን ተከትሎ በአንድ የውጪ ዜጋ የተሰጠኝ ምላሽ ዘገባው የአቻ ምዘና ተደርጐበት በሕክምና ምርምር ጆርናል የታተመ እንዳልሆነ የሚገልጽ ስለነበር በአንፃሩ ማስክ የኮቪድ-19 ቫይረስን ለመከላከል ስላለው ጠቀሜታ የሚያስረግጥ ሳይንሳዊ ማስረጃ መፈለግ ነበረብኝ፡፡

ይኹንና ከጠበቅኹት በተቃራኒው በርግጥም ጤናማ ሰዎች ማስክ መጠቀማቸው በተለይ በቫይረስ ከመጠቃት እንደሚያስጥላቸው የሚገልጽ አንድም ሪፖርት ማግኘት አለመቻሌ ሲገርመኝ በርካታ ጥናቶች የመተንፈሻ አካልን ለረጅም ሰዓታት ሸፍኖ መቆየት የከፋ ጉዳት እንዳለው በማያሻማ አኳኋን መግለፃቸው ስጋቴን ከማስክ ውጪ እንዳይንቀሳቀስ ለተገደደው ዜጋ ለማድረስ ያስገደደኝ ሲሆን በቅርቡ ይፋ ከሆነው ሳይንሳዊ ጥናት የምጀምረው ጽሁፌ የሚዳስሰው ከምርምር ውጤቶቹ ጥቂቶቹን ብቻ መሆኑን በመጠቆም ነው፡፡

አናልስ ኦፍ ኢንተርናል ሜድስን የተባለው የምርምር ጆርናል የኮቪድ-19 ሕሙማን በሚያስሉበት ወቅት የሚያደርጓቸው ማንኛቸውም ማስኮች ቫይረሱን በአግባቡ ገድበው ማስቀረት እንደማይቻላቸው “neither surgical nor cotton masks effectively filtered” ያስነበበው ባሳለፍነው መጋቢት 28 ቀን ይፋ ባደረገው እትሙ ነበር፡፡ ሚያዝያ 10 ቀን 2008 ዓ. ም. ለንባብ የበቃው የብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል ደግሞ የጨርቅ ማስክ መጠቀም ለእንፍሉዌንዛ መሰል በሽታ የማጋለጥ እድሉ ማስክ ጨርሶ ካለማድረግ ጋር ሲነፃፀር ከሶስት እጥፍ በላይ “over three times, the risk of contracting” እንደሆነ አስረግጧል፡፡

የኢፒደሚክስ ጆርናል ቅጽ 20 በመስከረም ወር 2010 ዓ. ም. በማስክ አጠቃቀም ዙርያ የተካሄዱ ምርምሮችን ካጠቃለለ ትንታኔ (meta-analysis) በመነሳት የደመደመው ጭምብል ማድረግ ቫይረስን ከመከላከል አንፃር የረባ ፋይዳ “non-significant protective effect” እንደሌለው ሲሆን ይኸው አቋም የጆርናል ኦፍ ኤክስፖዝር ሳይንስ ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ኢፒዲሞሎጂ ቅጽ 27 በተመሳሳይ አመት ከደረሰበት 97 በመቶ የሚሆኑት የቫይረስ ክፋዮች (particles) የጨርቅ ማስክን ሰርገው እንደሚገቡ እና የህክምና ማስኮች ደግሞ 44 በመቶ የሚሆኑት ቫይረሶች መገደብ አለመቻላቸውን ባረጋገጠ ሌላ የምርምር ውጤት የተደገፈ ነው፡፡

ለህክምና አገልግሎት የዋሉት ማስኮች በጥቅሉ በዓይን የማይታየው ቀዳዳቸው በአማካይ ከ2.5 ማይክሮሜትር ያነሰ መጠን ያለውን የበሽታ አምጪ ወደ አፍና አፍንጫ ከመግባት ማስቀረት እንደማይቻላቸው ኢፒዲሞሎጂስቶቹ ማግለፃቸው የኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜድስን የካቲት 10 ቀን 2012 ዓ. ም. የኮኖናቫይረስ ክፋዮች መጠን ከ0.06 ማይክሮሜትር እስከ 0.14 ማይክሮሜትር መሆኑን ከማሳወቁ ጋር ተዳምሮ አስገዳጅ የሆነውን ማስክ ተጠቅሞ የኮሮናቫይረስን በመከላከል የሚገኘው ጥቅም የእግር ኳስ ጐል መረብን ለወባ መከላከያ ዛንዚራ ከማዋል ጋር የሚነፃፀር ገፅታ ያለው ነው፡፡

ችግሩ ሕግን ለማክበር ወይም ለማንኛውም ተብሎ ታፍኖ የመቆየቱ አስፈላጊነት ከጥያቄ ውስጥ የሚገባው በሳይንሳዊ ዘገባዎቹ ከተረጋገጠው ማስክ የሚያስከትለው ጉዳት ያስገኛል ከሚባለው ጥቅም በእጅጉ የገዘፈ የመሆኑ ሃቅ ነው፡፡ ጭምብል በተከታታይ ለሰባት ሰዓታት ማድረግ በትንፋሽ የሚወጣው ካርቦንዳይአክሳይድ (ሲኦ2) ወደ ሰውነት እንዲመለስ በማድረግ የኦክስጂን አቅርቦትን እንደሚያውክ እና የበሽታ መከላከያ ስርአትን እንደሚያናጋ ኢርጐኖሚክስ ጆርናል በ2007 ዓ. ም. ባወጣው ቅጽ 56(5) አስነብቧል፡፡

የአሜሪካው የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ) እና የአለም የጤና ድርጅት ባለፉት የየካቲት እና የሚያዝያ ወራት በሰጧቸው መግለጫዎች ጭምብል የሚጠቅመው የኮሮና ቫይረስ ምልክቶች ለታዩባቸው ሕሙማን እንጂ ጤናማ ሰዎች በኮቪድ-19 በሽታ የተጠረጠረጠሩትን ሲንከባከቡ ካልሆነ በስተቀር ፈጽሞ ማስክ እንዲያደርጉ እንደማይመክሩ አስታውቀዋል፡፡

ማስክ ከሰውነት መወገድ የሚገባቸውን ጀርሞች ወደ አንጐል እንዲያቀኑ ከማድረግ በተጨማሪ የሚያስከትለው የኦክስጂን እጥረት ከራስ ምታት፣ እንቅልፍ ማጣት እና የድካም ስሜት አንስቶ እየከፋ ሲሂድ ለመተንፈስ መቸገር ብሎም ለሕልፈተ ህይወት ሊዳርግ የሚችል ነው፡፡ ለአብነትም ኒው ዮርክ ፖስት የሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ. ም. የዘገበው ሁለት ቻይናውያን ወጣቶች ማስክ ተጠቅመው ስፖርት በሰሩበት ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በተከታታይ መሞታቸውን ዘግቧል፡፡

እግረ መንገዴን የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒው ሳውዝ ዌልስ ተመራማሪዎች ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ. ም. ሃኪሞች ማስክ ሲያዘወትሩ ለመተንፈሻ አካል በሽታ እና ለቫይረስ ጥቃት ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚሆኑ መዘገባቸውን የማስታውሰው የጭምብል ተጓዳኝ ጉዳቶች ለአገራችን የጤና ባለሙያዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዘመቻ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በተደረገው የክፍያ ማሻሻያ እንኳን ሊካካስ የማይችል መሆኑን በርካታ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡ በማሳሰብ ነው፡፡

በመጨረሻም የኮቪድ-19 ቫይረስ ከሕሙማን በፈሳሽ መልክ በሚወጡ ብናኞች (droplets) ካልሆነ በስተቀር እንደ የሳንባ ነቀርሳ፣ የኢቦላ እና የፈንጣጣ ጀርሞች በአየር ላይ ቆይቶ ወደ ጤናማ ግለሰብ እንደማይዛመት ስለሚታወቅ ጭምብል ማድረግ አደገኛ እና ፊታችንን የቫይረስ መሰብሰቢያ ቋት በማድረግ በሽታን ለማስፋፋት በተጓዳኝም ባዮሎጂያዊ ዝገት (oxidative stress) እንደሚያስከትል ታውቆ አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር በቅርቡ የፀደቀው የማስክ አጠቃቀም ድንጋጌ ሊሰረዝ እንደሚገባው ልጠቁም እወዳለሁ፡፡

ይኹንና መነሻውን ከሳይንሳዊ ጭብጦች ይልቅ አሁንም ባልተጨበጠ መላምት ዙርያ አድርጐ በሚጓዘው የፀረ-ኮቪድ ወረርሽኝ ዘመቻ ስም የሚወሰዱት ፖለቲካዊ እርምጃዎች የተጠበቀውን ውጤት አለማስገኘታቸው እየታወቀ መሪዎቻችን አሁንም እየተቀባበሉ የምንላችሁን ብቻ ፈፅሙ ማለታቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ከአምባ ገነንነት ወይም ከንቀት የመነጨውን ትእዛዛቸውንና የፖሊሶችን ዱላ ፈርተን በጭምብል መታፈን ስለሚያስከትለው የማይቀለበስ ጉዳት እያወቅን ዓይናችን እያየ በየእለቱ ለሰዓታት አፍና አፍንጫችንን እየሸበብን ወደ መቃብራችን ለማዝገም የምንመርጥ አይመስለኝም፡፡

ጽሁፌን የማሳርገው ከላይ የዘረዘርኳቸውን ጥናታዊ ሰነዶች ቅጂ ማቅረብን ጨምሮ በተቃራኒው በጭምብል የፀረ-ቫይረስ ጠቀሜታ ዙርያ የሚቀርብ አሳማኝ ማስረጃ ካለ አቋሜን ለመቀየር ምን ጊዜም ዝግጁ መሆኔን በማረጋገጥ ነው፤ ሳይንስ በኃሳብ ፍጭት የሚዳብር እንጂ በስነ-መለኮት ድንጋጌ የሚመራ አይደለምና! የኮቪድ-19 ዘመቻ አስተሳሰብም ከዚህ እንደማያፈነግጥ አምናለሁ፡፡

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top