የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኤክሳይዝ ታክስ እናየጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጡትን አዋጆችን በአብላጫ ድምጽ አፀደቀ።
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ስብሰባውም የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።
ቋሚ ኮሚቴው በስራ ላይ ያለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ለረጅም ጊዜ በስራ ላይ የቆየ በመሆኑ እና የማምረቻ ወጪን መሰረት አድርጎ የሚሰላ በመሆኑ ግልፅነት የሚጎድለው መሆኑን አንስቷል።
ይህን ለማስቀረትም አዲሱ አዋጅ በመሸጫ ዋጋ ላይ እንዲሰላ በማድረግ ለከፋይ እና አስከፋዩ ግልፅነት የሚፈጥር መሆኑን አመላክቷል።
በተጨማሪም ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በአካባቢ ደህንነት ላይ እያስከተሉት ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ከተወሰነ ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ለመገደብ እንዲሁም ለጤና ጎጂ በሆኑ ምርቶች ላይ ያለውን የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔን በመፈተሽ ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ መዘጋጀቱን ቋሚ ኮሚቴው አስታውቋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ በተደረጉ ማሻሻያዎች ላይም ቋሚ ኮሚቴው፥ ከ1 ሺህ 300 ሲሲ ያልበለጠ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ተሽካረካሪዎች እና ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ አዲስ በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ፣ ሙሉ በሙሉ ተበትነው የቀረቡ፣ በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እንዲገጣጠሙ በከፊል ተበትነው የገቡ እና አዲስ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው የቀረቡ ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ30 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ እንደተደረገበት አንስቷል።
በተጨማሪም ከ1 ዓመት እስከ ከ2 ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ80 በመቶ ወደ 55 በመቶ እንዲሁም፥ ከ2 ዓመት እስከ ከ4 ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ130 በመቶ ወደ 105 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ ተደርጎበታል።
ከ4 እስከ 7 ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ230 በመቶ ወደ 205 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ መደረጉ ተጠቅሷል።
ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ ከ430 በመቶ ወደ 405 በመቶ ዝቅ እንዲል ማሻሻያ መደረጉም ነው የተነሳው።
ይህ ማሻሻያ መካከለኛ የገቢ ደረጃ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱንም ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።
በሲጋራ ላይ የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ በፓኬት በዋጋው 30 በመቶ እንዲሁም በፍሬ 5 ብር የነበረው በኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያው ተጨምሮ 8 ብር እንዲሆን መደረጉንም ነው የገለጸው።
በረቂቅ አዋጁ የታሸገ ውሃ ላይ ተጥሎ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ ከ15 በመቶ ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
በቴሌኮም አገልግሎቶች ላይ እንዲጣል በኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጁ ቀርቦ የነበረው የ5 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲወጣ መደረጉም ነው የተገለፀው።
በተጨማሪም አዋጁ በማሻሻያው ከፀናበት እለት በፊት የባንክ ፍቃድ የተሰጣቸው እና አዋጁ ስራ ላይ ከዋለበት እለት አንስቶ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገር በሚገቡ እቃዎች ላይ ኤክሳይዝ ታክስ የሚጣለው እና የሚሰበሰበው፥ በኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/1995 በተሻሻለው ድንጋጌዎች መሰረት ይሆናል ተብሏል።
ይህም በአዲሱ ማስተናገድ በታክስ አስተዳደር ስርዓት ላይ ችግር ስለሚያስቀምጥ ገደብ መቀመጡ ተመላክቷል።
ከቅጣት ጋር ተያይዞ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ዝቅተኛውን የቅጣት ገደብ የማያስቀምጥ በመሆኑ አንቀጹ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሰው ከ3 ዓመት እስከ 5 ዓመት የእስር ቅጣት እና ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲጣል በሚል ማሻሻያ እንደተደረገበትም ተገልጿል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁን በ4 ተቃውሞ፣ በ7 ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
በተያያዘ ዜና ፓርላማው የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በተመለከተ የቀረበ አዋጅን አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባው የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።
አዋጁ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ለማህበራዊ ስምሪት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ለሀገራዊ አንድነት፣ ለሰብዓዊ ክብር እና ለብዝሃነት ጠንቅ መሆኑን በመገንዘብ በተለይም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በህብረተሰቡ መካከል ያሉ መልካም እሴቶች በጥላቻ ንግግሮችና በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸሩና ለሀገርም ስጋት እየደቀኑ በመሆናቸው እንዲሁም እነዚህን ችግሮች አሁን ባሉት ህጎች መፍታት የማይቻል በመሆኑ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የጥላቻ ንግግር እና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ዴሞክራሲያዊ ውይይት እና ክርክር ለማድረግ እንቅፋት በመሆኑ ከብሄር እና ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ የጥላቻ ንግግር እና ሃሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨትን እንዲሁም ዘርን፣ ጾታን እና አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ የሚደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እና ሃሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ተገልጿል።
እንዲሁም የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭትን በህግ መከልከል አስፈላጊ በመሆኑ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱም ተነግሯል።
የምክር ቤቱ አባላትም በአዋጁ ላይ ያላቸውን ሃሳብ እና አስተያየት የገለጹ ሲሆን፥ ለአብነትም ይህ አዋጅ የዜጎችን ሃሳብ በነጻነት የመግለጽ መብት የሚጋፋ እንደሆነ ያነሱ ሲሆን፥ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥቶበታል።
በዚህም አዋጁ በህገ-መንግስቱ ላይ ከተቀመጠው የመናገር መብት ጋር እንደማይቃረን፣ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29 (6) እና (7) ከተቀመጡት ገደቦች ውስጥም አንዱ ምክንያት ሰብአዊ ክብርን መጠበቅ ሲሆን፥ የጥላቻ ንግግር ሰብአዊ ክብርን የሚነካ ዋነኛው በመሆኑ ከተቀመጠው ገደብ ጋር የሚገናኝ መሆኑ ምላሽ ተሰጥቶበታል።
ምክር ቤቱ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ አዋጅን በ23 ተቃውሞ እና በ2 ድምጸ ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።(ምንጭ፡-ፋና)