ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከያ የሕክምና መሣሪያዎች ማከፋፈያ ማእከል ሆና መመረጧን የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘጠኝ ቀናት ውስጥ መሣሪያዎቹን ለ50 የአፍሪካ አገሮች እንደሚያደርስም ገልጿል።
በዓለም በወረርሽኝ መልክ የተከሰተው ኮቪድ-19 በኢኮኖሚ በበለፀጉ አገሮች ጉዳቱ እየጨመረ መጥቷል። በአፍሪካም የሥርጭቱ መጠን እየጨመረና ሞትም እየተመዘገበ ይገኛል።
የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ባወጣው መረጃ እስካሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን 900 ሺህ መብለጡን ያሳያል። ከነዚህም ውስጥ 15 ሺህ 346 በአፍሪካ ይገኛሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡት ከ119 ሺህ ሲበልጥ፤ በአፍሪካ በወረርሽኙ የሞቱት ሰዎች ቁጥርም ከ830 ማሻቀቡን መረጃው ያሳያል።
በአፍሪካ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ባደረጉት ጥረት የዓሊ ባባ ፋውንዴሽኑ መስራች ጃክ ማ የተለገሱት የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ተሰራጭተዋል።
አየር መንገዱም ድጋፉን ለአፍሪካ አገሮች በማድረሱና በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ የሚያስተናግድበት መጋዘን ባለቤት በመሆኑ አገሪቱ የስርጭቱ ማዕከል ሆና መመረጧን በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ ዶክተር ቦሪማ ሳመቡ ገልጸዋል።
ድርጅቱ ለወረርሽኙ በሚሰጠው ዓለም አቀፍ ምላሽ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሰራጨት አዲስ አበባ የስርጭቱ ማዕከል እንድትሆን መመረጧን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎና ሎጀስቲክ ኃላፊ አቶ ፍፁም አባዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል ባደረገችው ዝግጅት ቀዳሚና ተመራጭ መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን በመመረጧ ለአገሪቱና ለኢትዮጵያውያን ስኬት መሆኑን ገልጸው፡ ድርጅቱ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያገኝበት አመልክተዋል።
አየር መንገዱ 200 ቶን የሕክምና መሣሪያዎች ለ50 አገሮች እንደሚያደርስም ኃላፊው ገልጸዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ስቴቨን ዌር ኦማሞ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቱ የስርጭቱ ማዕከል እንድትሆን በመፍቀዱን አመስግነዋል።
የአፍሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ ኦግዊል፣ ድርጅቱ ለአፍሪካ ያደረገው ድጋፍ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል ባደረገችው ዝግጅት የአፍሪካ ኩራት ናት ብለዋል።
ምንጭ:- ኢዜአ