Connect with us

የጤና ሚኒስቴር የቴንሴንት ፋውንዴሽን የላካቸውን ቁሳቁሶች ተረከበ

የጤና ሚኒስቴር የቴንሴንት ፋውንዴሽን የላካቸውን የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ቁሳቁሶች ተረከበ
Photo: Facebook

ዜና

የጤና ሚኒስቴር የቴንሴንት ፋውንዴሽን የላካቸውን ቁሳቁሶች ተረከበ

የቴንሴንት ኩባንያ የታዋቂው ማኅበራዊ ትስስር ገጽ “ዊ ቻት” ባለቤት ሲሆን በዋናነት በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማራ ኩባንያ ነው።

የኩባንያው ፋውንዴሽን ለኢትዮጵያ 100 ሺህ የመመርመሪያ መሳሪያዎችና ሁለት ሚሊዮን የህክምና ጓንቶችን የላከ ሲሆን፤ ድጋፉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ተረክበዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጄን በዚሁ ጊዜ ሀገራቸው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን የመከላከሉ ስራ በተናጥል ሳይሆን በትብብርና በጋራ እንዲከናወን እንደምትሻ ገልጸዋል።

ለዚህም ነው የቻይናው ፕሬዚዳንት ዤን ፒንግ ከቀናት በፊት በተካሄደው የዓለም ጤና ድርጅት ጉባኤ ላይ ስለ ትብብር አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ብለዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነታቸውን ቀደም ብለው ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂክ አጋርነት ማሳደጋቸውን አስታውሰው፤ የዛሬው ድጋፍም ይህንኑ እንደሚያሳይ አክለዋል።

ቻይናን ጨምሮ ኮሮናን በስኬት መከላከል ከቻሉ አገራት ጀርባ ያለው ምስጢር የምርመራ ተደራሽነት መሆኑንም ነው የተናገሩት። ከዚህ አንጻር የተደረገው ድጋፍ ለኢትዮጵያም ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል ከያዛቸው ቁልፍ ስትራቴጂዎች አንዱ የምርመራ አቅምን ማስፋት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን እውን ለማድረግም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የተደረገው ድጋፍ ጥረቱን በማገዝ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ለተደረገው ድጋፍም በመንግስትና በጤና ሚኒስቴር ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላውን አፍሪካ እያገለገለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ናቸው።

አየር መንገዱ የተፈጠረውን ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ እንደ ዕድል እየተጠቀመ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ካሉት የጭነት አውሮፕላኖች በተጨማሪ 25 የመንገደኛ አውሮፕላኖችን ወደ ጭነት ማጓጓዣነት በመቀየር ደንበኞቹን አያገለገለ እንደሚገኝም በአስረጂነት አንስተዋል።

አየር መንገዱ ይህን በማድረጉ ያለምንም የመንግስት ድጋፍና ብድር ሰራተኞቹን ሳይቀንስ ማቆየት መቻሉን ገልጸው፤ ይህም በዘርፉ የተፈጠረውን አስቸጋሪ ወቅት በስኬት እያለፈ ያለ ብቸኛው አየር መንገድ ያደርገዋል ያሉት አቶ ተወልደ፤ በዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኩራት ሊሰማው ይገባል ብለዋል። ENA

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top