በህዝብ ልብ ከመሾም የሚበልጥ ከፍታ የለም፤
የሰሜን ሸዋው ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወ/አገኝ እናመሰግናለን፡፡
መልካም የሥራ ዘመን ይሁንልዎት፤
****
ከሄኖክ ስዩም
እቀናበታለሁ፡፡ እንዲህ ያለ ትህትና፣ እንዲህ ያለ ወገን መውደድ፣ ደግሞም እድለኛ ነው፡፡ በሚወደው ተወዷል፡፡ አቶ ተፈራ ሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ በሆነ ማግስት ደስ የሚል ድባብ ሸዋን አዳረሰ፤ ደስ የሚል ትብብር በደብረ ብርሃን ታየ፡፡
እንቅልፍ የለሽ ሰው ነው፡፡ ከተመደበበት ቀን ጀምሮ ሲሮጥ አይተንዋል፡፡ የሰሜን ሸዋ ድምቀት፣ የኢንቨትመንቷ ግለት፣ የተወላጆቿ መነቃቃት ምክንያት ነው፡፡ ሰላም በሆነ ቀዬው የበለጸገ ህዝብ ማየት ይሻል፡፡ ለዚህ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡
ቢሮው መንገድም ነው፡፡ እየሄደ ይሰማል፤ እየሄደ ጉዳይ ይፈታል፡፡ መንገድ ላይ አግኝቶ ችግሩን የፈታ ሰው ምስክርነት ብዙ ሰምቻለሁ፡፡ እሱ ስለ አማራ አንድነት ይጨነቃል፡፡ የሸዋን የቀደመ ክብር ለመመለስ ይለፋል፡፡ ይሄ ሁሉ ደግሞ በሰላምና በልማት ብቻ እንደሚሆን ያምናል፡፡ ምናልባትም ሰባ አምስት አመታት የተኛውን ሰሜን ሸዋ ከእንቅልፉ የቀሰቀሰ ብርቱ ሰው ነው፡፡
ጥቅም ስላገናኘን ሰው እያወራሁላችሁ አይደለም፡፡ አንዲት ሲኒ ማኪያቶ የተጋበዘ ሰውም ኾኜ አይደለም፡፡ የህዝብን ልብ ባሸነፉ ፖለቲከኞች ስለምቀና ነው፡፡ ህዝብን ለማገልገል እራሳቸውን አሳልፈው ስለሚሰጡ ጎበዞች ማውራት ደስ ስለሚለኝ ነው፡፡
ተደጋጋሚ መድረኮች ላይ አይቼዋለሁ፡፡ ስለ ትውልድ ቀዬው እንኳን የሰማሁት የአማራ ክልል ሹመቱ ላይ ሲገለጽ ነው፡፡ እሱ እንዲህ ያሉ ሀሳቦች ለማሰብ እድል የማይሰጥ ብርቱ ሰው ነው፡፡ በደፋነው ሰው፡፡ እንዲህ ላለው ስብዕና ታድሎት የሚያስብል ሰው፡፡
ሰሜን ሸዋ ዞን በአማራ ክልል የቆዳ ስፋቱ ትልቁ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ቅርብ ብቻ ሳይሆን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሀገራችንን የኢንቨስትመንት አቅም የሚወዳደር ቀጠና ነው፡፡ እንዲህ ያለው ዞን መሪ ወደ ክልል ሄዷል፡፡ እዚያም እንደ ሰሜን ሸዋውን አይነት ተፈራ ካየነው ለአማራ ክልል ትልቅ እድል ነው፤ ግን ስጋት አለኝ፡፡
የብአዴን ሰዎች እንዲህ ያለ ጠባይ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ሃያ ሰባት አመት አድፍጠው ተላላኪ ነበርን ይላሉ እንጂ አልላክም አይሉም፡፡ እንዲህ ያለ የስራ አውድ ለተፈራ አይነት ሰው ሸጋ ቦታ አይደለም፡፡ የደሃው የአማራ ህዝብ ቀና ልብ ያግዘው፡፡
ተፈራ የተሾመ ሰው ነው፡፡ በህዝብ ልብ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ ቀና ብለው መሄድ የሚችሉ ልጆች አባት ሆኗል፡፡ የሚያውቀው እንደእኔ እንዲህ ሲመሰክር የማይሸማቀቀው ሰውዬው የማያሸማቅቅ ስለሆነ ነው፡፡ እንዲህ ላለው ሰው ረዥም እድሜ ብቻ አልመኝለትም፤ የሰው ዓይነት ብዙ ጓድ ያፈራ ዘንድ ነው፡፡ መልካም የሥራ ዘመን ይሁንልህ፤