Connect with us

የባንኮች ማህበር የብሔራዊ ባንክን መመሪያ ደገፈ

የባንኮች ማህበር የብሔራዊ ባንክን መመሪያ ደገፈ
Photo: Facebook

ኢኮኖሚ

የባንኮች ማህበር የብሔራዊ ባንክን መመሪያ ደገፈ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች የሚወጣን የጥሬ ገንዘብ መጠን ገደብ የሚጥል መመሪያ ማውጣቱ የባንኮች ማህበር ለረጅም ጊዜያት ሲያቀርብ የነበረው ጥያቄ ምላሽ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቤ ሳኖ ከማህበሩ የቦርድ አመራሮች ጋር በጋራ በሰጡት በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንዳሉት መመሪያው ህብረተሰቡን አማራጭ የክፍያ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ከማስቻሉም በላይ የሀገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ በመሰረታዊነት መቀየር የሚችል ነው።

አቶ አቤ አክለውም በአዲሱ መመሪያ ከዚህ በኋላ ማንኛውም ግለሰብ ከባንክ በጥሬ ገንዘብ ማውጣት የሚችለው በቀን እስከ 200 ሺሕ ብር ወይም በወር አንድ ሚሊዮን ብር እንዲሆን መደረጉን ገልፀው፤ ድርጅቶች ደግሞ በጥሬ ገንዘብ ከባንክ ማውጣት የሚችሉት የገንዘብ መጠን በቀን እስከ 300 ሺሕ ብር እንዲሁም በወር 2.5 ሚሊዮን ብር እንዲሆን መወሰኑን ገልፀዋል፡፡

አብዛኛው የህብረተስብ ክፍል በቀን ውስጥ የሚያወጣው የጥሬ ገንዘብ አሁን በመመሪያ ከወጣው በጣም ያነሰ መሆኑን ከመግለጫው መረዳት ተችሏል፡፡

ከተጠቀሰው የገንዘብ መጠን በላይ ማውጣትና ግብይት መፈጸም የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከሂሳብ ወደ ሂሳብ ማዘዋወር፣ ወይም በቼክና በሲፒኦ መጠቀም እንደሚቻልም ነው አቶ አቤ የገለፁት፡፡

በኢትዮጵያ ከባንክ ውጭ በግለሰቦች የሚዘዋወረው ገንዘብ ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎት ቆይቷል፤ ይህ አይነቱ መመሪያም በገበያው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ጥሬ ገንዘብ በአግባቡ ለማንቀሳቀስና ወደ ቁጠባ ለማምጣት እንደሚያስችልም ነው የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ የገለፁት።

የባንኮች ማህበር እንዳስታወቀው ከሆነ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ የሚያስችለው ውሳኔ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ነው። በተለይ ባንኮች በርካታ ሀብት ያፈሰሱባቸውን አማራጭ የባንክ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም ያስችላል፤ ገንዘብ በህጋዊ ስርዓት በገበያው ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ያግዛል፤ለጥሬ ገንዘብ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ወጪ ይቀንሳል፤ በገበያው ውስጥ የሚዘዋወረውን የሀሰተኛ ገንዘብ እንቅስቃሴ ያስቀራል፤ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ይከላከላል፤ ከሌላው ዓለም ጋር እኩል እንድንራመድ ያደርጋል፤ በቅርንጫፎች ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሬ ገንዘብ በተቀነባበረ መንገድ እንዳይዘረፍ ይከላከላል፤ የባንኮቹንና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ጉልበትና የገንዘብ ወጪ ይቀንሳል እንዲሁም የገንዘብ አስቀማጩን ደህንነት ለማረጋገጥ ያስችላል ነው የተባለው።

የዳሽን ባንክ ፕሬዚዳንትና የባንኮች ማኅበር ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት የሚታተም ገንዘብ ቤት ውስጥ ማስቀመጥ ወንጀል መሆኑን መረዳት እንዳለበት ገልፀው የወጣው መመሪያም የባንኩን ዘርፍ የሚያዘምን፣ የሀገራችንን ልማት የሚያፋጥን እና የሚደረጉ የዝርፊያ ሙከራዎችን የሚያስቀር ይሆናል ብለዋል።

የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንትና የማህበሩ የቦርድ አባል አቶ ደረጀ ዘበነ በበኩላቸው የመመሪያው መውጣት ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደማያመጣ ገልፀው እንዲያውም ደንበኞች ገንዘባቸውን በሒሳብ ቁጥር፣ በሲፒኦ፣ እንዲሁም በኢንተርኔትና ሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች አማካኝነት ያለገደብ ማዘዋወር እንዲችሉ ያደርጋል ብለዋል።

የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የማህበሩ አባል አቶ ፀሐይ ሺፈራው በበኩላቸው ከተጣለው ገደብ በላይ ጥሬ ገንዘብ የሚያስፈልግበት አጋጣሚ ወይም ችግር ሲፈጠር መመሪያው በልዩ ሁኔታ ፈቃድ እንደሚሰጥ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

በሌሎች ሀገራት ያለገደብ ጥሬ ገንዘብ ማውጣት የቀረ አሰራር ሲሆን ይህ መመርያ የወጣው የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮ በማየት ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ተጠቅሞ ገንዘብ ማንቀሳቀስ ወቅቱ የሚጠይቀው እንደሆነ በመግለጫው ተመልክቷል።

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top