Connect with us

የኤሌክትሮኒክ ንግድና ግብይትን ሕጋዊ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

የኤሌክትሮኒክ ንግድና ግብይትን ሕጋዊ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ቀረበ
Photo: Reporter

ሳይንስና ቴክኖሎጂ

የኤሌክትሮኒክ ንግድና ግብይትን ሕጋዊ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

የኤሌክትሮኒክ ንግድ ግብይትና ትራንዛክሽንን በሕግ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ። ‹‹የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ ረቂቅ ሕግ ለምክር ቤቱ የቀረበው ባለፈው ሳምንት ሲሆን፣ ጉዳዩ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር መርምሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ተመርቷል።

ረቂቅ አዋጁ ባስቀመጣቸው ትርጓሜዎች መሠረት ‹‹ኤሌክትሮኒክ ንግድ›› ማለት ኢንተርኔትን ወይም ሌሎች የመረጃ መረብን በመጠቀም የሚከናወን የሸቀጦችና አገልግሎቶች ግብይት ወይም ልውውጥ ነው።

በሌላ በኩል ‹‹ኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን›› ማለት ተንቀሳቃሽ ስልክንና ሌሎች መሰል መሣሪያዎችን ጨምሮ በኮምፒዩተር በታገዘ የኢንፎርሜሽን መረብ ሥራን ማከናወን መሆኑን፣ የኤሌክትሮኒክ ንግድና የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አገልግሎትን እንደሚያካትት ረቂቁ የሰጠው ትርጓሜ ያመለክታል።

በኤሌክትሮኒክ ንግድ አማካይነት የሚከናወኑ ግብይቶች በሸማቹ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለመጠበቅ፣ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አማካይነት የሚያቀርብ ድርጅት ወይም አቅራቢ ማሟላት የሚጠበቅበትን መሥፈርቶች ይዘረዝራል።

ሸማቹ በመረጃ ላይ በመመሥረት እንዲወስን ለማስቻል አቅራቢው ስላቀረባቸው ሸቀጦችና አገልግሎቶች ዓበይት ባህሪያት በቂ መግለጫ መስጠት እንዳለበት፣ የትራንስፖርት ወጪንና ታክስና ሌሎች ክፍያዎችን ወይም ወጪዎችን ጨምሮ የሸቀጦቹንና የአገልግሎቶቹን ሙሉ ዋጋ ማቅረብ እንደሚገባው ረቂቅ ድንጋጌው ያመለክታል።

ሸማቾች ሙሉ የኤሌክትሮኒክ ግብይቱን እንዲገመግሙ፣ ግብይት ጀምረው ከመፈጸማቸው በፊት ስህተቶችን እንዲያስተካክሉ፣ ግዥ ከመፈጸማቸው በፊት ግብይቱን ትተው እንዲወጡ ዕድል መስጠት እንደሚኖርበትም በረቂቅ ድንጋጌው ተካቷል።

የሸቀጡን ታሳቢ መሠረት በማድረግም ሸማቹ ያለ ምንም ምክንያትና ቅጣት ዕቃውን ከተቀበለበት ቀን ጀምሮ ባሉ ሰባት ቀናት ውስጥ ወይም አገልግሎቱን መቀበል ከጀመረ በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ የኤሌክትሮኒክ ግብይቱን መሠረዝ እንደሚችል፣ ይህ በሚሆንበት ወቅት አቅራቢው በሸማቹ ላይ ሊጥል የሚገባው ክፍያ ሸቀጡን ተመላሽ ለማድረግ የሚወጣ ቀጥተኛ ወጪን ብቻ እንደሆነም ረቂቁ ያመለክታል።

ክፍያ እንዲፈጸም የሚጠይቅ ትራንዛክሽን ክፍያው በኤሌክትሮኒክ መንገድ ከተፈጸመና አግባብነት ያለው የመንግሥት ተቋም ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ፣ በሕግ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ እንደተሟላ እንደሚቆጠር ረቂቅ ድንጋጌው ይገልጻል።

ለምሳሌ ከፍያ ለተፈጸመበት የንግድ ግብይት የክፍያ ደረሰኝ እንዲሰጥ በሌላ ሕግ ግዴታ የተቀመጠ ከሆነ፣ በሕግ የተቀመጠው ግዴታ እንደተሟላ እንደሚቆጠርና ይህ የሚሆነው ግን ኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሲሰጥ፣ ኤሌክትሮኒክ ደረሰኙ የወረቀት ደረሰኝ ይዘትን ሲያሟላ እንደሆነ ይገልጻል።

ይህ ረቂቅ አዋጅ ካካተተው የኤሌክትሮኒክ ንግድ በተጨማሪ የመንግሥት አገልግሎት በኤሌክትሮኒክ መንገድ ሊቀርብ የሚችልበትን ሕጋዊ ሥርዓትም አስቀምጧል። በዚህም መሠረት በሕግ መሠረት ሰነዶችን እንዲቀበል፣ እንዲያዘጋጅ፣ እንዲያስቀምጥና ፈቃድ እንዲሰጥ ኃላፊነት የተሰጠው የመንግሥት ተቋም ይህንን አገልግሎት በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን መሠረት ማከናወን እንደሚችል በረቂቁ ተካቷል።

የፌዴራል የኤሌክትሮኒክ ነጋሪት ጋዜጣም በዚሁ ረቂቅ አዋጅ እንዲቋቋም የሚያስችል ድንጋጌ አለ፡፡ የምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር መርምሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ታዟል።(ዮሐንስ አንበርብር ~ ሪፖርተር)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ሳይንስና ቴክኖሎጂ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top