Connect with us

ከዳይኖሰሩ ቅሪት ጋር በኦፕሳላ ኢቮሉሽን ቤተ መዘክር !

ከዳይኖሰሩ ቅሪት ጋር በኦፕሳላ ኢቮሉሽን ቤተ መዘክር

ሳይንስና ቴክኖሎጂ

ከዳይኖሰሩ ቅሪት ጋር በኦፕሳላ ኢቮሉሽን ቤተ መዘክር !

ከዳይኖሰሩ ቅሪት ጋር በኦፕሳላ ኢቮሉሽን ቤተ መዘክር !| ሀገሬ ሀገር አላት ስለምን ሰው አጣች?
******
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ኦፕሳላ ኢቮሉሽን ሙዚየም ጎራ ብሎ ከዓለም የተሰበሰቡ ቅሪቶች የሚገኙበትን የኦፕሳላ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መዘክር ጎብኝቷል።

የዳይኖሰር ቅሪት በተቀመጠበት ቤተ መዘክር ሆኖ ስለ ሀገሩ ለምን ሰው የለሽም በሚል ቅናት እንዲህ ከራሱ ይሟገታል። መልካም ንባብ) | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

ናሆሚ የሚናገረው ይጣፍጣል። ኦፕሳላን እንደ ፈረንጅ አራዳ ያውቃታል። ከሸገር በላይ ያጣጥማታል። የከተማዋን ቅርሶች እየዞረ አስጎበኘኝ። የጠገብሁ ካልመሰለው ተርኮ አያበቃም። ኦፕሳላ የመሸጉት ከሚባሉት አንዱ ነው። አንድ ቀን ስለ ኦፕሳላ መሻጊዎቹ ሸጋ ውሎ አወጋችኋለሁ።

አምና ኦፕሳላን ስነግራችሁ የከተማ ኮረዳ ናት ብዬ ነበር። ያ የከተሜነት ውርዝና ዛሬም ድባቧ ላይ አለ። ግን የተጀቦነች ኮረዳ መስላለች ጭጋግ እንደ ካባ ውርጭ እንደ ስካርፕ ጣል አድርጋ ደረስኩ።

ሙዚየሙ የዩኒቨርሲቲው አካል ነው። በከተማዋ እንብርት አረንጓዴ ቀለም ባደመቀው ቅጥር አርፏል። ኢዩቤልዩ ቤተ መንግሥት ህንፃችንን የመሰለ እድሜ ጠገብ ህንፃ እዚህም እዚያም ይታያል።

ለእያንዳንዳችን ሃምሳ የሲዊዲን ብር ከፈልን በሀገሬ ስመታው ሁለት መቶ ገደማ ነው። ወደ አንዱ ሕንፃ ገባን ውበት የአቀማመጥ ጥበብና የቴክኖሎጂ ቱሩፋትን መግለፅ የሀገር ልጅን ማሳቀቅ ነው። አሁን የገባሁበት ሙዚየም ኦፍ ኢቮሉሽን ዙኦሎጂ ይሉታል።

ልጄ እግር እስኪያቅተው የዓለም እንስሳ ቅሪት በክብር ተቀምጧል። የወፍ አይነቱና የታክሲ ደርሚው ጥበቡ ዱር እንጂ ሕንፃ አይመስልም። ከሦስት መቶ አመት ጀምሮ ብሩህ ልብ እንዲህ ያለውን ተፈጥሮ ለጥናትና ምርምር ሲሰበስብ ኖሯል። ዛሬ የጎብኚም መዳረሻ ነው። ገንዘብ ኾኖ ቱሪስት ያከርማል። እንዲህ ሀገርና ከተማ የታደገ ዩኒቨርሲቲ በእኔ ሀገር ብርቅ ነው። እንኳን የተፈጥሮ ቅሪቱ ምስሉን መያዝና ለትውልድ ማትረፍ ምኞት ነው።

ያላደገው ምቹ ቦታ ያላገኘው መንግሥታት ተቀያይረው እንክበርበት ያላሉትን የጥቂት ልሂቃን ድካም እውን ያደረገውን የአዲስ አበባን የተፈጥሮ ቅርስ ሙዚየም አሰብኩት ያመንኩት ፀጋችን የማይመጥነን ህዝቦች መሆናችንን ነው።

የእፅዋቱ ቤተ መዘክር የዚሁ አካል ነው። አበባና ቅጠል ከዓለም ተሰብስባለች። ምድር ጠባቡ ስፍራ አልወሰናትም። ወደ ፓላንቶሎጂና ሚኒራሎጂ ሙዚየም አቀናን።

አንድ ግቢ ሁለት ታላላቅ መካነ ቅርሶች በአንድ ክፍያ። ይኼ ደግሞ ያልያዘው የለም። የዓለም የመአድን ዓይነት ተደርድሯል። የግዙፍ እንስሳት ቅሪተ አካል ያረፈበት ሙዚየም ነው። ዓለም አበሳዋን ስታይ የጠፉት እንስሳት ምድር ቅሪታቸውን ስትተፋ ሳይንስ ዓላማና ገንዘብ እንዲህ በክብር ጠብቀዋቸዋል።

ቀና አልኩ በዓለም ግዙፉ የሚባለው የዳይኖሰር ቅሪት ቁልቁል አየኝ። የጠፋውን እንዲህ በሚያኖር ሀገር ያላትን ከምታጠፋ የመጣሁ እንግዳ መሆኔን አያውቅም።

ብናገር ባይሰማኝም ኢትዮጵያዊ መሆኔን ደበቅሁት። የሚጠይቀኝ መሰለኝ ስለ ወደመው የተፈጥሮ ሀብታችን ስላጠፋነው ፀጋ አፈርሁ። አንዱን ቅሪት አንስቶ እንደ ተያዘ ሌባ አቀርቅሬ ወጣሁ። የመጣሁት አለን ሳይሆን ነበረን ከሚባልበት ሀገር ነው። አለን ያልንውን ነበር ለማስባል ምድራችንን የምናወድም። ናሆሚ ዝምታዬን ተጋራ። እንደ እኔ አምኖበት ይኾን?

Click to comment

More in ሳይንስና ቴክኖሎጂ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top