ኢትዮጵያ ህዋውን ትጠቀም ዘንድ እንደ አባቶቻችን አልቀው ያሰቡ ጀግኖችን እናመስግን፤ ከእነዚህ አንዱ ተፈራ ዋልዋ ናቸው፡፡
ሼህ አላሙዲና ዶክተር ለገሠ ወትሮ ታሪክ ቅን ፈራጅና ውለታ መላሽ ነው። ታሪክ ይከፍላችኋል።
****
ከሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ
ደጋግሜ ስለ ህዋ ሲያወሩ ሰምቼ ነበር፤ አእምሯቸውን ታመው መስለኝ፡፡ ውሎ አድሮ ግን አእምሮዬ እንዲህ ያሰበው በጤናው አለመሆኑ ገባኝ፡፡ ምንም በሌለበት የምድሩን ሽኩቻ ለቀው ወደ ሰማዩ ቀና ያሉት፤ በህዋ ሀገራቸው የሚኖራትን የሀብት ድርሻ ማሰብ የጀመሩት ሰው ሩቅ አሳቢ ጤነኛ ነበሩ፡፡
አባቶቻችን በህዋው ላይ ስለመጠቀም ብዙ ጽፈው አልፈዋል፡፡ የሰማያትን ምስጢር መርምረዋል፡፡ ግን እድለኛ አልነበሩም፤ የተኩት ትውልድ ዓለም ስለ ህዋ ሲያወራ በጅረት የሚፋጅ ተራ ሆነ፡፡
በዚህ ጨለማ ትውልድ መካከል ብርሃን የሆኑ ከዋክብት እንደ አባቶቻቸው አስበዋል፡፡ ሼህ መሐመድ አላሙዲ ጥሪትዎን ሳይሰስቱ ሀገርን ከሌላው ሀገር እኩል አድርገዋልና ታሪክ ቅን ፈራጅ ውለታ መላሽ ነው።
ሳይንቲስቱ ለገሰ ወትሮ በኢትዮጵያውያን ቀጣይ ትውልድ ግዙፍ ቦታ የሚኖረው ሰው ነው፡፡ በእርዳታ እህል ጉርሷን በምትሸፍን ሀገር ስንፍና ሳይገድበው ሰማያት ስለመድረስ፣ ህዋውን ስለ መዳሰስ ሲያስብ እና ሲቀሰቅስ ኖሯል፡፡ እንዲህ ያሉ ሳይንቲስቶቻችን ብዙ ናቸው፡፡ የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም ስንፍና ሳይመልሳቸው የወሰኑትና ያስቀጠሉት ፕሮጀክት ዛሬ እንደመሪ መልሰው ኮርተውበታልና ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ሁሉም የሀገሬ ጀግኖች እንዲህ ላለው ውጤት ኢትዮጵያን ያበቁ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ከእነኚህ አንዱ የኢትዮጵያ የህዋ ጉዳይ አባት አቶ ተፈራ ዋልዋ ናቸው፡፡
አቶ ተፈራ የህዋ ሳይንስ ልባቸውን የወሰደባቸው ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ መተካካት ብለው ከፖለቲካው በማምለጥ ነፍሳቸው እጅ ወደሰጠችበት የህዋ ሳይንስ ጉዳይ በመግባት ታሪክ የማይረሳው ስራ ሰርተዋል፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ሊቃውንት የማትረሱት ባለውለታ ቢባሉ አስቀድመው የሚጠሩት ስም ተፈራ ዋልዋ ነው፡፡ እኒህ ሰው ቀላል ሰው አይደሉም፡፡ በበሬ በምታርስ ሀገር ህዋን ስለመጠቀም አስበው ሌት ተቀን ደክመዋል፡፡ የሳቀው ፖለቲከኛ ቤት ይቁጠረው፤ ዛሬ ግን በደስታ ሊያስቁን ነው፡፡
ብዙ ተማሪዎች ያኔ የመጀመሪያ ዲግሪ እንኳን አልጨረሱም፡፡ ሳይንሱ ለኢትዮጵያ ባዕድ ነበር፡፡ ባለቤት ነኝ ብለው ባለቤት አጥቶ በኖረው ዘርፍ ገቡበት፡፡ የትግል ጓዶቻቸው በበርሃ ሳሉም ጭምር አይናቸው ሰማይ ተተክሎ ከከዋክብት ይነጋገራል የሚሉላቸው ተፈራ ዋልዋ ብዙ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ እንዲያገኙ አድርገው ኢትዮጵያ እንዲህ ባለው የህዋ ሳይንስ ጥበብ ጥቂትም ቢሆን ለዶክትሬት የበቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ቻለች፡፡ የማህበሩ አባላትም በረከቱ፡፡ መንግስትም ወደ ህዋ ሳተላይት የማምጠቅ ፍላጎቱ ጨመረ፡፡
ኢትዮጵያ በሕዋ ሳይንስ ዘርፍ በር ከፋች የሆነች የመሬት ምልከታ ሳተላይት ወደ ሕዋ ዛሬ ታኅሳስ 10 ቀን 2012ዓ.ም ከቻይና የሳተላይት ማምጠቂያ ጣብያ አስወንጭፋለች፡፡
ዛሬ በሀገረ ቻይና አንድ የኢትዮጵያ ሳተላይት ወደ ህዋው ትመጥቃለች፡፡ እንዲህ ላለ ፍሬ ካበቁን ሰዎች መካከል ተፈራ ዋልዋ አንዱ ናቸውና ምስጋናችን ይድረሳቸው፡፡ ደስታቸውን እንደ መጠቀችው ሳተላይት ሩቅ ድረስ ያድርግላቸው፤ እድሜ ይስጥልን፤