የከተማዋ አስተዳድር በበኩሉ ቅጥሩ እና ፈተናው ከሰው ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ መከናወኑን ገልጿል።
ከተማ አስተዳድሩ የስራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት በሚል ከ8 ሺህ በላይ በ2010 እና 2011 የተመረቁ ወጣቶችን በተለያዩ ተቋማት ቀጥሯል።
አስተዳድሩ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት 23 ሺህ 248 ወጣቶች ተመዝግበው ፈተና የተቀመጡ ሲሆን ከተፈታኞቹ መካከል 8 ሺ 99ኙ ፈተናዉን አልፈዉ ከክፍለ ከተማ አስከ ወረዳዎች ባሉ የመንግስት ተቋማት ተቀጥረዋል።
ይሁን እንጂ የፈተናዉ አስተራረም እና የቅጥር ሁኔታዉ ግልፅ እና ገለልተኛ አይደለም በሚል በርካታ ተፈታኞች ቅሬታቸዉን ለኢትዮ ኤፍ እም ተናግረዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ዉጤታችን ተጭበርብሮብናል ለዚህ ደግሞ የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ለሙስና እና ለሌች ብልሹ አሰራሮች ተጋላጭ ነበር ይላሉ፡፡
ቅሬታቸዉን ለቢሮዉ ለማስረዳት ብዙ ጊዜ እንደተመላለሱ የሚገልፁት እነዚህ ወጣቶች የአዲስ አበባ አስተዳደር ፐብሊክ ሰረቪስ እና የሰዉ ሀብት ቢሮ ተጠባባቂ አድርጎናል፤ ነገር ግን እኛ የተሻለ ዉጤት አምጥተን ተጠባባቂ ልንሆን አይገገባም ስለዚህ መፍትሄ ይሰጠን ሲሉም አስተዳደሩን ጠይቀዋል፡፡
እኛ ካመጣነው ያነሰ ውጤት ያመጡ ተፈታኞች ስራ ተቀጥረዋል እኛ ግን ተጠባባቂ ናችሁ ተባልን ሲሉ አስተዳድሩ ስህተት እንደፈጸመ ተናግረዋል።
እኛም የወጣቶችን ቅሬታ ይዘን የአዲስ አበባ አስተዳደር ፐብሊክ ስረቪስ እና የሰዉ ሀብት ቢሮን የጠየቅን ሲሆን የቢሮዉ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ ሀድጉ ፀሃዬ ችግሩ የቢሮዉ ሳይሆን የራሳቸዉ የተፈታኖቹ ስህተት ነዉ ብለዋል፡፡
ይህም ወጣቶቹ የፈተናዉን መመሪያ ሳያከብሩ የመፈተኛ መለያ ቁጥር ሲጠየቁ እነሱ ግን ያስገቡት የመታወቂያ ቁጥራቸዉን ነበር ብለዋል፡፡
ተፈታኞቹ እንዳነሱት ከሆነ የፈተና አሰጣጡ ሂደት ግልፅ አልነበረም ፤ቢሮዉ የስራ ቅጥሩ በፍትሃዊ እና ግልፅ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ምን ምን ስራዎችን ሰርቷል ብለን ላነሳነዉ ጥያቄም አቶ ሀድጉ ከምዝገባ ጅመሮ የፈተና አሰጣጥ እና እርማት የተካሄደዉ በገለልተኛ አካል ነዉ ፈተናዉን የፈተነዉ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ነዉ ብለዋል፡፡
በፈተና ሂደት ዉስጥ የኮድ ስህተት ከነበረባቸዉ ተፈታኞች መካከል 471 ቢሮዉ ቅሬታቸዉን ተቀብሎ ተጠባባቂ እንዲሆኑ አድርጓል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የፈተና ውጤታቸው ዳግም እንዲታይ ተደርጎ በተጠባባቂነት ተይዘዋል ያሉት አቶ ሀድጉ በቀጣይ በሚኖሩ ክፍት የስራ ቦታዎች ላይ እንመድባቸዋለን ብለዋል።
ቢሮው ባወጣው መስፈርት መሰረት ፈተና አልፋችኋል ተብለው የተለዩት 8 ሺህ 99 ምሩቃን የስራ ስምሪት ስልጠና ተሰጥቷቸው ባሳለፍነው ሳምንት በከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ መመረቃቸው እና ስራ መጀመራቸው አይዘነጋም።
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን ትኩስ ዜናዎችን፣ መረጃዎች እና ሌሎች የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ስርጭቶችን ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። (ኢትዮ ኤፍኤም)