Connect with us

ጠ/ሚር አብይ የዝኆኖቹን መኖሪያ የጨበራ ጩርጩራን ብሔራዊ ፓርክ ጎበኙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዝኆኖቹን መኖሪያ የጨበራ ጩርጩራን ብሔራዊ ፓርክ ጎበኙ
Photo: Facebook

ዜና

ጠ/ሚር አብይ የዝኆኖቹን መኖሪያ የጨበራ ጩርጩራን ብሔራዊ ፓርክ ጎበኙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጨበራ ጩርጩራን ብሔራዊ ፓርክ ጎበኙ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዳውሮ ዞን ከህዝብ ጋር ውይይት ለማድረግ ወደ ስፍራው ሲያቀኑ ከነመላው ቤተሰባቸው የዝኆኖች መኖሪያ የሆነው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ጎብኝተዋል፡፡

በብሔራዊ ፓርኩ ቆይታቸው ባለቤታቸውና ልጆቻቸው የዝኆኖች መዋያ ወደ ሆነው የፓርኩ ክፍል ድረስ በመጓዝ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ክብርት የሰላም ሚኒስትሯ ከፍተኛ የክልልና የዞን የስራ ሃላፊዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን በብሔራዊ ፓርኩ የእይታ ማማ ላይ በመሆን የጨበራን ጩርጩራን ጎሾች በቅርበት ተመልክተዋል፡፡

በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው በአካባቢው የነበራቸውን ቆይታም አስደሳች እንደነበረ ሲገልጹ ምድሩን የአናብስትና የዝኆን መኖሪያ መሆኑን ገልጸው አወድሰዋል፡፡ በተመሳሳይ የብሔራዊ ፓርኩ ሃላፊና በሀገራችን ውጤታማ የተፈጥሮ ሀብት ስራን በመስራት ትልቅ ስም ያተረፈው የብሔራዊ ፓርኩ ሃላፊ አቶ አዳነ ጸጋዬም በተመሳሳይ በፌስ ቡክ ገጹ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት የህይወቴ የደስታ ቀንና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትልቁ ምዕራፍ ሲል ገልጾታል፡፡

የድሬቲዩም ምንጮች እንደገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከብሔራዊ ፓርኩ ሃላፊ ጋር በፓርኩ ልማት ጉዳይ መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡ የውይይታቸው ነጥቦች ምን እንደሆነ ለይተን ለማወቅም ባንችልም በብሔራዊ ፓርኩ ቀጣይ ልማትና ትኩረት ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ለመረዳት ችለናል፡፡

የጨበራ ጩርጩራን ብሔራዊ ፓርክ ከዚህ ቀደም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የጎበኙት ሲሆን በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስፍራዎች ለሚሰሩት የበጎ አድራጎት ፕሮጀክት የመረጡትም ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኦሞ ነጭ ሳርና ጨበራ ጩርጩራን በመጎብኘት ቀዳሚው በአጭር ጊዜ በርካታ ብሔራዊ ፓርኮችን የጎበኙ መሪ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዜናው የተጠቀምናቸው ፎቶ ግራፎች ከብሔራዊ ፓርኩ ሃላፊ ከአቶ አዳነ ጸጋዬ ገጽ የተገኙ ናቸው፡፡

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top