ንጽሕናን የመፍጠሪያ ንጹሕ ያልሆነ መንገድ | (ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት)
በድንቁርና የተያዘ ሐሳብና በአላዋቂ እጅ የተያዘ መድኃኒት ሁለቱም አደገኞች ናቸው፡፡ አላዋቂዎች የሰውን ልጅ የሺዎች ዘመናት የመስተጋብር ታሪክ ይረሱታል፡፡ ይሄንን ረስተው ‹ንጹሕ› ሕዝብ ሊፈጥሩ ይቃጣቸዋል፡፡ ከማንም ያልወረሰ፣ ለማንም ያላወረሰ፣ ከማንም ያልተዛመደ፣ ማንንም ያልገዛ፣ በማንም ያልተገዛ፣ ማንም ያልመጣበት ወዴትም ያልሄደ ሕዝብ ለመፍጠር ይሻሉ፡፡ ፈጣሪ እንዲህ ዓይነት ሕዝብ አልፈጠረም፡፡ ስለዚህም እየፈጠሩ ሳይሆን እያፈረሱት ነው የሚሄዱት፡፡ ይሄ ‹ንጹሕ› ሕዝብ የመፍጠር ንጹሕ ያልሆነ ሐሳብ ነው፡፡
በየትኛውም የሰው ማኅበር ውስጥ ሌላ ወገን አለ፡፡ እንኳን ኩታ ገጠም ሆኖ በኖረ ሕዝብ መካከል በአሜሪካ፣ በካናዳና በአውስትራልያ ነባር ሕዝቦች ውስጥ አፍሪካዊ ዘር አለ፡፡ ከነጮች በፊት አፍሪካውያን ሰሜንና ደቡብ አፍሪካን ኖረውበታል፡፡ በኢትዮጵያውያን ዝርያ ውስጥ ዓረብነት፣ ይሁዲነት፣ አፍሪካዊነት፣ እስያዊነት መኖራቸው የዲኤንኤ ምርመራዎች አሳይተዋል፡፡ የትኛውም ቋንቋ ሳይወራረስ አልኖረም፡፡ እንግሊዝኛ 29% ከላቲን፣29% ከፈረንሳይ፣26% ከጀርመን፣ 6% ከግሪክ፣ 10% ከሌሎች ቋንቋዎች ወስዷል፡፡
የአማርኛ ቋንቋን ያየን እንደሆነ ሴማዊ ጠባያትን ከኩሻዊ ጠባያት ጋር አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ እንዲያውም ኢትዮ ሴማዊ ቋንቋዎችን ያጠኑ (እንደ ሌስላውና፣ ባየ ይማም) ሊቃውንት በሴማውያን ቋንቋዎች ላይ የበዛ የኩሻዊ ቋንቋዎች ተጽዕኖ እንደሚገኝ ይገልጣሉ፡፡ በግእዝ የምናውቀው ‹ዶርሆ› የሚለው ቃል ከኩሽቲክ ቋንቋዎች በውሰት የመጣ እንጂ ሴማዊ አለመሆኑ ይነገራል፡፡ ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ወሳኙን አስተዋጽዖ ያደረጉት ታላላቅ ሊቃውንት አማርኛ ሁለተኛ ቋንቋቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ሕዝቦች ዛሬ በስም የምናውቃቸው ብቻ አይደሉም፡፡ ስማቸውን በታሪክ መዝገብ፣ ሥልጣኔያቸውን በኢትዮጵያ ሥልጣኔ፣ ደማቸውን ደግሞ ዛሬ ባሉት ሕዝቦች ውስጥ አሥርጸው የጠፉ ሕዝቦችም አሉ፡፡ ጋፋት፣ ቄዳ፣ ዳሞት፣ ወረብ፣ ከነዚህ መካከል ናቸው፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በወለጋ የነበሩ ጥንታዊ ሕዝቦችን በዶክትሬት ዲግሪ ጥናታቸው ዘርዝረዋቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ ሕዝብ፣ ሌላ ቋንቋ፣ ሌላ ታሪክ በባህሉ ውስጥ ያላለፈ ‹ንጹሕ› ሕዝብ ከማግኘት የሉሲን የሠርግ ካርድ ማግኘት ይቀላል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ነባር ስሞችን በመቀየር ይሄንን ታሪክ ለማጥፋት የሚመኙ ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የግዛታቸው ኃያልነት ማሳያ ይመስላቸዋል፡፡ ሁለቱም ስሑት መንገድ ነው፡፡ ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲሄዱ ጥንታዊ ቦታቸውን ማስታወስ ይፈልጋሉ፡፡ የአሜሪካና የካናዳ ከተሞች ስሞች በአውሮፓ ከተሞች ስያሜዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ ሰው ትዝታውን መርሳት ስለማይፈልግ፡፡ በአዲስ አበባኮ ወሎ ሠፈር፣ ሼሕ ሆጀሌ ሠፈር፣ ጎጃም በረንዳ፣ ወለጋ ሠፈር፣ ሲዳሞ ሠፈር፣ ዝም ብለው አልመጡም፤ የትውስታ ቦታ የመፍጠር ሂደት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ቅርስ የሕዝቦችን መስተጋብር የሚያሳይ ህያው ታሪክ በመሆኑ ለንብረት መተው ነበረበት፡፡ የሌሎች ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና ባህል የሚገኝበት ሕዝብ ብልጽግናውን እንጂ ድህነቱን አያሳይም፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የአንድን ሕዝብ ታሪካዊ ግንኙነት እንዲያመለክቱ ሆነው የሚሰየሙ ስያሜዎች አሉ፡፡ ደብረ ታቦር፣ ኤፍራታ፣ አርማንያ፣ ግብጻዊት፣ ደብረ ዘይት፣ ናዝሬት፣ ደብረ ሲና፣ ኢትዮጵያዊ ስያሜዎች አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር የነበራትን ሃይማኖታዊ ግንኙነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በሮሐ ላሊበላ አካባቢም ኢትዮጵያ ከዓረቡ ዓለም ጋር የነበራትን ግንኙነት የሚያሳዩ የአካባቢ ስሞች አሉ፡፡
በኢትዮጵያውያን ስያሜዎች ውስጥ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች፣ የእሥራኤልና የዓረብ ስሞች በብዛት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ስሞች የእምነትንና የባህልን ግንኙነት ቢያሳዩም ከዚያም ግን ይሻገራሉ፡፡ ባሕራን ዓረብኛ ነው ግን የክርስቲያኖች ስም ነው፡፡ አዱኛ ኦሮምኛ ነው፡፡ በአማራ ክልል ግን በብዛት የተለመደ ስም ነው፡፡ ሌሎች ስሞችም እየተሻገሩ ሄደዋል፡፡ በግእዝ የጸሎተ ሃይማኖት መጻሕፍት ‹ኑር እም ኑር› ይላል፡፡ ዐረብኛ ነው፡፡ ብርሃን ዘእም ብርሃን ማለት ነው፡፡ በአማርኛ ውስጥ ባንዳ፣ ሸንኬሎ፣ ፈርሜሎ፣ ማርቴሎ፣ ሊቤሎ፣ ባሬላ፣ ባሬስታ፣ ቴስታ፣ የሚሉት ቃላት መነሻቸው ጣልያንኛ ነው፡፡ እንደ ጠመንጃ ያሉት ከቱርክ፣ እንደ በርበሬ ያሉት ከፖርቹጊዝ፣ እንደ ምሥጢር ያሉት ከአካድ፣ የተዋስናቸው ናቸው፡፡
ጡር፣ ጦስ፣ ዋሻሻ ዋርድያ፣ ዋንጫ፣ ወንበዴ፣ ወንጀል፣ሰንጋ፣ ሸጌ/ሸጋ፣ሽፍታ፣ ሮሮ፣ ቁና፣ ቅርጫ፣ቄጤማ፣ ኮሮጆ፣ጀብዱን ጨምሮ አያሌ የኦሮምኛ ቃላት አማርኛ ሆነዋል፡፡ በተቃራኒውም የአማርኛ ቃላት ኦሮምኛ ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ብዙዎቹ የሀገራችን ብሔረሰቦች ተመሳሳይ መጠጥ መጠጣታቸው ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ስመ ጥራታቸውም አስደናቂ ነው፡፡ በአማርኛ ጠጅ የሚለው ቃል በአሪ (ጸጅ)፣ አርጎባ (ጠጅ)፣ ባስኬቶ (ጠጅ)፣ ዲሜ(ጠጅ)፣ ዶርዜ(ጠጅ)፣ ጋፋት(ጸጅ)፣ ጋሞ(ጠጅ)፣ ሐረሪ(ጠጂ)፣ ሶዶ/ክስታኔ(ጠጅ)፣ ኦይዳ(ጠጅ)፣ ሰባት ቤት ጉራጌ(ጠጅ)፣ ስልጤ (ጠጅ)፣ ወለኔ(ጠጃይ)፣ ዘርጉላ(ቸጅ) ተብሎ ሲጠራ እናገኘዋለን፡፡
ከሁሉም የዒትዮጵያ ክልሎች የተሰበሰቡት ወካይ ተረቶች ሦት ተመሳስሎ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ለእንስሳት በሚሰጡት ተመሳሳይ ገጸ ባህሪይ፣ በሞራላዊ ዕሴታቸውና በማኅበራዊ ሥሪታቸው(ለልጆች፣ ለሴቶች፣ ለሽማግሌዎች፣ ለአጭሮች፣ለረዥሞች፣ ለገበሬዎች፣ ለነጋዴዎች፣ ለመሪዎች በሚሰጡት ቦታ) ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ይሄም ታኅታይ መዋቅራቸው አንድ መሆኑን ያስረዳል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁለት ዓይነት መዋቅር አላቸው፡፡ ላዕላይና ታኅታይ፡፡ ላዕላይ መዋቅሩ ከላይ የምናየው የቋንቋ የባህል፣ የእምነት፣ የመልክ፣ ወዘተ. ጠባያት ናቸው፡፡ ታኅታይ መዋቅሩ ግን ከሥር ያለው፣ ተቆፍሮና ተጠንቶ ካልሆነ በቀላሉ የማይታየው፤ እንዲህ በቀላሉ የማይታወቀው ክፍል ነው፡፡ ላዕላይ መዋቅሩ ልክ እንደ መሬት አፈር ነው፤ በየጊዜው ብዙ ነገር ይደባለቅበታል፡፡ ታኅታይ መዋቅሩ ግን ልክ እንደ ምድር ሥር ዐለት ነው፡፡ ዐለቱ በዘመናት ብዛት በተፈጥሮ ሂደት ጠንክሮ፣ ጸንቶ የተገነባ ነው፡፡ በቀላሉ መንካትና ማፍረስ፣ ከሌላ ነገርም ጋር መደባለቅ አይቻልም፡፡
ዛሬ ዛሬ አንዳንድ ወገኖች አንድን ሕዝብ ‹ንጹሕ› የማድረግ ያልነጻ መንገድ ላይ ናቸው፡፡ መደባለቅ፣ መተሣሠርና መዋሐድ የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ መሆኑን ሆን ብለው ይዘነጉታል፡፡ እንደማይሆን እያወቁት፣ የአካባቢ ንጽሕና መጠበቅ አቅቷቸው የሕዝብ ‹ንጽሕና› ለመጠበቅ ይነሣሉ፡፡ ከሌላ መጋባትን፣ ከሌላ ጋር አብሮ መኖርን፣ ሌላ ቋንቋና ባህል መማርንና መውረስን፣ በሌላ ስም መጠራትን፣ ሊያጠሩ ይታትራሉ፡፡ ወደ ኋላ ሄደው ባሕታዊ ሕዝብ(ለብቻው ተነጥሎ የኖረ) መፍጠር ያምራቸዋል፡፡
አንድ ወንድ የሴት ማስክ ስላደረገ ጾታው አይቀየርም፡፡ አንድን ሕዝብም ከላይ የሆነ ነገር ስለሳልንበት እሱነቱን አይቀይርም፡፡ ከዚያ ይልቅ የታሪክንና የሳይንስን እውነታ ተቀብሎ፣ በሕዝብ ላይ ከመሥራት ለሕዝብ መሥራት ይሻላል፡፡ ‹ንጹሕ› ሕዝብ የመፍጠር ንጹሕ ያልሆነ አካሄድ የማይሳካው ከሕዝብ ታኅታይ መዋቅር ጋር አብሮ መሄድ ስለሚቸግረው ነው፡፡