Connect with us

በአርባምንጭ ከተማ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠረች እንስት ሕይወቷን አጠፋች

ፎቶ፦አርባ ምንጭ ከተማ ባሕልና ቱሪዝም ጽ/ቤት

ዜና

በአርባምንጭ ከተማ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠረች እንስት ሕይወቷን አጠፋች

በደቡብ ክልል አርባምንጭ ከተማ በኮቪድ 19 ተሐዋሲ በመጠርጠሯ ሕይወቷን ያጠፋችው እንስት ከተሐዋሲው ነፃ (negative) ኾና መገኘቷን የአርባምንጭ ከተማ ፖሊስ ዐስታወቀ።

የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዳንኤል አረጋ ዛሬ ለዶቼ ቨለ (DW) አንደገለጹት ወርቅነሽ ዲባባ የተባለችው የ25 ዓመት ወጣት ባለፈው ዓርብ እራሷን አጥፍታ የተገኘችው በአርባምንጭ ከተማ የሙቀት ልኬት ከተደረገላትና በለይቶ ማቆያ እንድታርፍ ከተደረገች በኋላ ነው።

ኮማንደር ዳንኤል በማያያዝም «በእለቱ በአርባምንጭ ከተማ መግቢያ ላይ በአውቶብሱ ውስጥ በነበሩ 36 መንገደኞች ላይ የሙቀት ልኬት ፍተሻ ይካሄዳል። የሟች ወርቅነሽ የሙቀት መጠን ከፍ ብሎ በመገኘቱ ከሌሎች ተጓዦች ተለይታ አንድትቀር ይደረጋል። በምርመራ እንዳረጋገጥነው ወጣቷ ምናልባት የገጠር ነዋሪ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል በሁኔታው የመደናገጥ፣ የመረበሽና የመገለል ስሜት ይስተዋልባት ነበር። የደም ናሙና ምርመራ አንደሚደረግላትና ከተሐዋሲው ነፃ ከሆነች ጉዞዋን እንደምትቀጥል ተሐዋሲው ካለባት ደግሞ እዚሁ የህክምና ድጋፍ እንደሚደረግላት ተነግሯት በለይቶ ማቆያ እንድታርፍ ተደርጋ ነበር። ይሁን እንጂ በማግስቱ ጠዋት ባደረችበት የማቆያ ክፍል ውስጥ በለበሰችው የአንገት ልብስ (ሻርፕ) እራሷን ሰቅላ መገኘቷን ለማረጋገጥ ተችሏል» ብለዋል ።

የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት አስተባባሪ አቶ በርገና ኦላሞ በበኩላቸው በእርግጥ ሟች ወርቅነሽ ከሌሎች መንገደኖች ተለይታ በመቅረቷ ደስተኛ አልነበረችም ፣ የመረበሽ ስሜትም ይታይባት ነበር ይላሉ። የምርመራ ውጤቷ እስከ ነገ እንደሚታወቅና እዚህ የምትቆየውም ለአንድ ሌሊት ብቻ እንደሆነ በማግባባት በማቆያው እንድታርፍ መደረጉን ይናገራሉ።

አስተባባሪው አክለውም «ወርቅነሽ በእለቱ ያረፈችው በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ውስጥ ነው። በተሰጣት የማረፊያ ክፍል ውስጥ ቀኑን በሰላም ማሳለፏን እርግጠኞች ነን። በነጋታው ግን የህክምና ባለሞያዎች መደበኛ ቅኝት ሲያደርጉ አንድ ሰው መጉደሉን በማረጋገጥ ሪፖርት አደርጉ። በሪፖርቱ መነሻነት በተደረገው ክትትል ወርቅነሽ ባረፈችበት ክፍል ሞታ መገኘቷንና ፖሊስም ሕይወቷን በራሷ እጅ እንዳጠፋች ማረጋገጡን ገልጾልናል። አሳዛኙ ነገር ግን የወርቅነሽ የደም ምርመራ ውጤት ሲመጣ ከኮረና ተሐዋሲ ነፃ (negative) እንደነበረች የሚያረጋግጥ ሆኖ መገኘቱ ነው» ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ሲጠየቁ የፍረሃት፣ የጭነቀትና የመገለል ስሜት እንደሚስተዋልባቸው የሚናገሩት የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት አስተባባሪው አቶ በርገና ለይቶ ማቆያ በመግባታቸው ብቻ ራሳቸውን በተሐዋሲው አንደተያዙ አድርገው የሚቆጥሩ ብዙዎች ናቸው ይላሉ። በቀጣይ በኮረና ወረርሽኙ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፈጠር ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በለይቶ ማቆያ ማዕከላት የስነ ልቦና ምክር አገልግሎት (counselling service) በስፋት ሊቀርብ ይገባል ሲሉም ምክረ ሀሳባቸውን ለግሰዋል ።

ዶቼ ቨለ (DW) የሟች ወርቅነሽ ቤተሰቦችን አስተያየት ለማካተት ጥረት ቢያደርግም ቤተሰቦቿ ይገኙበታል የተባለው ጋሞ ዞን ደራ ማሎ ወረዳ ኤሊ በተባለች የገጠር መንደር ምንም አይነት የስልክ መገናኛ አገልግሎት ባለመኖሩ ሊሳካ አልቻለም ።

ዘገባ፦ ዶቼ ቨለ | ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ ከሀዋሳ

(ፎቶ፦አርባ ምንጭ ከተማ ባሕልና ቱሪዝም ጽ/ቤት)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top