በጀቱ ለምንግሥት ሠራተኞች ለእኩል ሥራ እኩል ደመወዝ ማስተካከያን ይጨምራል
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትንትናው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ የ2012 የፌዴራል መንግስት የተጨማሪ በጀት እና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ብር 28 ቢሊየን በተጨማሪ በጀትነት አጸደቀ፡፡
ለተጨማሪ በጀቱ መሰረታዊ መነሻ የሆነው በቅርቡ በመንግስት የተዘጋጀው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሲሆን ዋናው አላማው ኢኮኖሚው አሁን ከገጠመው ተግዳሮቶች የሚላቀቅበትን የፖሊሲ እርምጃዎች ተግባራዊ ለማድረግ ብር 18 ቢሊየን፤ ለልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ትግበራ ብር 2 ቢሊየን እንደዚሁም ለእኩል ስራ እኩል ደመወዝ አገራዊ ትግበራ ብር 7 ነጥብ 9 ቢሊየን በድምሩ ብር 27 ነጥብ 89 ቢሊየን ተጨማሪ በጀት እንዲጸድቅ የገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው የተጨማሪ በጀት ረቂቅ እዋጅ ላይ በስፋት ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
በመቀጠልም ምክር ቤቱ የተወያየው በገንዘብ ሚኒስቴር የቀረቡትን ለደብረ ማርቆስ-ሞጣ የመንገድ ሥራ ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ ለአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልዕቀት ማዕከል መመስረቻ ፕሮጀክት እና ለሁለተኛው አገር አቀፍ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ሳንቴሽንና ሐይጅን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውሉ የብድር ስምምነቶች እና ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ሲሆን ብድሮቹ ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙ፣ የ10 ዓመት እፎይታ ያላቸው፣ በረጅም ጊዜ የሚከፈሉ እንደዚሁም ወለድ የማይታሰብባቸው በመሆናቸው አዋጆቹ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ መዝሙርና የአፍሪካ ቀን ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ አገራችን ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን አጋርነት ለማሳደግ፣ ለፓን አፍሪካኒዝምና ለአፍሪካ የውህደት አጀንዳ ተግባራዊነት ያላትን ቁርጠኝነት ለማስቀጠል እንዲሁም የህብረቱ ኮሚሽን አስተናጋጅ አገርነት ሚናዋን ለመወጣት ከምታከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ አላማን ማውለብለብ፣ የአፍሪካ ህብረት መዝሙርን ማዘመር እና አፍሪካ ቀን ታስቦ እንዲውል ማድረጉ አገራችን ለህብረቱ አላማዎች ስኬት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ በመሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የግብርና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆችን ለማቋቋም በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ኮሌጆቹ ተጠሪነታቸው ለግብርና ሚኒስቴር ሆኖ እራሳቸውን የቻሉ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማት እንዲሆኑና በግብርናው ዘርፍ በአገሪቱ ልዩ ፍላጎቶች ላይ አትኩረው እንዲሰሩ ማድረግ እንዲቻል የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆችን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡
ም/ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ከላከልን መረጃ ለማወቅ ተችሏል