Connect with us

የጠ/ሚ ዐብይ መልዕክት

የጠ/ሚ ዐብይ መልዕክት
Photo: Aron Simeneh

ዜና

የጠ/ሚ ዐብይ መልዕክት

ኦስሎ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እስክትመስል ድረስ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና በኢትዮጵያ ባነሮች ተውባ ሰነበተች፡፡ ሚዲያዎች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ በኩራት መሰከሩ፡፡ ኢትዮጵያን በድህነትና በጦርነት፣ በረሐብና በእልቂት የሚያውቋት ሁሉ አዲስ ታሪክ ሆነባቸው፡፡ በሩጫ ስናሸንፍ ነበር የሚያውቁን፤ ዛሬ ደግሞ በሰላም ሥራችን በዓለም አቀፍ መድረክ ስናሸንፍ አዩን፡፡ ከግሪን ላንድ እስከ ኒውዚላንድ፣ ከቺሊ እስከ ጃፓን ዓይኖች ሁሉ ወደ ኦስሎ ተተክለው ስለ ኢትዮጵያ ተመለከቱ፡፡

በመላው ዓለም ተበትነው የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን የዜግነት ክብራቸውን ከፍ የሚያደርግ ሥራ በታሪክ ውስጥ ሲመዘገብ አዩ፡፡ ልጆቻቸው በባዕድ ሀገር በታሪካቸው ኮሩ፡፡ ሀገራቸው በምሳሌነትና በአርአያነት ስትነሣ በዓይናቸው ብሌን ተመለከቱ፤ ሰሙ፡፡ በዓረብ ሀገር የሚኖሩ ዜጎቻችን አሠሪዎቻቸው ወደታች ሳይሆን ወደላይ እንዲዩዋቸው የሚያደርግ ታሪክ በዓለም አደባባይ ሲከወን ዕንባ በተሞሉ ዓይኖቻቸው አደነቁ፡፡

ሁለት ዓይነት ታሪክ ሲሠራ የዓለም ዓይኖች ታዘቡ፡፡ በጦርነት የምትታወቅ ሀገር የሰላም ሽልማት ተሸለመች፡፡ የሰላምን ዋጋ የሚያውቀው ዓለም፤ የሰላም ሽልማት በቀላሉ እንደማይገኝ የሚያውቁ የዓለም ዜጎች በደስታና በክብር አብረውን ከረሙ፡፡ ለሕዝቦች መቀራረብ፣ ለሕዝቦች መገናኘት፣ ለሕዝቦች ዕርቅና ሰላም መሥራት የሚያሸልም ተግባር መሆኑን የሚያውቁ ሁሉ፤ የቻሉ በኦስሎ ጎዳናዎች ተገኝተው፤ ያልቻሉ በየቴሌቭዥን መስኮቶች አፍጥጠው ክብር ሰጡን፡፡

በኦስሎ ያገኘነው ክብር የሀገራችን ጉዞ ከትናንት የዛሬው፣ ከዛሬውም የነገው እጅግ የተሻለ መሆኑን አመላክቶናል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይሆንም፡፡ በሰላም፣ በሳይንስ፣ በሥነ ጽሑፍ ገና ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ኖቤል ሀገር ወደ ኖርዌይ ይመጣሉ፡፡

ዛሬ ያገኘነውን አክብረን አያሌ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ሀገራቸውን እንዲያስጠሩ እንሠራለን። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ሀገር የሚያስጠራ ጥረት እንድናደርግ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top