አብዲ ኢሌ ለኢትዮጵያ ሹማምንት ትህትናን ያስተማሩት መሪ፤
ሸክም ውርድት ሳለ የመጀመሪያውን ኩንታል ለተሸከሙት አብዲ ኡመር መሐመድ አርአያ ሆነው ብዙ አፍርተዋልና እናመሰግናለን፡፡
ከስናፍቅሽ አዲስ
ያኔ ሸክም የሚናቅ ሲሆን በለስልጣናቱ በሙሉ ሱፍ ለብሶ መንጎማለል እንጂ እንዲህ ኩንታል መጫን የሚያዋርድ ተግባር ነው ብለው ያምናሉ፡፡
አብዲ ኢሌ በብዙ ጉዳዮች ችግር አለባቸው ተብሎ ቢነገርም፤ በአንዳንድ ተጨባጭ ጉዳዮች ደግሞ ቢኮነኑም የማይታሙበት አንድ ነገር ግን ህዝባዊ ለመሆን ያደረጉት ጥረት በዘመኑ ሌላ መሪ ያልደፈረው ተግባር ነበር፡፡
አብዲ ኢሌ ኩንታል ተሸክመው ሲያጓጉዙ ተአምር ሆኖ ብዙ ሰው በማህበራዊ ሚዲያ ተቀባበለው፡፡ ሸክም ትህትና ከሆነ የኢትዮጵያ ሹማምንት የትህትና አባት አብዲ ኢሌ ናቸው፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ እንኳን ሸክም ተሸካሚን አታሳዮኝ የሚሉ አለቆች ብዙ ነበሩ፡፡
ህዝብን ተሸክሞ ማገልገል የማስመሰል ነው የእውነት የሚለው ዛሬም ማህበራዊ ሚዲያው ላይ አከራካሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ብዙ ሰዎች ኩንታል መሸከም ፋሽን ሆናለች ሲሉ ከማድነቅ ይልቅ ይኮንናሉ፡፡ አንዳንዶች ግን ሸክሙ ሳይሆን ጉዳዩ ተሸካሚው መጨረሻው እንደ አብዲ ኢሌ እንዳይሆን የሚል ስጋት ነው ያላቸው፡፡
ህወሃት የሸክም ፖለቲካ ውስጥ የለችም፤ የህወሃት ሹማምንት ኩንታል ተጭነው አይተን አናውቅም፡፡ ምክንያቱን ባናውቅም ስንገምት ግን ወይ የሸክም ፖለቲካው ማስመሰል ነው አናስመስልም ብለው ንቀውታል፤ ወይም ደግሞ ሹመኛ አይሸከምም ይልቁንም ዛሬም የህዝብ ሸክም ነው በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል፡፡
በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ግን መሸከም ብቻ ሳይሆን ተሸክሞ ፎቶ መነሳት ፎቶ ተነስቶ በተቀጠሩ ሰዎች በኩል እናመሰግናለን ተብሎ መመስገን የዕለት ተግባር ሆኗል፡፡ እኔ ማስመሰልም ቢሆን እንዲህ ያለ አገልጋይነት የሚወደድ የሚደነቅና የሚመሰገን ነው ባይ ነኝ፡፡ የማገልገልና ዝቅ የማለት የትህትና መንፈስ ቢያንስ ትውልድን አንድ ነገር የሚያስተምር ከመሆኑም በላይ እኩል ነን የሚለው ሀሳብና መንፈስ በደንብ እንዲናኝ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
ይህም ሆኖ መረሳት የሌለበት እውነት ግን የዚህ ባህል ፈር ቀዳጅና የባለስልጣኖች ዝቅ ማለት አለብን ባይነት አብዮት አፈንጂ አብዲ ኢሌ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ ሸክም ውርደት ሳለ የመጀመሪያውን ሸክም ለተሸከሙት ለቀድሞው የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት እነሆ ፍሬ አፍርተዋል ተከታዮችዎም በዝተዋልና እንኳን ደስ ያለዎት፤ እግዚአብሔር ከእስር ያስፈታዎትና ደግሞ በቴሌቨዥን ብቻ ሳይሆን በአካልም ለማየት ያብቃዎት፡፡