Connect with us

ቆንጆ እንቅልፍ ምንድነው? ለእንቅልፍስ እንዴት መዘጋጀት አለብን?

ቆንጆ እንቅልፍ ምንድነው? ለእንቅልፍስ እንዴት መዘጋጀት አለብን?
Photo: GETTY IMAGES

ጤና

ቆንጆ እንቅልፍ ምንድነው? ለእንቅልፍስ እንዴት መዘጋጀት አለብን?

ሁሌም ድካም ይሰማዎታል? ብቻዎን አይደሉም። በጣም ደክሞዎት ለመተኛት ወደ አልጋዎ ሲሄዱ እንቅልፍዎ የገባበት ጠፍቶብዎት ያውቃል?

ይህ ነገር በብዙ ሰዎች ላይ የሚከሰትና አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማድረግ ሊስተካከል የሚችል ችግር ነው።

በጣም ጥሩ የሆነ እንቅልፍ ለማግኘት እነዚህ ከስር የተጠቀሱት አምስት ነጥቦች በጣም ወሳኝ ስለመሆናቸው በርካቶችን አነጋግረን በምርምር ደርሰንበታል ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

‘የማለዳ ወፍ’ ነዎት ወይስ ‘የሌሊት’?

ስለ እንቅልፍ የተሳሳቱ አመለካከቶች

1. በእርግጥም ደክሞዎት እንደሆነ ያረጋግጡ

ምናልባት ቀላል ነገር ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ሰውነታችን በእውነትም ለእንቅልፍ ዝግጁ መሆኑን ማወቅ ጠቃሚ ነው። ለሰውነታችን ውስን የእንቅልፍ ሰዓት መስጠትና እራሳችንን ለጠዋት ፀሐይ ማጋለጥ ደግሞ ጠቃሚ ናቸው።

እያንዳንዱ ሰው የፀሐይን መውጣትና መግባት ተከትሎ የራሱ የእንቅልፍ ሰዓት አቆጣጠር አለው። ለዚህም ነው ሲመሽ እየተኛን፤ ሲነጋ የምንነቃው። ይሁን እንጂ ይህ ለሁሉም ሰው ላይሰራ ይችላል፤ ምክንያቱም የአንዳንድ ሰዎች ሰዓት ከሌሎቹ ዘግይቶ ይዘውራልና።

ስለዚህ በትክክል ሰውነትዎ ለእንቅልፍ ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው።

ሰውነታችን በአካላዊ እንቅስቃሴዎች ሲደክምም እንቅልፍ ቀላል ይሆናል፤ ነገር ግን ከእንቅልፍ አራት ሰአት በፊት ምንም አይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግም ጠቃሚ ነው።

2. የሚበሉትና የሚጠጡትን ነገር ይከታተሉ

ወደ አልጋ ከመሄድ በፊት አልኮል አንድ ሁለት ማለት ጥሩ እንቅልፍ ያስተኛል የሚባል አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ ቢኖርም ይህ ፍፁም ትክክል አይደለም ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

በተለይም ለትምህርትና ትውስታ የሚጠቅመውን የእንቅልፍ ሂደት REM (rapid eye movement) ያውካል አልኮል። አልኮል የሚፈጥረው የፊኛ መወጠርም ሌላ ለእንቅልፍ መረበሽ ምክንያት ነው። በጥቅሉ ከእንቅልፍ ጋር በተያያዘ አልኮል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።

• እንቅልፍ እንዲህ ጠቃሚ ነገር ኖሯል?

ቡና ወይም ሻይም ቢሆን ከእንቅልፍ ስድስት ሰአት በፊት መጠጣት አይመከርም።

ለአንዳንዶች ደግሞ በባዶ ሆድ ወደ አልጋ መሄድ የማይታሰብ ነገር ቢሆንም ጠግቦ እንደ መተኛት ግን የእንቅልፍ ጠላት የለም። ቢቻል ቀለል ያሉ ምግቦችን ከእንቅልፍ አራት ሰአት በፊት መመገብ እንቅልፍን ጥሩ ያደርገዋል።

3. ከእንቅልፍ በፊት የሚወዱትን ነገር ያድርጉ

በጣም የሚያስደስትዎትን ነገር ከእንቅልፍ በፊት ሁሌም ማድረግ አካላዊና ስነልቦናዊ እረፍትን ይሰጣል። ሁሌም ከሚደረጉ ነገሮች መካከል ሞቅ ባለ ውሃ ገላን መታጠብ፣ መፃህፍት ማንበብ፣ ሙዚቃ መስማትና በተመስጦ ማሰላሰል ይጠቀሳሉ።

ነገር ግን እነዚህ የዕለት ተዕለት ተግባራት ተመሳሳይ ናቸው ማለት አይደለም፤ ለእናንተ የሚስማሟችሁና ለእንቅልፍ የሚረዱ ሌሎች ነገሮች ካሉ እነሱን ሁሌም ቢሆን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።

4. ንጹህ የእንቅልፍ ቦታ ያዘጋጁ

ይሄ ማለት ከእንቅልፍ በፊት ገላን መታጠብና ጥርስን መቦረሽ አይደለም። ነገር ግን እነሱም ጥሩ ልማዶች ናቸው።

ንጹህ የእንቅልፍ ቦታ ማለት ምቹ የሆነ አካባቢን ማዘጋጀት ነው። የመኝታ ክፍሎቻችን ዋነኛ አገልግሎታቸው እንቅልፍና ከእንቅልፍ ጋር ለተያያዙ ነገሮች ብቻ መሆን አለበት።

ምናልባት ለአንዳንድ ሰዎች ባይሰራ እንጂ የመኝታ ክፍል ጨለማ ሲሆንና ቀዝቀዝ ያለ የአየር ጸባይ ሲኖረው ብዙ ሰዎች ቶሎ እንደሚተኙና ጥሩ እንቅልፍ እንደሚወስዳቸው ይናገራሉ።

ከእንቅልፍ በፊት በተለይ ደግሞ አልጋ ውስጥ ሆኖ ሞባይልና ላፕቶፕ መጠቀምም ቢሆን ለእንቅልፍ ጠቃሚ አይደሉም። ረዘም ያለ ሰአት በስክሪን ላይ አፍጥጠን የምንቆይ ከሆነ የምንተኛው እንቅልፍ ጥራት የጎደለው ይሆናል።

5. ለእንቅልፍዎ ቅድሚያ ይስጡ

ምናልባት በርካታ የዓለማችን ስኬታማ ሰዎችና መሪዎች በቀን ለአራት ሰአት ብቻ እንደሚተኙ በኩራት ሲናገሩ ሰምተን ይሆናል፤ ነገር ግን እውነታው ሁሉም ሊያደርገው አይችልም ነው። ለጤናችንም ብዙ እክሎችን ያስከትላል።

የእንቅልፍ ሰአትዎን በአንድ ሰአት ቢቀንሱ ወዲያውኑ ለውጡን ሊያስተውሉት አይችሉ ይሆናል፤ ነገር ግን ቀስ በቀስ ሰውነትዎ እየተዳከመ ይመጣል። በተጨማሪም ትንሽ የእንቅልፍ ጊዜ ለተለያዩ የልብ በሽታዎች፣ ስትሮክ እና ካንሰር ያጋልጣል።

ስለዚህ ሁሌም ቢሆን ለእንቅልፍ ቅድሚያ መስጠትና ቢያንስ ለሰባት ወይም ስምንት ሰአት መተኛት ያስፈልጋል። በጠዋት መነሳትም ተገቢ ነው።

ምንጭ:- ቢቢሲ አማርኛ

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top