Connect with us

የውሃ ፋብሪካዎቻችን እያገዙን ወይስ እየበዘበዙን?

የውሃ ፋብሪካዎቻችን እያገዙን ወይስ እየበዘበዙን?

ኢኮኖሚ

የውሃ ፋብሪካዎቻችን እያገዙን ወይስ እየበዘበዙን?

የውሃ ፋብሪካዎቻችን እያገዙን ወይስ እየበዘበዙን? | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

ቴሌቪዥኑን፣ ሬድዮኑን፣ ሶሻል ሚዲያውን… ስትከፍተው የምታገኘው መልዕክት ‹‹እጅህን ታጠብ›› የሚል ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የቤትህን በር ስትከፍተውም አጥርህ ላይ ‹‹እጃችሁን በመታጠብ ኮሮናን ይከላከሉ›› የሚል ባነር ተስቅሎ ይጠብቅኻል፡፡ በመሆኑም አንድ ነገር ከሚከፈቱ ነገሮች ሁሉ አንድ ነገር ስትከፍት ብቻ ነው ይሄን መልዕክት የማታገኘው፡፡
ቧንቧህን!!

እናት ኢትዮጵያ እንዲህ ናት እኮ፡፡ ውሃውን አጥፍታ ነው ‹‹ታጠብ›› የምትልህ፡፡ እህሉን ነስታ ነው ስለአበላሉና አበሳሰሉ የምታስረዳህ፡፡ (ያም ሆኖ ግን በበሽታ መሞት የለብህምና እጅህን በሳኒታይዘር ማጽዳትህን እንዳትረሳ፡፡)

አሁን አሁንማ የለገዳዲ ውሃ የሚመጣበትን ቀን ከመጠበቅ ይልቅ ዝናብ የሚጥልበትን ቀን መጠበቅ ሳይቀል አይቀርም፡፡ በተለይ ደግሞ የኮንዶሚንየም ሳይቶች ላይ ያለው ስቃይ አያድርስ ነው፡፡ ሽንት ቤቱ የተገነባው መኖሪያ ቤቱ መሃከል በመሆኑ ኮሮና እንዳይዝህ ቤትህን ዘግተህ በጉንፋን ስትሰቃይ ትከርማለህ፡፡ ከዚያም ከብዙ ጥበቃ በኋላ በቧንቧ ውሃ የመጣ እለት የኮሮና መድሃኒት የተገኘ ይመስል የኮንዶሚንየም ሳይቱ በደስታ ጩኸት ይደበላለቃል፡፡

የሚገርመው ነገር ታዲያ ውሃ ለረዥም ጊዜ መጥፋት የጀመረው ከኮሮና ክስተት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ የምኖርበት ሳይት ላይ ከወራት በፊት ቢያንስ በሶስት ቀን አንዴ ይመጣ ነበር፡፡ አሁን ግን ሳምንት ሙሉ ላይመጣ ይችላል፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ከቤትህ ስትወጣ ሰፈሩና መደብሩ በፋብሪካ ውሃ ተጥለቅልቆ ታገኘዋለህ፡፡ ከመኖሪያ ቤትህ የነጠፈው የቧንቧ ውሃ በኮዳ ታሽጎ ሱቁኑንና መኪናውን አጨናንቆት ታያለህ፡፡

ስለሆነም ገንዘብ ኖረህም አልኖረህም ከልጆችህ ወተት በላይ የቤተሰብህን ጤንነት በማስቀደም ሁለት ሊትር ውሃ በ 15 ብር አንድ ጃር ውሃ በ50 ብር ገዝተህ ወደ ቤትህ ትወስዳለህ፡፡

እንደሚታወቀው ኮሮና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ የሚገኝ በሽታ ነው፡፡ ኢንዱስትሪንና ሠራተኛን፣ ሆቴሎችንና ተስታናጋጆችን፣ አየር መንገዶችንና ተጓዦችን፣ ድርጅቶችንና ደንበኞቻቸውን ነጣጥሎ ሁሉንም ሥራ ፈት በማድረጉ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ አንዳንድ ባለሃብቶች ይሄ በሽታ እስኪያልፍ ድረስ ድርጅታቸውን ‹‹ለማገገሚያነት ተጠቀሙበት›› ብለው ለመንግሥት ሲሰጡ አስተውለናል፡፡

ይህ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ግን የውሃ ፋብሪካዎቻችንን አይመለከትም፡፡ አረቡ ዓለም ላይ የነዳጅ ዋጋ ሲያሽቆለቁል በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የውሃ ፋብሪካዎች ግን ‹‹የለገዳዲን ውሃ አጥፍቶ ኮሮናን ያመጣላቸውን›› ዘመን እያመሰገኑ እሽግ ውሃቸውን በመቸብቸብ ላይ ይገኛሉ፡፡

በበኩሌ ግን ኮሮናን ለመከላከል ከምንም ነገር በላይ ውሃ አስፈላጊ እንደ መሆኑ መጠን እኒህ ፋብሪካዎች ከገንዘብ ትርፍ በላይ ሕዝብ ለማትረፍ መጣር አለባቸው›› ባይ ነኝ፡፡ የቡሬ ውሃ ፋብሪካ ከግል ጥቅሙ ይልቅ የህብረተሰቡን ጥቅም በማስቀደም ፋብሪካውን የአካባቢውን የውሃ ችግር ለመፍታት እንዳዋለው ሁሉ ሌሎቹም ፋብሪካዎች ተመሳሳዩን ማድረግ አለባቸው›› ባልልም የተወሰነ የዋጋ ማስተካከያ ግን ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

ያለንበት ወቅት የምንረዳዳበት እንጂ አንድ ሊትር ውሃ በአሥር ብር እየሸጥን ትርፋችንንና ገባያችንን የምናስቀጥልበት አይደለም፡፡ ስለሆነም ሥራ በመጥፋቱ የተነሳ የሕብረተሰቡ የመግዛት አቅም ሲዳከም ሥራ የደራላቸው የውሃ ፋብሪካዎቻችን ዋጋቸውን ቀነስ፣ አቅርቦታቸውን ጨመር በማድረግ ትርፋቸውን ማስቀጠል ስለሚችሉ ይሄን መንገድ ቢከተሉ ጥሩ ይመስለኛል፡፡

መንግሥታችንም ቢሆን አቅርቦቱ እየቀነሰ የመጣውን የለገዳዲን ውሃ ማስተካከል ባይቻለው እንኳን እየተስፋፋ በሚገኘው የውሃ ገበያ ላይ እጁን በማስገባት ለአቅራቢዎቹ ‹‹ውሃና ወተት ይለያያሉ›› የሚል ምክር ቢሠጣቸው ደግ ነው እላለሁ፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top