Connect with us

ዶሃ:- የባሕረ ሰላጤዋ ዕንቁ

ዶሃ:- የባሕረ ሰላጤዋ ዕንቁ
Photo: Booking.com

ኢኮኖሚ

ዶሃ:- የባሕረ ሰላጤዋ ዕንቁ

ዶሃ:- የባሕረ ሰላጤዋ ዕንቁ
(ከመኩሪያ መካሻ)

የባብ ኤል ባህር ዳርቻ ነው። መሻሽቷል። ሂልተን ዶሃ ስምንተኛው ፎቅ ላይ ነው ያለሁት። ቁጥር 81ዐ። ከዚያ ፎቅ ላይ የዶሃ ከተማን ዙሪያ ገባ መመልከት ይቻላል። በቀን ብርሃን ዶሃን በወፍ በረር ከመቃኘት ይልቅ አመሻሹን መመልከት የልብ ሃሴትን ይሰጣል። ዶሃ የካጣር ዋና ከተማ ናት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢተ ኢሳይያስ የተጠቀሰውን ምዕራፍ 21ን መለስ ብዬ አነበብኩ። ‹‹ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ከሚያስፈራ አገር ከምድረ በዳ ይወጣል›› ይላል። አዎን! Qatar ካጣር፣ (አንዳንዶች ኳታር ይሏታል) ምድረ በዳ ናት። ዳሩ ግን የምታስፈራ ምድረ በዳ አይደለችም። እንዲያውም ‹‹ማርና ወተት የሚፈልቅባት›› ቢባል ያንሳታል እንጂ አይበዛባትም። ይህች ትንሽዬ የባህረ-ሰላጤ ሀገር በዕንቁና በጥቁር ወርቅ ሀብቷ መትረፍረፍ ሰማይ ጥግ ደርሳለች።

የዛሬዋ ካጣር (Qatar) ከመመሥረቷ በፊት ጥንታዊቷ ካጣር የዕንቁ ንግድ የሚካሄድባት ነበረች። ከቻይና፣ ከአውሮፓ፣ ከአፍሪካውያን ጋር ስትነግድ ኖራለች። በ2ዐኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ የበላይ ጠባቂነት ሥር ስትተዳደር ቆይታለች። በ1971 (እ.ኤ.አ.) ነው ነፃነቷን የተጐናፀፈችው። ነፃነቷን ከማግኘቷ በፊት እንግሊዞች ባወጡት የነዳጅ ሀብት ትንሽየዋ ሀገር ፈረጠመች። ነፃነቷን ከመጐናፀፏ አንድ ዓመት በፊት ደግሞ የተፈጥሮ ጋዝ አገኘች።

ከዚህ በኋላማ ማን ይድረስባት። ሀብት፣ በሀብት ሆነች። ተድላና ደስታ በእያንዳንዱ ካጣሪ ቤት ውስጥ ገባ። በነገራችን ላይ የዜጋው አማካይ የገቢ መጠን ከ9,5ዐዐ ዶላር በላይ ሁኗል። እስቲ ይህን ገቢ ከኢትዮጵያውያን ገቢ ጋር አስሉት፣ ከ14 እጥፍ በላይ ነው። ይህ የሀገሪቱ ሀብት ለ3ዐዐሺ ዜጐቿ ይከፋፈላል። በካጣር አስገራሚው ነገር የውጭ ሀገር ዜጋ ከሀገሬው ዜጋ በአሥር እጥፍ መብለጡ ነው። በየስፍራው የፓኪስታንን፣ የህንድን፣ የሲሪላንካን፣ የኔፖልን፣ የፊሊፒንስን፣ የዩክሬይን ወዘተ. ዜጐች የሀገሪቱን ህይወት ወደፊት ይመራሉ። ለአንድ ካጣሪ አሥር የውጭ ዜጋ ይደርሰዋል እንደማለት ነው።

ሳውዲን ከሳውዲ ቤተሰብ (House of Saud) የወጡት እንደሚመሯት ሁሉ ካጣርን የአል-ታኒ ቤተሰቦች (House of Thani) ይመሯታል። የዶሃን የዘንድሮውን ዓለማቀፍ ፎረም (Doha Forum) በንግግር የከፈቱት ዘንካታው ሼህ አልታኒ (ታማም ቢን ሃማድ አልታኒ) ነበሩ። ዛሬ በዓለማችን ታዋቂውን የአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ 15ዐ ሚሊዮን ዶላራቸውን ሆጭ አድርገው ያቋቋሙት እኚሁ ሰው ናቸው። በካጣር ከሌላው የዐረብ ዓለም የተሻለ ዘመናዊነትና የሴቶች መብት ይከበራል። በዶሃ ጐዳናዎች ረጃጅም ሌክሰስና ጂኤምሲ (GMC) መኪናዎችን ሴቶቹ በነፃነት ያሽከረክራሉ። የእኛ ሴቶች የሚያዘወትሯት ቪትዝ ትኖር ይሆን? ብዬ ነበር፤ አንድም ለዓይን የለችም። የካጣር ሴቶች ተነግሮ የማያልቅ ውበት አላቸው።

ከጥቁሩ ሂጃብ ውስጥ ለተመለከታቸው የዕንቁ ፈርጦች ናቸው። ከነዚሁ ሴቶች አንደኛዋና ወደ ዶሃ የጠሩኝ ወይዘሮ ሎልዋህ ራሽድ አልካጠር ነበሩ። አዲስ አበባ ሲመጡ የካጣር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሆነው ሲሆን፣ አሁን ዶሃ ፎረም ላይ ሳገኛቸው በስልጣናቸው ጨምረው ጠበቁኝ። በሚፍለቀለቅ ፈገግታቸው ተቀበሉኝ።

‹‹ሹመት ያዳብር!›› አልኳቸው። ‹‹በናንተ መጀን የኢትዮጵያ ምልኪ (Omen) መልካም ነበር፣ ይኸው ለዚህ በቃሁ›› አሉኝ። በሉ፣ ይበርቱ!›› ብያቸው ተለያየን።

ከፊት ለፊት በሻይ ጠረጴዛ ዙሪያ ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከባለቤታቸው ጋር፣ አምባሳደሯ ወ/ሮ ሳሚያ ያወራሉ። ጠጋ ብዬ ተወወቅሁ። አለፍ ስል ወርቅነህ ገበየሁን ተመለከትኩ።

ለሠላምታ እጄን ስሰነዝር በቁመታቸው ልክ የሞቀ ሠላምታ ሰጡኝ። ከዐቢይ መንግሥት ወዲህ የባለስልጣኖቻችንን የባህርይ ለውጥ ተመለከትኩ። ከመጀነን ይልቅ ሠላምተኛ ሆነዋል። ከእኔ ትይዩ የፍልስጤሟ የፖለቲካ ሰውና ቃል አቀባይ ሃናን አሽራዊ ተከበው ያወራሉ። እሳቸውንማ መተዋወቅ አለብኝ ብዬ ተጠጋሁ። ተዋወቅኳቸው። ‹‹ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ ኦሪያና ፋላቺ የፃፈችውን የአቡ አማርን (የያሲር አረፋት የሽምቅ ስም) ቃለምልልስ ወደ ሃገሬ ቋንቋ ተርጉሜ አስነብቤያለሁ›› አልኳቸው።

ፊታቸው ደስታን ረጨ። ፎቶ ራስ-ገጭ (ሰልፊ) ተነስተን ተለያየን። ሃናን ደስ አላቸው፤ እኔም ውስጤ ደስታን አዝሎ ተሰናበትኳቸው።

አለፍ እንዳልኩ በግራንድ ሸራተን መስተናገጃ ስፍራ ቡና ማፍያና ማቅረቢያ ስኒዎች የደረደረ ሰው ተመለከትኩ። ዕጣንም አጠገቡ እያጨሰ ሀድራው ሞቅ ብሏል። የቡና ሱሴ ውል አለብኝ። የሊሙ ኢናሪያን ቡና ሲለቅምና ሲጠጣ ላደገ ለእኔ ዓይነቱ ሰው ቡና ሁሉም ነገር ነው።

የግራንድ ሸራተኑ ቡና ከእኛ ሀገሩ ቡና ጋር አይመሳሰልም። ልዩ አቀራረብና መልክ አለው። እንደኛው ዓይነት የፈረስ ጭራ የመሰለ ቡና አለመሆኑ ደንቆኛል። ጠጋ ብዬ ቡና ቀጂውን ሰዒድ አቡበከርን ‹‹ይቻላል?›› አልኩት። ግማሽ ፍንጃል ለቅምሻ የሚሆን ቀዳልኝ። ስመለከተው ጠጅ ሊያስቀምሰኝ የቀዳልኝ እንጂ ቡና አይመስልም።

ለመጀመሪያ ጊዜ ብጫ ቡና ልጠጣ ነው። ፉት ስላት አለቀች። ፍንጃሉን መለስኩለት። ደገመኝና ቴምር ሰጠኝ፤ የሚገርም ቴምር፣ የሚገመጥ ቴምር ነበር።

የካጣር ቡና አይቆላም። ጥሬው ተጨምቆ ነው የሚፈላው። ለዚህም ነው መልኩ ብጫ የሚመስለው። ፍፁም አርኪ ቡና ነበር። ወዲያው ሱሴን አበረደልኝ። ‹‹ሹክረን›› ብዬ ሰዒድን ተሰናበትኩና ወደ ማረፊያዬ ተመለስኩ። የኤሌክትሮኒክ ቁልፉን ለበሩ አሸተትኩት። ተበረገደ። ለዓይን ያዝ ማድረግ ጀምሯል። የቁጥር 81ዐን መስኮት ከፍቼ ቀዝቃዛውን አየር ማግ፣ ማግ አደረኩ። የተለየ ጠረን አወደኝ። የቱስካኖ ሲጋራም፣ የሺሻም ሺታ መሰለኝ። ለማንኛውም ወደ ባህሩ ዳርቻ ልውጣ ብዬ ወደዚያው አመራሁ። የባብ ኤል ባህር ሰርጥ ዳርቻ አሸብርቋል። ከቡና ቤቱ የሚፈሰው ሙዚቃ ይንቆረቆራል። የሪታ ኦራ ‹‹Let you Love me›› ሙዚቃ ነው።

የዌስት ቤይ የባህር ወጀብ ፋልማውን ተጠግቶ ይገማሸራል። ከባህሩ ወጀብ ጋር የቀዘቀዘ አየር እየማጉ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። ነጫጭ ጀለቢያቸውን የለበሱ አሚሮች፣ ሼኮች፣ የዶሃ እመቤቶች ተቀምጠው የሺሻቸውን ኵርቢት ይምጋሉ። ስለ ቢዝነስ ያወራሉ። ስለፍቅርም ሊሆን ይችላል የሚያወሩት። አንዱ ሼህ ከኋላዬ ከሎንደን የቢዝነስ አጋሩ ጋር በሞባይሉ ያወራል። ጆሮዬን ጣልኩበት። በዶሃ 2ዐ22 በሚዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ውድድር ስለሚያስገባው ዕቃ ነበር ድርድሩ። ‹‹ሦስት ቢሊዮን ነው?›› አለው። ጆሮዬን አላመንኩም።

ሦስት ቢሊዮን! ‹‹ከሎንደን ወገን ከ2.6 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ቢሆን ነው›› ይለዋል። ‹‹ችግር የለም ቶሎ እንዲገባ ይሁን!››። ‹‹Let you love me›› ሙዚቃን በዓይን የማዬት ያህል በኦራ ድምጽ ሲንቆረቆር ወደ ሌላ ትዝታ ይዞ ይነጉዳል። ሺሻ ይጨሳል፣ ድርድር ይካሄዳል። የዶሃ ወይዛዝርት ለሁለት፣ ለሦስት፣ ሆነው በሺሻ ማጨሺያ ክፍሎች ሺሻውን ይምጉታል። የዶሃ ምሽት እንዲህ እየተንተከተከች ከሺሻው ጭስ ጋር የዶሃ ወይዛዝርትና አሚሮች ሃሳባቸውን አራግፈው ከዶሃ ሂልተን ወደየቤታቸው ይለያያሉ።

ከባህሩ ፋልማ ላይ ተቀምጨ ስቆዝም ባህሩ ላይ ቱሪስቶች ምሽቱን ተጠግተው በፈጣን ጀልባ ይንሸራሸራሉ። እኔን ባደረገኝ ያሰኛል። መልካም ያበሻ ቅናት። በመሃሉ ጨረቃዋ ሰማዩን ቀዳ ከባህሩ ስትወለድ ታየችኝ። እኔ ከልምዴ ጨረቃን ሰማይ ሲያዋልድ ነው የማውቀው። በገልፍ ሀገሮች ግን ባህር ቀዳ የምትወጣ ነበር የምትመስለው። ከዚያም ባህሩ ላይ ባውዛዋን ረጨች። ለካስ ዐረቦች ከጨረቃ ጋር ያላቸው ቁርኝት ከምንም ተነስቶ እንዳልሆነ ገባኝ። ድምቀቷ ጤፍ የሚያስለቅም ነበር። ‹‹Let you love me›› ቀጥሏል።

ፋታ ሳገኝ ‹‹መቀመጥ-መቆመጥ›› በሚለው መርህ መሠረት ወጣ ማለት ፈለግሁ። የሆቴሉን አስተናጋጅ ግብፃዊ መሀመድን ‹‹ዬት ሄጄ ታሪካዊ ነገር ብቃኝ ትመክረኛለህ?›› ስል ጠየኩት። ‹‹ወደ ሱቅ ዋቂፍ ሂድ!›› ሲል መከረኝ። መቼም ዶሃና የዶሃ ፎቆች የሚጠገቡ አይደሉም። ሁሉም ፎቆች ትናንት አልቀው ርክክብ የተደረጉ የሚመስሉ ጥርትና ልቅም ያሉ ናቸው።

የፎቆች ዝናብ በዶሃ የዘነበ ይመስላል። ዲዛይናቸው ምርጥ የተባሉና አስደማሚ ናቸው። የዶሃ ዘንባባዎች እንደ ክብር ዘብ በሰልፍ ቆመው ይዘናፈላሉ። ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ፈጥረዋል። አንዱን አይተው ሳይጨርሱ ሌላኛው ፎቅ ይማርካል። የከተሜነት አዋሲስ (illusion) ሰቅዞ ባለ በሌለ ሀይሉ ይይዛችኋል። ምናለ የእኛ አርክቴክቶች ለአንዲት ቀን ዕድል አግኝተው ቢያዩዋት ያሰኛል። የአል-ታኒ ቤተሰቦች ገንዘባቸውን በሀገራቸው ግንባታ ላይ ማዋላቸውን መመስከር ይቻላል። ከቤጂንግ፣ ወይም ከኒውዮርክ ፎቆች በላይ የጐብኚን ዓይን መማረክ የሚችሉ ናቸው። ፎቆች ላይ የሚለጣጠፉ ማስታወቂያዎች ዓይን አይረብሹም። ምናለ የእኛዎቹ የከተማ አስተዳዳሪዎች ዶሃን በጐበኙ ያሰኛል።

የኢቢሲው አብዱል ጀሊል በህንፃዎቹ ከመማረኩ የተነሳ ቀንም ማታም ህንፃዎቹን ፎቶ ያነሳል። ‹‹ምን ዓይነት ተአምር ነው?›› እያለ መልስ የሌለው ጥያቄ ይጠይቃል።
እስቲ የዶሃን ታላቅ ሱቅ ልጐብኝ ብዬ ወደ ሱቅ ዋቂፍ (Waqif) አመራሁ። ሱቅ ዋቂፍ ከዶሃ ዘመናዊነት መንጥቆ ወደ ቀድሞ የዶሃ ጥንታዊነት የሚወስድ ቋሚ ገበያ ነው። ይህ የደራ ገበያ አልባሳት፣ ቅመማ-ቅመሞች፣ ዕጣኖች፣ ሽቱዎች፣ የዐረብ ጣፋጮች፣ የስጦታ ዕቃዎችና ስዕሎች ይገኙበታል።

ከካጣር ዘመናዊነት ዓለም አውጥቶ የካጣር ጥንታዊነትን ለመጎብኘት ትክከለኛው ሥፍራ ሱቅ ዋቂፍ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ባለእጆችና ባህላዊ ልብስ ሰፊዎች ይታዩበታል። የሶሪያ፣ የሊባኖስ መመገቢያ ሥፍራዎችና የሺሻ ማጨሻዎች ዓይንና ልብን ሰቅዘው ይይዛሉ። ዋጋቸው ግን ለአበሻ ኪስ የሚሆኑ አይደሉም። በዓይን ጠግቦ መውጣት የሚቻልበት ሥፍራ ሱቅ ዋቂፍ ብቻ ይመስለኛል።

ከጣርን ከገልፍ ሀገሮች ሁሉ እጅግ ተፈላጊ ያደረጋት ስትራቴጂካዊ አቀማመጧ ነው። የአሜሪካና የእንግሊዝ የአየርና የህዋ ኦፕሬሽን ማዕከል የሚገኘው እዚያ ነው፤ በአል ኡዴድ የአየር ምድብ። ይህ የኃያላን ሀገራት የዕዝና ቁጥጥር ማዕከል ከኢራን እስከ አፋጋኒስታን ዘልቆ 17 ሀገራትን ይቆጣጠራል። ስለዚህ ካጣር ዋና ስትራቴጂካዊ ማዕከልና ለአሜሪካኖቹ እጅግ አስፈላጊ ሀገር ናት።

በዚህ ልዩ ቦታዋ ዓለማቀፋዊ ኮንፈረንሶችን ታዘጋጃለች። የዘንድሮው የዶሃ ፎረም እንኳ 4ዐዐዐ ሰዎችን ከ1ዐዐ ሀገራት አስተናግዷል። በዚህ ሸብ-ረብ ውስጥ ዋነኛውን ሚና የሚወጣው አልጀዚራ ሲሆን፣ የአልጀዚራ ጋዜጠኞች በአስተባባሪነት፣ በመድረክ መሪነት፣ በጠያቂነት፣ ሪኮርድ በማድረግ ይሳተፋሉ። የእኛን የኢትዮጵያውያንን ጉዞ ያደራጀልን ወዳጄ፣ ዕውቁ ጋዜጠኛና የአልጀዚራ የኢትዮጵያ የቢሮ ሃላፊ መሀመድ ጠሃ ተወከል በዚህ አጋጣሚ ሊመሰገን ይገባል። ሀገር ቤት ገብቼ ኢ-ሜሌን ስከፍት ሙሉ ዶክመንቱ ደረሰኝ። ደስም አለኝ።

የዶሃ ፎረም ስብሰባ እንደተጠናቀቀ ጉብኝቴን የቀጠልኩት በአልጀዚራ ጣቢያና የሚዲያ ማሠልጠኛ ተቋም ጉብኝት ነበር። አልጀዚራ ሚዲያ ከሥራውና ካለበት ህንፃ ጋር ሲወዳደር ‹‹አልጀዚራ እዚህ ሆኖ ነው እንዴ ዓለምን የሚያነጋግር ሥራ የሚሠራው?›› ያሰኛል። የተቋሙ አባል የሆነውና አስጐብኚያችን ሙንታሲር ሙራይ እንደነገረኝ ‹‹ለሚዲያ ጥንካሬ ዋናው ህንፃና ዕቃ ሳይሆን የያዘው ሙያተኛ ነው ወሳኙ›› ሲል ነበር የሰው ኃይልን ወሳኝነት የገለፀልኝ።
*****
የመጨረሻው የዶሃ አዳሬ ዶሃን ብቻ ሳይሆን ሀገሬን እንዳስብ አደረገኝ። አንዲት የባህረ-ሰላጤ ትንሽ ሀገር 3 ሚሊዮን ለሚበልጡ የውጭ ሀገር ዜጐች የሥራ ዕድል ፈጥራ ስታሰራ ስመለከት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ዬት ነን? እላለሁ። ቅናት አይሉት የውድድር አባዜ ብቻ በእዝነ-ልቡናዬ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ተመላለሱብኝ።

ዛሬ የሚታየው የኢትዮጵያውያን እርስ በርስ መናከስ፣ መበላላትና የሰው ልጅ ሊፈጽመው ይችላል ተብሎ የማይታሰብ የአውሬነት ባህርይ ከየት መጣ? ስል ጠየቅኩ። ይህች የባህረ-ሰላጤ ዕንቁ ከተማና የእኛ ከተሞች ህይወት በንጽጽር በዓይኔ እየተደቀኑ በማይጐረብጠው፣ እጅግ ምቾት – በምቾት በሆነው 81ዐ ክፍል ውስጥ ዕንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር ነቃሁ። ለካስ ምቾትም እንቅልፍ ይነሳል?

ወለል ብሎ የዶሃ ሰማይ በርቷል። በመስኮት ስመለከት የባብ ኤል ባህር ዳርቻ ህይወት እያንሰራራ ነው። የባህረ-ሰላጤው ባህር ፋልማውን እየገጨ ይፎክራል። የዶሃ-ህይወት መንተክተኳን ቀጥላለች። በስሱ የተለቀቀ የEasy Listening ሙዚቃ ጆሮ ሰርስሮ ይገባል። የልብ ሀሴትን ይሰጣል። ‹‹Lake of Peace›› ሙዚቃ ነበር የሚንቆረቆረው።
አሁን ሰዓቱ ደረሰ። በፍቅር የጣለችኝን ዶሃ ለቅቄ መብረሬ ነው። ከኢትዮጵያ ከመጣነው የቡድን አባላት ጋር የሃማድ አለማቀፍ አይሮፕላን ማረፊያን መንገድ ተያያዝነው።

የዶሃን ልዩ ከተማነት፣ የህዝቡን ሥርዓትና እንግዳ አክባሪነት እያደነቅን ሃማድ አለማቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ደረስን። በአይሮፕላን ጣቢያው ልክ እንደ ግራንድ ሸራተኑ የካጣር ቡና (ቃዋ ነው እነሱም የሚሉት) ተፈልቶ ጠበቀን። አንድ ፍንጃል ቃዋዬን አወራርጄና ቴምር ቀምሸበት ዶሃን ተለየሁ። ዶሃ የባህረ-ሰላጤዋ ዕንቁ ከተማ ሁሌም ከአእምሮዬ የምትጠፋ አትሆንም። የሪታ ኦራ ‹‹Let you love me›› አሁንም በውስጤ ይሞዝቃል።

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top