የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤት ስለ ቫይረሱ ምን ይነግረናል? | አምኃየስ ታደሰ | amhayest@gmail.com
መጠሪያውን ሳርስ-ሲኦቪ-2 (ኤስሲ2) ያደረገው የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ከሚያስከትለው እልቂት የሚታደገንን ክትባት “እጃችንን እየታጠብንና ጭምብል በማጥለቅ ተራርቀን ከመጠበቅ ውጪ ምርጫ እንደሌለን“ የሚሞግተንን መለኮታዊ ገፅታው የገዘፈ አመለካከት ከስዊድን በስተቀር መላው ዓለም ለመቀበል ከተገደደ እነሆ ወራት ተቆጠሩ፡፡ ወረርሽኙን ለማስቆም በሚል የሚወሰደው እርምጃ የሕግ ከለላ እያገኘ በመጣበት በቅርቡ ደግሞ ለኮቪድ-19 ቫይረስ ተጋላጭ ስለመሆናችን ቤት-ለቤት በሚደረግ አሰሳ ጭምር መረጋገጥ መጀመሩን እያስተዋልን ነው፡፡
ታዲያ ከምድረ-ገፅ መጥፋታችን ያስጨነቃቸውን በጐ-አድራጊዎች እያመሰገንን አንዳንዶች ከመላዕከ-ሞት ጋር እንደመጋፈጥ የቆጠሩትን በሰውነታችን ውስጥ የቫይረሱን መኖር የሚያሳውቅ የምርመራው ውጤት በፀጋ ተቀብለን ወደ ነጥሎ ማቆያ ስፍራ የምናቀናው በሽታውንና መንስኤውን አስመልክቶ ያለው እውነታ በርግጥም ያለመታከት ሲነገረን ከቆየው የተለየ ሆኖ ካላገኘነው ይመስለኛል፡፡
ለአብነትም በኮቪድ-19 ዙርያ የተዘጋጀው የኤፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር ሁሉን-አቀፍ ብሄራዊ መመሪያ “በአሁኑ ወቅት ለመደበኛ ምርመራ እንዲውል የተፈቀደው (approved) አርቲ-ፒሲአር የተባለው ቴክኖሎጂ” እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ”የቫይረሱ አርኤንኤ ወይም ሪቨርስ-ትራንስክሪኘቴስ ኤንዛይም በመተንፈሻ አካል ውስጥ ናሙናው በተወሰደበት ወቅት መኖሩን በሚያጣራው” በዚሁ ፖሊመሬዝ ቼን ሪአክሽን በተባለ ቴክኖሎጂ “የበሽታው ምልክቶች የሚታዩባቸው ሕሙማን በሙሉ ምርመራ ሊደረግላቸው እንደሚገባ” የሚያስገነዝበው መመሪያ “የምርመራው ውጤት በስሕተት ኔጌቲቭ (false negative) እንዲሆን የሚያደርጉ ከናሙና አወሳሰድ አና ማጓጓዝ ጋር የተያያዙ እንዲሁም ቴክኒካዊ ምክንያቶች በመኖራቸው ነፃ የተባሉ ተጠርጣሪ ሕሙማን በሙሉ ከታችኛው የመተንፈሻ አካላቸው ተጨማሪ ናሙና በመውሰድ ውጤቱን ማስረገጥ እንደሚጠበቅ” ሰነዱ ሳያስገነዝብ አላለፈም፡፡
በአንፃሩ ምርመራው ምናልባትም ቫይረሱ በሌለበት ማለትም በስሕተት ፖዚቲቭ ውጤት ሊያስመዘገብ ስለመቻሉ ጨርሶ የማያወሳው የጤና ሚኒስቴር መመሪያ “ቫይረሱ ተገኘ ተብሎ ሊደመደም የሚገባው ከፒሲአር ምርመራ በተጓዳኝ ከሚካሄድ የሕሙማኑን አካላዊ የጤንነት ሁኔታ እና የበሽታውን አመላካቾች ታሳቢ ካደረገ ተጨማሪ የማረጋገጥ ሂደት ሊሆን እንደሚገባ” አያይዞ ለመጠቆም ምን እንዳነሳሳው ማወቅ የምርመራ ውጤታችንን ምንነት በመረዳት በመረጃ የተደገፈ ውሣኔ (informed consent) ላይ ለመድረስ እንደሚያስችለን አምናለሁ፡፡
ከሌሎች የሕክምና ምርምርና የጤና ተቆጣጣሪ ተቋማት አማኝነት መነሳት የምርመራውን ገፅታ በአግባቡ ለመረዳት ከማስቻሉ አንፃር የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል (CDC) 2019-ኤንሲኦቪ አርቲ-ፒሲአርን አስመልክቶ የሚለውን እናስቀድም፡፡ ከጤና ሚኒስቴር በተለየ ሁኔታ ሲዲሲ “በምርመራው የቫይረሱ አርኤንኤ ተስተዋለ ማለት የበሽታ መንስኤ የሆነ ቫይረስ በሕሙማኑ ሰውነት ውስጥ ተገኘ ማለት ላይሆን እንደሚችል (may not indicate the presence of infectious virus)” በመጠቆም ሳይገታ ይልቁንም ”በተመርማሪው ላይ የሚስተዋሉት ክሊኒካዊ የጤና ችግሮች መንስኤያቸው (causative agent) የኮቪድ-19 ቫይረስ ነው ብሎ ለመደምደም እንደማያበቃ” ይገልፃል፡፡
ሲዲሲ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጠቁመው የምርመራ ውጤቱ የቫይረሱን መኖር ቢያመላክትም ኮቪድ-19 ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዘ የጤና ችግር ማስከተሉ አለመረጋገጡን ሲሆን የማዕከሉን መግለጫ በጥልቀት መፈተሽ ደግሞ ቫይረሱ ከነ ጭራሹ በሕሙማኑ ሰውነት ውስጥ ፈጽሞ ላይኖር የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩን ከመጠቆሙ አንፃር ፒሲአር ለተጠቀሰው ምርመራ ስለመዋሉ የዓለም የጤና ድርጅትን አቋም ማጤን አግባብነት አለው፡፡
የኮቪድ-19 የቤተ-ሙከራ የደም ምርመራ በሕሙማን ላይ እንዴት ሊደረግ እንደሚገባው የሚገልጸው የመንግስታቱ የጤና ድርጅት የቴክኒክ መመሪያ “አንዳንድ የፒሲአር የመመርመሪያ መንገዶች ቫይረሱን ብቻ ነጥለው ቢያሳዩም የተወሰኑ መሳሪያዎች ደግሞ ሕሙማኑ ነባሮቹ የሳርስ ኮኖና አና ከተመሳሳይ ጐራ የሚመደቡ ሌሎች ቫይረሶች ቢኖሩባቸውም (some may also detect other strains) ፖዚቲቭ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ“ አልሸሸገም፡፡
የመንግታቱ የጤና ድርጅት ከምርመራ ሂደቱ ውስንነት ጋር በማያያዝም “አማራጭ ክሊኒካሙ ናሙናዎች ለምርመራ እንዲውሉ አልተፈቀዱም (Optional clinical specimens for testing has [have] not yet been validated)” ማለቱ የቫይረሱን በሰውነት ውስጥ መኖር አስረግጦ ለማወቅ የሚያስችል በሌላ የሕሙማኑ የአካል ክፍል ላይ ሊደረግ የሚገባ ተጨማሪ ምርመራ እንደሌለ የሚገልጽ ሲሆን ይኽም የጤና ሚኒስቴር የተሳሳተ ኔጌቲቭ ውጤትን ተከትሎ በተጨማሪ ሊደረግ ይገባል ከሚለው የፒሲአር ምርመራ ጋር የሚቃረን መሆኑን ሳንዘነጋ ወደ የአሜሪካው የምግብና የመድሃኒት አስተዳደር (FDA) ምስክርነት እናቅና፡፡
ኤፍዲኤ በላብኮርኘ ኪቪድ-19 አርቲ-ፒሲአር ኢዩኤ (የአሜሪካ ቤተ-ሙከራ ኮርፖሬሽን) የቴስት ኪት ማጠቃለያ ላይ “የኮቪድ-19 ቫይረስ መኖር የሚታወቀው ሕሙማኑ ለቫይረሱ በተጋለጡበት ሰሞን ከመተንፈሻ አካል ከሚወሰድ ናሙና በመነሳት እንደሆነና ፖዚቲቭ ውጤት የቫይረሱን አርኤንኤ (Positive results are indicative of the presence of SARS-CoV-2 RNA) እንጂ ኮቪድ-19 በሰውነት ውስጥ መኖሩን እንደማያረጋግጥ ይልቁንም ሕመምተኛው ከሚታዩበት ምልክቶች፣ የጤና ታሪክ እንዲሁም ከሌሎች የምርመራ መረጃዎች በመነሳት በቫይረሱ የመጠቃት ውጤት ሊታወቅ (other diagnostic information is necessary to determine patient infection status) እንደሚገባ“ ያትታል፡፡
ተቆጣጣሪው አክሎ “የምርመራው ውጤት የሆነው ባዕድ-አካል የበሽታው እርግጠኛ መንስኤ ላይሆን ይችላል (The agent detected may not be the definite cause of disease)“ ከሚለው ግራ የሚያጋባ አቋሙን የቋጨው “እንዲያም ሆኖ ፖዚቲቭ የምርመራ ውጤቶች በሙሉ ሪፖርት ሊደረጉ እንደሚገባ“ በመጠቆም መሆኑ ቫይረሱ ተገኘባቸው የሚባለውን ሠብአዊ ፍጡራን አኃዝ ለማሳበጥ ስላለመሆኑ በርግጠኝነት ለመናገር አያስደፍርም፡፡
በአገራችን እየተሰራባቸው ያሉት የትኞቹ የፒሲአር የምርመራ መሣሪያዎች እንደሆኑ ከጤና ሚኒስቴርም ሆነ ከእኛው ኤፍዲኤ ድረ-ገፅ ማግኘት ባለመቻሌ የሚኒስቴር መ/ቤቱ እንዴት የተሳሳተ ፖዚቲቭ ውጤት ሊኖር እንደሚችል አለመግለጽ ስላለው አግባብነት ተጨማሪ ፍንጭ የሚሰጡ የመሰለኝን በተለይ የአሜሪካውን ኤፍዲኤን ቡራኬ አግኝተው ለኮቪድ-19 ምርመራ አገልግሎት የተፈቀዱ ፒሲአሮች የምርት መግለጫ (Packet Insert) በመዳሰስ ጽሁፌን ላሳርግ ወሰንኩ፡፡
የኤክፒአርሳርስ-ሲኦቪ2-10 አምራች የሆነው ጄንኤክፐርት የተባለ ኩባንያ መሣሪያው “በሌሎች የባክቴሪያና የቫይረስ ተደራቢ ጥቃቶች ጭምር ፖዚቲቭ ውጤት ሊያስመዘግብ እንደሚችል (do not rule out bacterial infection or co-infection with other viruses)“ ብቻ ሳይሆን “በምርመራው የተገኘው ኤጀንት በሕሙማኑ ላይ የሚስተዋለው በሽታ ትክክለኛ መንስኤ ላይሆን ይችላል ሲል“ የኤፍዲኤን እና የሲዲሲን ማስጠንቀቂያ መሰል አቋም ጭምር ይጋራል፡፡
ክሬቲቭ ዲያግኖስቲክስ የተባለው ፋርማሲዩቲካል ኩባንያ ደግሞ አርቲ-ኪውፒሲአር “ለቤተ-ሙከራ የምርምር አገልግሎት እንጂ የቫይረሱን በሰውነት ውስጥ መኖር ለማረጋገጥ ተግባር ሊውል እንደማይገባ ይልቁንም ከኮቪድ-19 ጋር ቁርኝት በሌላቸው (non-specific interference) በተለይም ኢንፍሉዌንዛ እና ኒሞንያን ጨምሮ ሌሎች የመተንፈሻ አካል በሽታ አምጪ ጀርሞች በሚያስከትሉት መምታታት የተነሳ የተሳሳተ ፖዚቲቭ ውጤት እንደሚከሰት” ያስገነዝባል፡፡
በነገራችን ላይ በ1990ዎቹ መግቢያ ላይ የኤድስ መንስኤ ነው ተብሎ የሚታመነውን የኤችአይቪ ቫይረስ አሃዝ ወይም አርኤንኤ ለመቁጠር እንዲያገለግል ተግባራዊ የተደረገው የበራሄ ጅናዊ ርዝራዦችን ለማባዛት (amplifying genetic fragments) የዋለውን ፒሲአር (Polymerase Chain Reaction) የተባለውን ቴክኖሎጂ በመፈልሰፍ በኬሚስትሪ የ1993 የኖቤል ተሸላሚ የሆነው አማሪካዊ ባዮ-ኬሚስት ዶ/ር ካሪ ሙሊስ የግኝቱን ለበሽታ አምጪ ቫይረስ ምርመራ መዋል በፅኑ ከሚቃወሙት ሳይንቲስቶች አንዱ ነበር፡፡
የመገናኛ ብዙሃን እና የጤና አጠባበቅ ተቋማት ባይነግሩንም ለኮቪድ-19 ምርመራ የዋሉት አንዳቸውም መንገዶች ከሠው ወደ ሠው በቀላሉ እየተላለፈ በሰውነት ውስጥ በገፍ ይራባል የሚባለውን ፈውስ-አልባ የመተንፈሻ አካል የሚያወድም ቫይረስ መኖር ለማረጋገጥ (infection) እንዲውሉ አልተፈቀዱም፣ በአርኤንኤ እና የሪቨርስ ትራንስክሪኘቴስ ኤንዛይም ብሎም ፀረ-እንግዳ አካላት እና ኘሮቲኖች አመላካችነት በተዘዋዋሪ መንገድ ቫይረስ የተባለው የባዕድ-አካል መታየቱን ለመጠቆም እንጂ፡፡ ከዚህም አንፃር የቤት-ለቤት ፍለጋ እና የመመርመር ቅስቀሳና ግዴታ ተጠቃሚው ሊታወቅና ዓላማው ሊጤን የሚገባው ይመስለኛል፡፡
ይኹንና በዘመነ-ግሎባላይዜሽን ከሠው ልጅ ጤንነት ይልቅ ቅድሚያ የተሰጠው ምጣኔ-ኃብታዊ ፍላጎት ሆኖ ጨዋታዎች ሁሉ በንግድ ሕግ ብቻ እንዲዳኙ ካስፈለገም የቢሊዮኖችን ሕይወት የሚመለከተው ቫይረስ አልባ የቫይረሱን መኖር የማያሳይ ምርመራ ወይም የውጤት አተረጓጐም ልዩነት የመሳሰሉት እውነታዎች በጥቂቶች ዘንድ ተዳፍነው መቅረት ባልተገባቸው ነበር፡፡ በተለይ የጤና ሚኒስቴር ለዜጐች ጤና ለሃገር ብልፅግና ከሚለው መርሁ አንፃር አቋሙን እንደሚገልፅልን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ምክንያቱም ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት ድርጅት እና ክሬቲቭ ዲያግኖስቲክ እንደሚሉን በኮቪድ-19 ምርመራ ቫይረሱ በሌለበት ጭምር ሳርስ እና ሌሎች የኮሮና ቫይረሶች፣ የእንፍሉዌንዛ እና ባክቴሪያ አመጣሽ የመተንፈሻ አካል የጤና ችግሮች ጭምር ፖዚቲቭ ውጤት ሊከሰት ከመቻሉ አንፃር ምናልባትም ከአንግዲህ በኋላ የሳንባ ችግሮች ሁሉ የስያሜ ለውጥ አድርገው በኖቭል ኮሮና ጥላ ስር የሚመደቡበት ጊዜ እምብዛም ሩቅ አልመሰለኝምና ነው፡፡ “መፍራት ያለብን አንድ ነገር ቢኖር ፍርሃትን ብቻ ነው” በሚለው የኘሬዝዳንት ሩዙቬልት አባባል ልሰናበት፡፡