መንገድ በማቋረጥ ላይ እንዳለች በተሽከርካሪ የተገጨችው ነብር በግሉኮስ ድጋፍ ሪፈር ተብላ ለተጨማሪ ህክምና ከአድዋ በተሽከርካሪ መቀሌ መግባቷን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ ።
ነብሯ ህዳር 9 ቀን 2012 ዓ.ም መንገድ አቋርጣ በማለፍ ላይ እንዳለች በተሽከርካሪ የተገጨችው በትግራይ ክልል ማእከላዊ ዞን ታህታይ ማይጨው ወረዳ “ማይበራዝየ“ በተባለ አካባቢ ነበር ።
የነብሯን ህይወት ለማትረፍ አድዋ በሚገኘው የእንስሳት ህክምና መለስተኛ እንክብካቤ ሲደረግላት ቢቆይም የተሟላ የህክምና መሳሪያና መድሃኒት እንደ ልብ ማግኘት ባለመቻሉ ወደ መቀሌ ሪፈር መባሏን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።
የነብሯን ቀጣይ ህክምና የተመለከተ ሙሉ ኃላፊነት የወሰደው ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ ስር የሚገኘው ሆስፒታል ነው ።
በኮሌጁ የእንስሳት ህክምና ባለሞያ ዶክተር ተወልደ ፅጋብ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በራሱ ሀኪሞች ነብሯ ከአድዋ ወደ መቀሌ እንድትመጣ ያደረገው ህዳር 12 ቀን 2012 ዓም ነው ።
ነብሯ ወደ መቀሌ ከመጣች በኋላ በኤክስሬይ የታየች ሲሆን አንገቷ አካባቢና ግራ እግሯ ላይ ጉዳት እንደደረሰባት ተረጋግጧል ።
በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ምግብ መውሰድ ባለመቻሏ በግሉኮስ ድጋፍ ሌሎች መድሀኒቶች እንድትወስድ እየተደረገ መሆኑን ሀኪሙ ይናገራሉ ።
ነብሯ አንገቷ አካባቢና ግራ እግሯ ላይ በደረሰባት ጉዳት በቅርቡ የቀዶ ጥገና ህክምና ይደረግላታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሀኪሙ ተናግረዋል።
ዶክተር ተወልደ ፅጋብን ጨምሮ በኮሌጁ የሚገኙ የእንስሳት ሀኪሞች በህይወት ዘመናቸውና በስራ ልምዳቸው ነብርን በአካል አይተው እንደማያውቁ ይናገራሉ ። ነብሯ ከጉዳቷ ጋር በተያያዘ በተንፈራገጠች ቁጥር የመደንገጥ አጋጣሚዎች እየተከሰቱ መሆኑንም ከዶክተር ተወልደ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።
ነብርን ማከም ስጋት የሚኖረውን ያክል መልካም አጋጣሚም እንዳለው የገለፁት ዶክተር ተወልደ የነብሯን ህይወት ለማዳን የሚደረገው የህክምና ርብርብ ለሀኪሞችም ሆነ ለኮሌጁ ተማሪዎች የተግባር መማሪያ ሆኖ የሚያገለግል ክስተት መሆኑን አስረድተዋል ።
በአካባቢው የእንስሳት ማቆያ/ዙ/አለመኖሩን የተናገሩት የህክምና ባለሙያው ነብሯ ህክምናዋን ከጨረሰች በኋላ የደመቀ የሽኝት ፕሮግራም በማዘጋጀት ወደ ነበረችበት አካባቢ እንድትመለስ ይደረጋል ።
በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የዱር እንስሳት ባለሙያ አቶ ብርሃነ መረሳ በበኩላቸው በክልሉ እየጨመረ ከመጣው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ጋር በተያያዘ የዱር እንስሳት አይነትና ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ።
ጉዳት የደረሰባት እንስሳ ሳይንሳዊ መጠሪያዋ ሊዮፓርድ ወይም የአፍሪካ ነብር መሆኑን የገለጹት ባለሙያው በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ከሚገኙ ሶስት የነብር ዝሪያዎች አንዷ መሆንዋ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ በዱር እንስሳት ያለውን ግንዛቤ እየተሻሻለ በመምጣቱ የነብሯን ህይወትም የአካባቢው ሰዎች በሰጡት ጥቆማ መሰረት ህክምና የምታገኝበት እድል መፈጠሩን ነው ያስረዱት ።
እንደኢዜአ ዘገባ በክልሉ ባለው የደን ሃብት ለዱር እንስሳት ማቆያ የተከለለ ቦታ ባለመኖሩ አሽከርካሪዎች በዱር እንስሳት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እየጨመረ በመሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ባለሙያዎቹ ጥሪ አቅርበዋል ።