Connect with us

ያደፈጠው ኮሮና በበዓል እንዳያንሠራራ

ያደፈጠው ኮሮና በበዓል እንዳያንሠራራ

ነፃ ሃሳብ

ያደፈጠው ኮሮና በበዓል እንዳያንሠራራ

ዓውድ ዓመት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ልዩ ቦታ ያለው ሲሆን፤ ገና በበዓሉ ዋዜማ በየቤቱ ቄጤማው ተጎዝጉዞ ዕጣን ከርቤው ሲጨስ ልዩ ቃናና ትዝታ አለው። ሬዲዮኑና ቴሌቪዥኑ በአውደ ዓመት ሙዚቃ በዓሉን ያደምቁታል። መንገዱ በሰው ይሰክራል። የበጉ፣ የዶሮው የከብቱ፣ የቄጤማው ገበያ በአያሌው ይደራል።

በአጠቃላይ በዓውደ ዓመት ዘመድ አዝማዱ፣ ወዳጅ ጎረቤቱ ተጠራርቶ፣ ቡናው ተፈልቶ ብሉልኝ ጠጡልኝ እየተባባለ በጋራ ሲበላና ሲጠጣ የበዓሉ መዓዛና ድባቡ ከዚህም ከዚያም ቀልብን ይሰርቃል፣ መልካም ጠረኑ አፍንጫን ያውዳል።

ይህ የዓውደ ዓመት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ጎልቶ ከሚታይባቸው ኃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የትንሣኤ (የፋሲካ) በዓል ነው።

ዘንድሮም ለሚከበረው በዓል ክርስቲያኑ እንደወትሮው በዓሉን ለማድመቅ የሚውሉ የተለያዩ ግብዓቶችን ለመሸመት ወደ ገበያ ሲወጣና ከወዳጅ ዘመድ ጋር ሲጠያየቅ ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆንና በአገሪቱ የቫይረሱ ስርጭት ተስፋፍቶ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ምን ዓይነት ጥንቃቄዎችን ሊወስድ ይገባል ስንል የተለያዩ የጤናና የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን አነጋግረናል።

የህብረተሰብ ጤና ሲፔሻሊስት ሐኪምና በኢትዮጵያ የግል ጤና ድርጅቶች አሠሪ ማህበር ሊቀመንበር ዶክተር መኮንን አይችሉህም እንደሚሉት፤ ወረርሽኙ በቀላሉ የሚሰራጭና ክትባትም ሆነ መድሃኒት በወጉ ያልተገኘለት በመሆኑ፤ ቫይረሱ እያስከተለ ካለው የጤና ቀውስ ባሻገር የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በመግታት በዓለም ላይ ከፍተኛ ማህበራዊ ሥነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል።

ኮቪድ-19 ከሩቅ ምሥራቅ እስከ አውሮፓ ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ ኃያላን የሚባሉትን አገሮች እያሽመደመደ እንደሚገኝ ጠቁመው ለአብነት በቫይረሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዜጎቻቸውን ህይወት የተነጠቁ እንደ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ እስፔንና ኢራን የመሳሰሉ አገራት የህክምናው ማማላይ በደረሰ ጥበባቸውና ቴክኖሎጂያቸው በመታገዝ በቫይረሱ ለተጠቁ ዜጎቻቸው ድጋፍና ህክምና ቢያደርጉም ቅድመ መከላከሉ ላይ ባለመሥራታቸው ቫይረሱ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖባቸዋል። አሁንም በየዕለቱ አያሌ ቁጥር ያለው ዜጎቻቸው እያለቁ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዶክተር መኮንን የዓለም ኃያላን አገራት የረቀቀ የህክምና መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂ የዳበረ የህክምና ጥበብ ያለው ባለሙያ ባለቤቶች ቢሆኑም ቅሉ ወረርሽኙን መቋቋም አቅቷቸው እጅ ወደ ላይ ብለዋል። ስለዚህ በነዚህ አገሮች ተሞክሮ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ቀድሞ መከላከሉ ላይ በጥብቅ መሥራት ካልቻሉ በጣም አነስተኛ የሆኑ የህክምና መሣሪያዎችና ኋላቀር ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ባሉበት ሁኔታ በቫይረሱ ለተጠቁ ሰዎች ድጋፍና ህክምና በመስጠት ህይወታቸውን መታደግ አዳጋች እንደሚሆን ይናገራሉ።

በቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ ከተጠቁ አገራት መማር የሚገባውም በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችን አክሞ ማዳን ውጤታማ መንገድ ስላልሆነ ትልቁ ዕድል ቀድሞ የመከላከል ሥራው ላይ መረባረብ ነው። ስለዚህ ቫይረሱ በኢትዮዸያ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም መገኝቱ ከተረጋገጠ ጀምሮ እየተከናወነ ያለው ከፍተኛ የቅድመ መከላከልና ማህበረሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ህብረተሰቡም መዘናጋት እንደሌለበት የጤና ባለሙያው ያሳስባሉ።

መጪውን የትንሣኤ (ፋሲካ ) በዓል ለማክበር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለመሸመት በነቂስ ወደ ገበያ የምንወጣና ከዘመድ አዝማድ እንዲሁም ጎረቤት ጋር በቸልተኝነት የምንጠያየቅና የምንገናኝ ከሆነ፤ ከፍተኛ አካላዊ ንክኪ ስለሚኖር በአገሪቱ የቫይረሱ ሥርጭት ተስፋፍቶ በአውሮፓና አሜሪካ የሰው ህይወት እንደቅጠል እንደረገፈው ሁሉ በእኛም ላይ ተመሳሳይ ችግር የማይመጣበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር አስጠንቅቀዋል።

ህብረተሰቡ በበዓሉ ሳይዘናጋ የጤና ባለሙያዎች የቫይረሱ ሥርጭት እንዳይስፋፋ እየሰጡ ያሉትን የጥንቃቄ መልዕክት በመተግበርና ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንቃቃ መሆን እንደሚገባ ዶክተር መኮንን አሳስበዋል፡፡

“ህብረተሰቡ በዓሉን ከዚህ ቀደም በሚያከብረው መንገድ ገበያ በነቂስ ወጥቶ በመገብየት ዘመድ ጎረቤቱ ተጠራርቶ በጋራ በመብላትና በመጠጣት ለማክበር ከተዘጋጀ የህይወት ዋጋ እንደሚያስከፍለን ማወቅ ያስፈልጋል፤ ሁሉም ሰው በዓሉን ቀለል ባለና ለወረርሽኙ ተጋላጭ በማይሆንበት መንገድ ሊያከብር ይገባል” ብለዋል።

በተለይ በትንሳኤ (ፋሲካ) በዓል በዛ ብሎ ከብት በማረድ ሥጋ የመቃረጥ ባህል መኖሩን አውስተው፤ ሰዎች ሥጋ ለመከፋፈል በብዛት ሲሰበሰቡ ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ ማድረግ፤ ከተቻለም በየመንደሩ የሚደረጉ ዕርዶችን በመተው የጤና ቀውሱን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የጤና ባለሙያዎች የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ህብረተሰቡ አብስሎ መመገብ እንደሚገባው አበክረው የሚመክሩ ሲሆን፤ ያልበሰሉ የእንስሳት ተዋጽኦ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እንደሚያጋልጡ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ በበዓሉ እነዚህን ምግቦች ሲጠቀም አብስሎ መመገብ እንደሚገባው አሳስበዋል።

በአጠቃላይ ህብረተሰቡ የተጋረጠበትን በህይወት የመኖርና ያለመኖር አደጋን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነገ ከነገ ወዲያ በህይወት ከቆየ በዓሉን በተሻለ መንገድ ሊያከብረው እንደሚችል አውቆ፤ ቢቻል ቀለል አድርጎ ዕለቱን አስቦ በመዋል በቤቱ ከአካላዊ ንክኪ ተጠብቆ ሊያሳልፍ ይገባል።

እንደ አገር የሰዎችን ህይወት ከሞት ለመታደግ ያለው አንድ ዕድል የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ መከላከል ብቻ ነው፤ መንግሥት ብቻውን ምንም ማድረግ ስለማይችል ሁሉም አካላት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው እርብርብ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። የፀጥታ ኃይሉም የተሰጠውን ኃላፊነት በሚገባ መወጣት አለበት ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ዶክተር ተኬ አለሙ በበኩላቸው፤ በበዓል የቅርጫ ሥጋ፣ በግ፣ ዶሮ፣ ዳቦ፣ ጠላና ሌሎች ምግቦችን በአንዴ መጠቀም የተለመደ ባህል ነው። ነገር ግን ይህን ከሰው ላለማነስ በሚል በአንዴ ያለዕቅድ ወጪ የሚያስወጣ፣ የምግብ ብክነትና ብልሽትን የሚያስከትል በመሆኑ፤ ህብረተሰቡ ከዚህ አስተሳሰብ ወጥቶ ለበዓሉ መዋያ የሚሆን ግብዓቶችን ቀድሞ በትንሹ ገዝቶ በማስቀመጥ ከገበያ ግር ግር መራቅና እራሱን ከቫይረሱ መጠበቅ እንደሚገባው ተናግረዋል።

አሁን ላይ በአገሪቱ ከተጋረጠው የጤና ቀውስ አንፃር ቀደም ሲል ህብረተሰቡ አርዶና ጠምቆ ከሚያከብርበት መንገድ ወጣ ብሎ ቤት ያፈራውን አሰናድቶ ቀለል አድርጎ በዓሉን አስቦ መዋል እንደሚገባ ገልፀው፤ ሁሉንም በዚህ ወቅት ካልገዛሁ በሚል የሚፈጠር የገበያ ግርግር የቫይረሱ ስርጭት ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ ስለሚችል ህብረተሰቡ በቤቱ ተወስኖ መዋል ይገባዋል ብለዋል።

በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ለበዓል መዋያ ለመሸመት በነቂስ ወደ ገበያ በሚወጣበት ወቅት የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ፤ መንግሥት የተለያዩ ግብዓቶችን በሸማቾችና መሰል አደረጃጀቶች በኩል በየመንደሩ ቢያቀርብ፤ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ሰዎች በግተራ ወጥተው የገበያ ግር ግር ከሚፈጥሩ በቤታቸው ከሱፐር ማርኬቶች ግብዓት እንዲቀርብላቸው ቢያደርጉ፤ ጎረቤት ለጎረቤት ያለው ለሌለው በማካፈል ሰው በቤቱና በአካባቢው ተወስኖ ለቫይረሱ ተጋላጭነቱን ቀንሶ እንዲውል ህብረተሰቡ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ዶክተር ተኬ ገልፀዋል።

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2012

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top