Connect with us

የቀድሞ ሠራዊት አባላት ለህዳሴው ግድብ ዘብ እንቆማለን አሉ

የቀድሞ ሠራዊት አባላት ለህዳሴው ግድብ ዘብ እንቆማለን አሉ
Getty Images

ዜና

የቀድሞ ሠራዊት አባላት ለህዳሴው ግድብ ዘብ እንቆማለን አሉ

ግድቡ እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅብንን እንወጣለን

የኢትዮጵያ የቀድሞው ሰራዊት የልማትና የድጋፍ ማህበር ግብጽ ታላቁን የህዳሴ ግድብ አስመልክታ የምታሰማውን ድንፋታ አጣጣለው፡፡ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ሰራዊቱ አስታውቋል፡፡
ማህበሩ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በራስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ግብጽና የአረብ ሊግ ያሳለፉትን ውሳኔ ያጣጣለ ሲሆን፤ ግድቡን አስመልክቶ መንግስት ለሚያደርገው ጥሪ ከጐኑ እንደሚሰለፉ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሀምሳ ዓለቃ ብርሃኑ አማረ ተናግረዋል፡፡

ሰራዊቱ ማህበሩን በሲቪል ማህበርነት ያቋቋመ ቢሆንም በአገር ላይ ለሚቃጣ ማንኛውም ጉዳይ የውትድርና ሙያው በውስጡ ያለ በመሆኑ ለየትኛውም ያገር ጥሪ ፈጥኖ እንደሚደርስ አስታውቀዋል፡፡

ማህበሩ በአየር ሀይል፣ በባህር ሀይል በመደበኛና በሚሊሺያ በአጠቃላይ በአምስቱም ዘርፍ አገሩን ሲያስከብር የነበረና ኤርትራን ጨምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በ200 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የተዋቀረ ከ1. ሚ በላይ አባላትን ያቀፈ መሆኑን የገለፁት የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ አባል መቶ አለቃ ታሪኩ በቀለ፤ ሰራዊት አያረጅም፤ በጦር ግንባር፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በመረጃ ትንተናና በማማከር በኩል አገሩን የሚያገለግል የ18 ዓመት ወጣት ወኔ ያለው ሀይል ነው” ብለዋል፡፡ ለየትኛውም የድጋፍ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ሰራዊቱ ዝግጁ መሆኑን – በመግለጽ፡፡

ኢትዮጵያ ብቻ ተጠቅማ ግብፃዊያን ወንድሞቻችን በርሃብ ይለቁ አንልም፤ ነገር ግን የውሃውም የአፈሩም ባለቤት ሆነን ሳለ ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸውና አቅም ባለመፍቀዱ ሳንጠቀም ቆይተናል፤ አሁን በራስ አቅም ግንባታ ተጀምሯል፤ ተጠናቅቆ ስራ እስኪጀምር የሚጠበቅብንን እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሀገርን ጥቅም በማይጐዳ መልኩ የድርድር ጥሪ ከቀረበላት መደራደርና በሰላም መፍታት ለሁሉም ወገን አዋጪ መሆኑን የገለፁት የቀድሞ ሰራዊት አባላት ያ ካልሆነ ግን ለግብጽ ድንፋታ ምላሽ በመስጠቱ በኩል ግንባር ቀደም ተሰላፊ የሚሆን ሰራዊት በመላ አገሪቱ እንዳለ ተገልጿል፡፡

ሰራዊቱ በአሁኑ ሰዓት ከ30 ዓመት ጭቆናና አንገት መድፋት ለውጡ ታድጐት ለልማት ዝግጁ እንደሆነ የገለፁት የማህበሩ ኃላፊዎች በቀጣይ ሁለት ትልልቅ የልማት ተቋማትን ለማቋቋም በሂደት ላይ ሲሆን ተቋማቱ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ባንክና የጥበቃ ካምፓኒ መሆናቸውን ገልፀው በቀጣይ በሚዛን ሻኮ አካባቢ የዶሮና የከብት እርባታና ማደለቢያዎችን ለማቋቋም እንዲሁም በግብርናውም አመርቂ ሥራ ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ሰራዊቱ ምክር ቤት በማቋቋም በሂደት ላይ ሲሆን ሁለት ጥያቄዎችን ለመንግስት ማቅረቡን የገለፁት ሃላፊዎቹ ጥያቄዎቹም የጡረታና የህክምና ጥያቄዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመጪው ክረምት በሚደረገው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሰራዊቱ ስላለው አስተያየት ተጠይቀው ኃላፊዎቹ ሲመልሱ “ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ያሉ ሲሆን በፀጥታ፣ በምርጫ ታዛቢነትም ሆነ በጥበቃ ስራ ሊገለገልብን ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

#አዲስ_አድማስ

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top