ውቅር ያደመጠው ያሬዳዊ ዜማ-የቤዛ ኩሉ ትዕይንት
ከሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ
ልደት እኛ ኢትዮጵያውያን የምናከብረው በዓል ብቻ ሳይሆን ዓለም ፊት እኛን ያስከበረ ኩነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ነፍስ ከሚዘራባቸው ልዩ ወቅቶች አንዱ የታህሳስ መጨረሻ ነው፡፡ የልደት በዓል በላሊበላ ለብዙ መቶ ዓመታት ሲከበር ኖሯል፡፡ ዓለም ካወቀው በኋላ ደግሞ ብዙዎች ውቅሩ አፋፍ ላይ ቆመው፤ ከውቅሩ ሆድ ገብተው፤ የተሰራው ሲያፈዛቸው የሚሰራው ግራ ሲያጋባቸው ኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን እናቶች ላስታ ለመድረስ ያሉበት ቅርብ ነው፡፡ ተራራው ሜዳ ይኾንባቸዋል፡፡ ወንዙ እድሜ ለበጋው መምጣት፤ ደራሽ የለውም፡፡ ቁርና ሀሩር ደግሞ ለበረከት ምንም ማለት አይደሉም፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚበልጠው ዓለም ማየት ነው፡፡ ከዚያ ታቦቱ ፊት መቆም፡፡ እልልታ እያሰሙ ያዩትን ዓለም በውዳሴ መግለጽ፤
“ዓይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ
የድንጋይ ወጋግራ የድንጋይ ምሰሶ”
እናቶቻችን ማድነቅ ይችላሉ፡፡ እግር ሲሄድ ዓለም እንደሚታይ ከብዙ መቶ ዓመት በፊት በዝማሬ የገለጹ የቱሪዝም ፍልስፍና ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ ላሊበላ ሲደርሱ ከምንፍስናው ባሻገር ያን ለሰሩ እጆች ክብርን ይሰጣሉ፡፡ ቅዱስም ንጉሥም የሆነው ታላቅ ያመሰግኑታል፡፡ እንደ ንጉሥ ድንቅ ስራው ያፈዝዛቸዋል፡፡ እንደ ቅዱስ ምልጃውን አስበው ይነቃሉ፡፡
የላሊበላ የልደት በዓል አከባበር ለእኛ ድንቅ የአምልኮ ሥርዓት፣ መወለዱን እንደሰሙት እረኞች ለዓለም የመላዕክቱን መውረድና የዝማሬያቸውን ማማር ስናሳይ የኖርንበት አንድም የሚባል ብዙ ትርጉም ያለው እሴት ነው፡፡ ላስታን ደግሞ እንኳን የልደት ዕለት ደርሰውበት ይቅርና በአዘቦትም ክብርን ከነገስታቱ፣ መልካም ማድረግን ከቅዱሳኑ የተማረ ህዝብ ነው፡፡
ልደትን በአስደናቂዎቹ ውቅር መገኛ ማክበር መታደል ነው፡፡ የላሊበላ የልደት በዓል ሰው እንደ መላዕክት በዝማሬ ሲንሳፈፍ የሚታይበት ልዩ ቀን ነው፡፡ ያሬዳዊ ዜማችን ከባህል መንፈሳዊ ልብሳችን ጋር የሚታይበት ኩነት ነው። ዓለም ውቅያኖሱን እንደ ኩሬ ቆጥሮ የሚመጣው ከዚህ ምስጢር ለመገናኘት ነው። የእኛ ስለኾነ እኮራለሁ።
እርግጥ ነው ልደት በመላ ኢትዮጵያ በድምቀት ይከበራል። ትግራይ የደረሰ አፅቢ ወንበርታ ተአምር ያያል። ሰሜን ሸዋ ኦፍና አማኑኤል የአብረሃ ወአፅብሃው አሻራ ሲሞሸር መድረስ የልደት ነው። የላሊበላ ግን ይለያል። የወል የሚባለው መገለጫችን ነው።