Connect with us

ኢትዮጵያ በአሜሪካው የህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ እንደማትሳተፍ አሳወቀች

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር በአሜሪካ ሊካሄድ የታሰበው ስብሰባ ላይ እንደማትገኝ አስታወቀች
Photo: Facebook

ዜና

ኢትዮጵያ በአሜሪካው የህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ እንደማትሳተፍ አሳወቀች

ኢትዮጵያ በዋሽንግተን የመጨረሻ ቀጠሮ ተይዞለት በነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀጣይ ድርድር ላይ እንደማትሳተፍ ለአሜሪካ አሳወቀች።

በአሜሪካ ዋሽንግትን ዲሲ ነገ እና ከነገ በስቲያ ሊካሄድ ታስቦ በነበረው ቀጣዩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ በሚደረገው ድርድር ላይ ኢትዮጵያ እንደማትካፈል የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቋል።

ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው የአሜሪካ መንግሥትና የአለም ባንክ በታዛቢነት በሚገኙበት የካቲት 17 እና 20/2012 ዓ.ም ከሱዳን እና ግብጽ ጋር ሊካሂድ በታቀደው ቀጣይ የሦስትዮሽ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ እንደማትገኝ አስታውቋል።

ጨምሮም በዋሺንግተን ከተማ ለሁለት ቀናት ሊካሂድ ታስቦ በነበረው የሦስትዮሽ የድርድር መድረክ ላይ ኢትዮጵያ የማትሳተፈው፤ ተደራዳሪ ቡድኑ በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት ባለማጠናቀቁ በተጠቀሰው ጊዜ በአሜሪካ በመገኘት ውይይቱን ማድረግ እንዳልተቻለ ጥሪውን ላደረገው የአሜሪካ የትሬዠሪ ቢሮ ማስታወቁን ገልጿል።

ለድርድሩ ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግብጽ የውይይቱን አቅጣጫ ከውሃ አሞላልና አለቃቅ ርዕሰ ጉዳይ በማውጣት በተለያዩ ወቅቶች ማግኘት በሚገባት የውሃ ድርሻ ላይ በማተኮሯ ሂደቱ በተፈለገው ፍጥነት ለመሄድ አልቻለም።

ግብጽ የሱዳንን ድጋፍ በመያዝ በደረቅና ድርቅ በሚያጋጥምባቸው ጊዜያት ከአባይ ወንዝ ላገኘው ይገባል ብላ ባስቀመጠችው የውሃ መጠን ላይ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችን ተቀባይነት አላገኘችም። ባለሙያዎቹ ጨምረውም በዚህ ድርድር ሱዳንና ታዛቢ የተባሉት ወገኖች ከግብጽ ፍላጎት ጎን የመቆም አዝማሚያ አሳይተዋል።

በዋሽንግተን ከተማ የተካሄደውን የመጨረሻውን ውይይት ተከትሎ ነገና ከነገ ወዲያ ይደረጋል በተባለው ድርድር ላይ ከስምምነት ተደርሶ በፊርማ መቋጫ እንደሚያገኝ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ በውይይቱ ላይ እንደማትግኝ በማሳወቋ ለሌላ ጊዜ መተላለፉ አይቀርም።

ቀደም ሲል ተደረገውን ድርድር ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ስልክ ደውለው ሂደቱ በዚህኛው ድርድር መቋጫ እንደሚያገኝ ተስፋ እንዳለቸው ተናግረው ነበር። በቅርቡም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ማይክ ፖምፒዮ አዲስ አበባ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተው ነበር።

ምንም እንኳ የመጨረሻውን ድርድር ለማድረግና ስምምነት ላይ ለመድረስ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በግድቡ ጉዳይ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት አወያይቶ ስላልጨረሰ በመድረኩ ሊሳተፍ እንደማይችል አሳውቋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ የተካሄዱት ውይይቶች ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ከ9 ቀናት በፊት በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ስላሉት የድርድር አካሄድ እና አቅጣጫ ላይ ውይይት መደረጉ ይታወሳል።

በዚያ ውይይት ላይ ሚኒስትሮች፣ የተደራዳሪ ኮሚቴ አባላት፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎችም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ግለሰቦችን በውይይቱ ተሳትፈው ነበር።

ለመገናኛ ብዙሃን ዝግ በነበረው ውይይት ላይ ኢትዮጵያ በቀጣዩ የዋሽንግትን ስብሰባ እንደማትሳተፍ ስለመወሰኑ የታወቀ ነገር የለም።

በአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ አደራዳሪነት በአዲስ አበባ፣ ካይሮ፣ ካርቱም እና ዋሽንግተን ዲሲ ሲደረጉ የነበሩት ውይይቶች ያለውጤት እንዲበተኑ የሆነው የግብጽ መከራከሪያ ነጥቦች መለዋወጥ መሆኑ ተጠቁሟል።

ቢቢሲ ለውይይቱ ቅርበት ካላቸው ባለሙያዎች እንደተረዳው ምንም እንኳን የሚካሄደው ውይይት በግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ እንዲሆን ኢትዮጵያ ጥረት እያደረገች ቢሆንም በግብጽ በኩል ድርድሩ የውሃ ድርሻ ላይ እንዲያተኩር ግፊት እያደረገች ነው።

ምንጭ:- የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፣ ቢቢሲ

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top