Connect with us

የጨርቅ ማስክ አስፈላጊነት…

የጨርቅ ማስክ አስፈላጊነት...
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የጨርቅ ማስክ አስፈላጊነት…

የጨርቅ ማስክ አስፈላጊነት… | (ቅዱስ መሀሉ)

የአሜሪካ የበሽታ መከላከያ እና ቁጥጥር መስሪያ ቤት(ሲዲሲ) ቀደም ሲል ሃኪሞች ወይም በሳንባ ቆልፍ የተጠረጠሩ ወይም እነሱን የሚያስታሙ ሰዎች ብቻ ማስክ ይጠቀሙ ይል የነበረውን መመሪያ ሰርዞ ዛሬ ሁሉም አሜሪካዊ የጨርቅ ማስክ እንዲጠቅም በማለት አሻሽሎታል። የጨርቅ ማስክ አስፈላጊነት አሁን በደንብ ሁሉም እየተናገረው ነው።

እኔም የሚታጠብ የጨርቅ ማስክ የሳንባ ቆልፍ በሽታ እንዳይዛመት በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ ወሳኝ መሆኑን እና ከሌሎች አማራጭ መፍትሄዎች አንጻር በመመዘን ገልጫለሁ።

አሁንም መንግስት ግራ ከመጋባት እና ከጥድፊያ ወጥቶ የሚፈለገውን ሁሉ ሳይሆን ከመፍትሄዎቹ ውስጥ በውስን አቅም ከፍተኛ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉት ላይ ብቻ ማተኮር አለበት። ማስክ በከፍተኛ ሁኔታ የበሽታውን ስርጭት፣ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራን እና ማህበራዊ ምስቅልቅልን ይታደጋል። የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ያለባቸው ከተሞች ደግሞ በራሳቸው ወጭ ለከተማው ህዝብ እና በዙሪያው ላለው አካባቢ ነዋሪዎች የሚታጠብ የጨርቅ ማስክ አምርተው ማህበራዊ ግዴታቸውን በዚህ በክፉ ቀን ሊወጡ እና ከህዝብ ጋር ሊቆሙ የግድ ነው።

ለምሳሌ የባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የአዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪ፣ የአዲ ግራት ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ወዘተ በየአካባቢው ያሉ ፋብሪካዎች ለህዝቡ በፍጥነት አምርተው የፋብሪካዎቹ በዚያ መገኘት በዚህ ክፉ ቀን ለህዝቡ ሊኖራቸው የሚችለውን ጥቅም በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል።

የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በሌለባቸው ስፍራዎች የሚገኙ ሌሎች ፋብሪካዎች እና አምራች ድርጅቶች ደግሞ ቢያንስ ፋብሪካ እና ምርታቸን ለሚያመርቱበት አካባቢ ህዝብ የሚታጠብ የጨርቅ ማስክ አስመርተው በነጻ እንዲከፋፈል ማድረግ አለባቸው።

መንግስት ደግሞ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ለህዝብ ሲሉ በሚገቡበት አዲስ ምርት ተጨማሪ ወጭ እና ስራ ለሚጠብቃቸው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ማበረታቻ በዚህ ረገድ የሚያወጡትን ወጭ ታሳቢ ያደረገ የግብር ቅነሳ በማድረግ በፍጥነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚበቃ ምርት እንዲመረት ማድረግ ይኖርበታል።

ከዚህ በተጨማሪ አስፋልት ላይ ኬሚካል የሚረጩ ከተሞች ከሚገኘው ውጤት አንጻር ይህ ድርጊታቸው ውስን የኢኮኖሚ አቅምን ማባከን እንደሆነ ተረድተው በጀቱን ለሚገኙበት አካባቢ ህዝብ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ የጨርቅ ማስክ በማስመረት ለህዝቡ በነጻ ቢያከፋፍሉ መልካም ነው።እንዴት ሊከፋፈል እንደሚችል እኔ በጽሁፎቼ አንዳንዱን መንገድ ጠቁሚያለሁ።

ርጭት ማከናወን ካስፈለገ መደረግ ያለበት አስፋልት ላይ ሳይሆን ሰዎች ቀን ቀን የሚበዙበት እንደ መናከሪያ እና ገበያዎች ያሉ ስፍራዎች ሲሆኑ እሱም ማታ ሰዎች ወደየ ቤታቸው ከገቡ እንጅ በቀትር ሰዎች እየተንቀሳቀሱ መሆን የለበትም። በዚህ ረገድ የሚረጨው ነገር ውህድ ውሎ አድሮም ሰዎችን እንደማይጎዳ በአካባቢ ጥበቃ እና በጤና ጥበቃ በባለሙያዎች ሊረጋገጥ ይገባል።

ከሳንባ ቆልፍ ወረርሽኝ አደጋ የሚያወጣን ኢትዮጵያዊ መፍትሄ ብቻ ነው። ፈረንጆቹ መፍትሄ የሚሉትን በሙሉ ኮፒ ፔስት ለማድረግ ከሞከረን ማድረግ የምንችለውንም ሳናደርግ ያለችንን አቅም አሟጠን ጨርሰን እንዲሁ ባክነን እንቀራለን። ያን ማድረግ የለብንም። ያን ካደረግን ከሳንባ ቆልፉ በፊት ብዙ ህይወትን የሚቆልፉ ማህበራዊ ምስቅልቅልን የሚያነግሱ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሰብዓዊ ውጥንቅጦች ቀድመው ሊከሰቱ ስለሚችሉ በደንብ ይታሰብበት ለማለት ነው!!

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top