Connect with us

የአዲስ አበባ አስተዳደር በሥሩ ለሚገኙ የንግድ ተቋማትና ሠራተኞች የግብር እፎይታ ሊያደርግ ነው

የአዲስ አበባ አስተዳደር በሥሩ ለሚገኙ የንግድ ተቋማትና ሠራተኞች የግብር እፎይታ ሊያደርግ ነው
Photo: Social media

ዜና

የአዲስ አበባ አስተዳደር በሥሩ ለሚገኙ የንግድ ተቋማትና ሠራተኞች የግብር እፎይታ ሊያደርግ ነው

የአዲስ አበባ አስተዳደር በሥሩ ለሚገኙ የንግድ ተቋማትና ሠራተኞች የግብር እፎይታ ሊያደርግ ነው

~ እስከ 3,200 ብር ወርኃዊ ደመወዝ የሚያገኙ ከሚያዝያ ጀምሮ ለሦስት ወራት ከግብር ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ

~ከ3,200 ብር በላይ ወርኃዊ ደመወዝ የሚያገኙ ሠራተኞች የሚከፍሉት 50 በመቶ ግብር ቀሪ ሊሆንላቸው ይችላል

~ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎች የግብር ዕፎይታው ይመለከታቸዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትና ተጓዳኝ ጉዳዮች በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ከግምት በማስገባት በሥሩ ለሚገኙ የንግድ ተቋማትና ተቀጣሪ ሠራተኞች፣ ከሚያዚያ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. ድረስ የግብር ዕፎይታ እንዲያገኙ ሊወስን ነው።

የግብር ዕፎይታው በሕግ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግም ረቂቅ የግብር ዕፎይታ አዋጅ የተሰናዳ ሲሆን፣ ረቂቅ ሕጉ ውሳኔ እንዲያገኝ ለአስተዳደሩ ካቢኔ በመጪው ሳምንት እንደሚቀርብ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በማኅበረሰቡ ላይ ከሚያደርሰው የጤና ጉዳት በተጨማሪ የቫይረሱ ሥርጭትን ለመከላከልና ለጥንቃቄ ሲባል የሚወሰዱ ዕርምጃዎች የሚያደርሱትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖችን ለመቀነስና ነጋዴዎችን በንግድ ሥራቸው ለማቆየት የሚያስችል የግብር ዕዳ ማቅለያ፣ እንዲሁም ሌሎች አስተዳደራዊ መፍትሔዎችን ግብር ከፋዮች እንዲያገኙ የከተማው ገቢዎች ቢሮ ረቂቅ ሕግ አዘጋጅቷል።

የገቢዎች ቢሮ ይህንን ረቂቅ ሕግ ያሰናዳው በከተማ አስተዳደሩ ማቋቋሚያ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 አንቀጽ 11 ድንጋጌን የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 51 ድንጋጌን፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ አዋጅ ቁጥር 51/2009 መሠረት በማድረግ እንደሆነ ረቂቅ የሕግ ሰነዱ ይገልጻል።

የግብር ዕዳ ማቅለያ ረቂቅ ሕጉ የተዘጋጀው በወረርሽኙና በተጓዳኝ ምክንያቶች እየተፈጠረ የሚገኘው የንግድ መቀዛቀዝ የሚያደርሰውን ጉዳት፣ በተለይ በዝቅተኛ ገቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነጋዴዎች ኪሳራን እንዲቋቋሙና በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ እንዲቆዩ ለማድረግ፣ እንዲሁም በሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ መሠረታዊ የፍጆታ አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም ለማስቻል ታስቦ ነው።

በዚህም መሠረት በከተማ አስተዳደሩ ሥር በሁሉም የታክስ ደረጃ (ማለትም በደረጃ ሀ፣ ለ እና ሐ ) የሚገኙ ግብር ከፋዮች ከሚያዝያ 1 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የግብርና የታክስ ዕዳ ማቅለያ እንዲያገኙ፣ በተረቀቀው ሕግ በዝርዝር ቀርቧል። የግብር ማቅለያው ለሦስት ወራት የሚቆይ ሆኖ በረቂቁ የቀረበ ቢሆንም፣ የወርሽኙ ሁኔታ እየታየ እንደ ሁኔታው ሊራዘም ወይም ሊሻሻል እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል።

በዚህም መሠረት በከተማ አስተዳደሩ የገቢዎች ቢሮ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ምድብ ውስጥ የሚገኙ ጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ተቋማት፣ ከሚያዝያ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሚያገኙት ገቢ ላይ መክፈል የሚጠበቅባቸው የንግድ ትርፍ ግብርና ተርን ኦቨር ታክስ ነፃ (ቀሪ) እንዲሆንላቸው በረቂቅ ሕጉ ድንጋጌ ተካቶ ቀርቧል።

በተጨማሪ ዘንድሮ ወደ ታክስ መረቡ የገቡ በቀን ገቢ ግምት የሚከፍሉ ሆነው የቀን ገቢ ግምት ያልተገመተላቸው ማለትም እንደ የኪራይ ገቢ ግብር፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ገቢ ግብርና ሌሎች ተመሳሳይ ግብሮችን መክፈል የሚጠበቅባቸው አዳዲስ ግብር ከፋዮች፣ በቀጣዩ ዓመት በሚደረግ የቀን ገቢ ግምት እንዲከፍሉ እንዲደረግ በረቂቅ ሕጉ ተካቷል።

በዚህ የግብር ከፋዮች ምድብ ዕፎይታ የሚያገኙት ግብር ከፋዮች በቁንጅና ሳሎኖች፣ በምግብ ቤቶች፣ በባርና ሬስቶራንቶች፣ በሆቴሎች፣ በመዝናኛ ቤቶች፣ በቤትና ሕንፃ ኪራይ፣ በመኪና ማሽነሪ ኪራይ፣ በመጠጥ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሕፃናት መዋያዎች፣ በጉዞ ወኪሎች፣ በመኝታ አገልግሎቶችና በትራንስፖርትና መሰል ዘርፎች የተሰማሩ መሆናቸውን የረቂቁ ማብራሪያ ያመለክታል።

እነዚህ የንግድ ዘርፎች በባህሪያቸው ወረርሽኙን የማስተላለፍ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር መንግሥት ሊዘጋቸው የሚችላቸው ከመሆናቸው አንፃርና ገቢያቸውም በዚያው ልክ የሚቀዛቀዝና ብሎም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው መሆኑን ከግምት በማስገባት፣ ዕፎይታውን እንዲያገኙ ታሳቢ መደረጉን ሰነዱ ያመለክታል።

በዚህ ምድብ ውስጥ የሚወድቁ የንግድ ተቋማት ብዛት 234,335 እንደሚሆን መረጃው የሚያመለክት ሲሆን፣ እነዚህ ተቋማት በሚያገኙት የግብር ዕፎይታ የከተማ አስተዳደሩ 500 ሚሊዮን ብር የሚገመት ገቢ ሊያጣ እንደሚችል ተገምቷል።

በደረጃ ‹‹ለ›› ምድብ የሚገኙ ግብር ከፋዮች በሒሳብ መዝገብ መሠረት የግብር ግዴታቸውን መወጣት ያለባቸው ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት በሚያቀርቡት ትክክለኛ ሒሳብ መዝገብ አማካይነት ግብራቸውን እንዲከፍሉ፣ ነገር ግን በወረርሽኙ ምክንያት የተሟላ የሒሳብ መዝገብ ማቅረብ የማይችሉበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል የ2012 ዓ.ም. አራተኛ ሩብ ዓመት ገቢያቸው ላይ ሊከፈል ከሚገባው የንግድ ትርፍ ገቢ ግብር ነፃ እንዲደረጉ በረቂቅ ሰነዱ ቀርቧል።

በዚህ ጉዳይ ላይም ረቂቁ የሚቀርብለት የአስተዳደሩ ካቢኔ ተገቢ ብሎ ያመነበትን አማራጭ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል። በደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች ምድብ 45,199 ግብር ከፋዮች በአስተዳደሩ ሥር እንደሚገኙ መረጃው ያመለክታል።

በደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች ምድብ 68,626 ግብር ከፋዮች የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህም በሒሳብ መዝገብ የሚስተናገዱ እንደ መሆናቸው መጠን በወረርሽኙ ምክንያት የተሟላ የሒሳብ መዝገብ ማቅረብ የማይችሉበት ሁኔታ ስለሚኖር፣ የ2012 ዓ.ም. የአራተኛ ሩብ ዓመት ገቢያቸው የንግድ ትርፍ ገቢ ግብር ነፃ እንዲሆንላቸው የሚል ድንጋጌ በረቂቁ ተካቶ ቀርቧል፡፡ በሌላ በኩል መድኃኒትና ንፅህና መጠበቂያ በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ አምራቾች በዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ለኅብረተሰቡ እያመረቱ የሚያቀርቡ እንደሆነ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ባገኙት ገቢ ላይ ሊከፍሉ ከሚገባቸው የንግድ ትርፍ ገቢ ግብር 50 በመቶ የታክስ ማቅለያ እንዲደረግላቸው በረቂቅ ሰነዱ የቀረበ ሌላው የጫና ማቅለያ ድንጋጌ ነው።

‹‹ምግብና ምግብ ነክ ምርቶችን በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ አምራቾች በዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ለኅብረተሰቡ እያመረቱ የሚያቀርቡ ሆነው የተገኙ እንደሆነ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ባገኙት ገቢ ላይ ሊከፍሉ ከሚገባቸው የንግድ ትርፍ ገቢ ግብር መቶ በመቶ የታክስ ማቅለያ ቢሰጣቸው ለኅብረተሰቡን የአቅርቦት ችግር ከመፍታት አንፃር ማበረታቻ ሊሆን ይችላል፤›› የሚል ድንጋጌም በረቂቁ ተካቷል።

የደመወዝ ገቢ ግብርን በተመለከተም ረቂቁ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን፣ በዚህ ወረርሽኝ ጊዜ በፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት መስተጓጎል የተነሳ የዋጋ ንረት ሊኖር ስለሚችል፣ ይህም በደመወዝ ኑሮቸውን በሚያስተዳድሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ቀጥተኛ ጉዳት ስለሚያስከትል ማቅለያዎች እንዲደረጉ ሐሳብ ቀርቧል። በዚህም መሠረት የወረርሽኙ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ በመመሥረት ወርኃዊ ግብር የሚከፈልበት ደመወዝ ገቢ ከ3,200 ብር በታች የሚያገኙ ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ ከደመወዝ ግብር ነፃ እንዲሆኑ፣ ወርኃዊ ደመወዛቸው ከ3,200 ብር በላይ የሆኑት ደግሞ 50 በመቶ ከደመወዝ ገቢ ግብር ነፃ እንዲሆኑ በረቂቁ ተካቷል።

ይህም ከሚያዚያ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ወራት በሚገኝ የደመወዝ ገቢ ላይ የሚፈጸም ሆኖ በረቂቁ የተካተተ ነው። በደመወዝ ገቢ ላይ የታሰበው የግብር ማቅለያ ተቀጣሪ ሠራተኞች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን የኑሮ ውድነት ጫና በመቋቋም ጤናቸውንና ደኅንነታቸውን እንዲጠብቁ የሚያግዝ እንደሆነ፣ ነገር ግን ለሦስት ወራት የሚደረገው የደመወዝ ግብር ምሕረት የከተማ አስተዳደሩን 1.8 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚያሳጣው ሰነዱ ያመለክታል።

ረቂቅ ሰነዱ የታክስ ተመላሾችን ለማፋጠንና ሌሎች አስተዳደራዊ ጫናዎችን የሚቀንሱ ድንጋጌዎችን አካቶ የያዘ ሲሆን፣ በቅርቡ ለአስተዳደሩ ካቢኔ ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል።(ምንጭ:-ሪፖርተር ጋዜጣ)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top