“ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ካደረግን የመከራው ጊዜ ያጥራል” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ
ማድረግ ያለብንን ሁሉ ካደረግን በኮሮና ተህዋስ የመጣው መከራ እንደሚያጥር፤ ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን የመከራው ጊዜ እንደሚረዝም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ።
የትንሣኤ በዓልን አስመልክቶ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ትናንት ባስተላለፉት የእንኳን አደርሳችሁ መልዕክት እንዳስታወቁት “አሁን ያለንበት ጊዜ ከሐሙስ ምሽት እስከ ቅዳሜ እኩለ ሌሊት ያለውን የክርስቶስን የመከራ ሰዓት ይመስላል።
ለእኛም ጊዜው የወረርሽኝ፣ የብዥታና የጥርጣሬ ጊዜ ነው። ጽናትና ጥንካሬያችን፤ መልካምነታችንና ተባባሪነታችን፤ አንድነትና ወንድማማችነታችን የሚፈተንበት ወቅት ነው።” ብለዋል።
በዚህ ወቅት ማድረግ የሚገባንን ካደረግን በተህዋሲው የመጣ መከራ የሚያጥር ሲሆን ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን የመከራ ጊዜው እንደሚረዝም ገልፀዋል።
አሁን ከገጠመን በላይ እንዳይገጥምን፣ እንደ መንግሥትና እንደ ህዝብ እንደ አንድ ልብ መክረን እጅ ለእጅ ተያይዘን ለተግባራዊነቱ መጽናት ይኖርብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትንሣኤ የተማርናቸውን ትምህርቶችም በኮቪድ 19 የገጠመንን ፈተና ልንጠቀምበት ብንችል ውጤታማ እንሆናለን ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ለኮሮና ተህዋስ በሚገባ ከተዘጋጀን ያለከባድ ጫና ልንወጣው እንችላለን። ፈተናውን የምናልፈው በዝግጅታችን መጠን፣ ለተግባራዊነቱ በምናሳየው ጽናት ልክ ነው። የምንታገለው እንዲያልፍ ብቻ ሳይሆን ወረርሽኙ በብዙ ሳይጎዳን የህማማቱ ጊዜ አልፎ ትንሣኤው እንዲቀርብ ነው።
“አንዳንዶች፤ የተነገራቸውን ይረሳሉ። ሌሎች ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ስህተት ይሠራሉ። የሚወራ ወሬ ከእውነታው በልጦ ይወስዳቸዋል። አንዳንዶችም የለንበትም ብለው ጥለው ይሸሻሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ “ከዚህ በተቃራኒው ያሉት ደግሞ እስከ መጨረሻው ፀንተው ይገኛሉ። በሐሰተኛ ወሬ ሳይበገሩ ከእውነት ጋር ፀንተው ይቆማሉ። አንዳንዶች ጣት በመጠቆምና በፀያፍ ቃላት በማንቋሸሸ ሲጠመዱ ሌሎች ከመከራው ቀንበር ለመሸከም ትከሻቸውን ያዘጋጃሉ። አንዳንዶች እንደ ይሁዳ ከእንግልቱ ለማትረፍ ሲሞክሩ ሌሎች የህዝቡን መከራ ለመካፈል ይመጣሉ” ብለዋል።
አቅማቸው እየፈቀደ እጃቸውን የሰበሰቡ ሰዎች ተረስተው ሲቀሩ ተገቢውን ነገር በተገቢው ጊዜ ያደረጉት ሰዎች ታሪካቸው በመልካም እንደሚነሳም ጠቅሰዋል። ዛሬ በታሪክ አጋጣሚ ለዘመናት ስማችን ከመልካም ወይም ከክፋት ጋር ተያይዞ እንዲነሳ ታላቅ የታሪክ አጋጣሚ ላይ ደርሰናልም ብለዋል።
አሁን ያለንበት ጊዜ ወቅቱ የሚፈልገውን ሥራ በተገቢ ቦታና ሰዓት አከናውነን ተጋድሎአችንን በድል ለመወጣት መወሰን ያለብን ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን። ዛሬ መናገር ያለብንን እንናገር። ዛሬ ለሌሎች ማድረግ ያለብን እናድርግ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 11 ቀን 2012 ዓ.ም