አሣ ከመርዳት ማጥመድ ማስተማሩ የሚቀለው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፤ ጥሩ አድርጎ አሣ ላጠመደ አሣ እመርቃለሁ ብሎ መጥቷል፡፡ አዲሱ የኃይሌ ቻሌንጅ፤ ህይወት፣ ውበት፣ ገንዘብና ሰውን የመቀየር መንፈስ
ከሄኖክ ስዩም ድሬቲዩብ
ትናንት ፍራፍሬውን ተሸክሞ ሰይፉ ሾው ላይ ከተፍ ሲል በሙሉ ልቤ አንድ ነገር አመንኩ፡፡ ኃይሌ ገዝቶ አይመጣም፤ አድርጎታል ማለት ነው፡፡ ስኬቱ የጥረት ነው፡፡ ህይወቱን እንደ ሩጫ ስፖርቱ ካሳበችው ወደኋላ እንዳትቀርና እንዳትንቀረፈፍ አድርጓታል፡፡
በአነስተኛ ቦታ የግብርና ስራ በኢትዮጵያ አልተለመደም፡፡ ሰፊ ግቢ ያለው ሰው ገበያ ወጥቶ ጤና አዳም ይገዛል፡፡ ጓሮ ያለው የዶሮ ዋጋ በዛ ብሎ ያማርራል፡፡ ባለ ብዙ ሆቴሉ፣ ዓለም አቀፉ ሯጭ፣ ባለ ሃብቱ ኃይሌ በቴሌቨዥን መስኮት መጣ፡፡ ኃይሌ እንዲህ ባለው መድረክ ዝም ብሎ አይወጣም፡፡ ግሩም ሀሳብ ለወጣት ያቀብላል፡፡ ሀገር የሚቀይር መንፈሱ ይታያል፡፡
ሰይፉ ሾው ላይ ፍራፍሬ ተሸክሞ የመጣው ኃይሌ ሰፋፊ ስለኾኑ ግዙፍ የግብርና ኢንቨስትመንቶቹ ምራቃችንን እያስዋጠ አልተረከልንም፤ ይልቁንም ትንሽ ቦታ ትልቅ ነገር እንዴት እንደምትሰራ ለማስታወስ ፈለገ፡፡
ኃይሌ ገብረሥላሴ አሣ መስጠት አይወድም፡፡ አሣ መስጠት የጠላት ሀሳብ ነው ለሚሉት የሚጠቅም የመላ ሰው ነው፡፡ ግን አሣው የት እንዳለ ያሳያል፡፡ አሣው ድረስ ይወስዳል፡፡ አሣ የማጥመድ ጥበብን ያስተምራል፡፡ ግቡ ሁሉም ሰው ማንንም ሳይጠብቅ አሣ በልቶ ያድር ዘንድ ማድረግ ነው፡፡
ሰውዬው አትሌት ብቻ አይደለም፡፡ ስራ ፈጣሪና የቢዝነስ መምህር ነው፡፡ አንድ ሰው ከሚቀይሩ ትንንሽ ሀሳቦችን ከማጉነን ግዙፍ እቅዶችን እውን አድርጎ ለብዙዎች የስራ እድል መፍጠርን መላ ብሎ ይዞታል፡፡ መላው ለወገን የደረሰ ትልቅ አስተዋጽኦ ነው፡፡
ኃይሌ ቻሌንጅ በጀት የመደበለት ስራ ሲሆን አነስተኛ ቦታዎችን ተጠቅሞ የግብርና ምርትን ለሚያመርት ከተሜ ሽልማት ይሰጣል፡፡ ይሄ ሀሳብ ህይወት ነው፡፡ የአረንጓዴ እጽዋት ፋይዳ ከሰው ልጅ እድሜ ጤናና ፈውስ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አላቸው፡፡
እንደ ጥላ የምንተክላቸው የፍራፍሬ ዛፎች ምግብም ናቸው፡፡ ገንዘብ በማጣት የሚገታ አታክልትን የመመገብ ፍላጎት በቀላሉ በሚገኝ የእረፍት ቀናት እንክብካቤ እውን ይሆናል፡፡
ኃይሌ ቻሌንጅ ውበት ነው፡፡ ደጃፎቻችን እና ጓሮዎቻችን ከቆሻሻ መጣያነት ይፈወሳሉ፡፡ ለዓይን ምግብ የኾኑ የምግብ ተክሎችን ማምረት መቻል ነው፡፡ አነስተኛና የተናቀ ቦታ ላይ ልብን የሚያሳርፍ ውበት ማኖር ነው፡፡
በሌላ በኩል ቻሌንጁ ገንዘብ ነው፡፡ ታላቁ አትሌት ቦታችሁን ልቀቁ ላልማበት እና ገንዘብ ላግኝ የሚል ሀሳብ ይዞ አልመጣም፡፡ በቦታችሁ ሁኑ፤ በዚህ መልኩ አልሙ፤ አሪፍ ነገር የሰራውን እሸልመዋለሁ ብሏል፡፡ ይህ አነስተኛ ቦታን ተጠቅሞ በግብርና ስራ ትርፍ ጊዜን ማሳለፍ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ በቀላሉ ከአታክልትና ፍራፍሬ ወጪዎች ይታደገናል፡፡ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ካለን ደግሞ ገንዘብ እናገኛለን፡፡ ሰባት መቶ ብር ዶሮ ከመግዛት በጥሩና ተገቢ ዋጋ ለወገን ለመሸጥ የሚያስችል እድል ይኖረናል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ቻሌንጁ ራስን መለወጥ ነው፡፡ በአለን ውስን አቅምና እድል ትልቅ ራዕይ ይዞ የመነሳትና ያንን እውን የማድረግ ጅማሬ ነው፡፡ ውዱን የኢትዮጵያ ልጅ ኃይሌን አለማመስገን ንፉግነት ነው፡፡