የኢትዮጵያን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በመምራት ዩጋንዳ ካምፓላ የሚገኙት የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2012 ዓም ከዩጋንዳ ሪፐብሊክ ፓርላማ አፈ ጉበኤ ርብቃ ካዳጋ ጋር ተወያይተዋል።ሁለቱ አፈ ጉባኤዎች የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኘነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
የዩጋንዳ ሪፐብሊክ ፓርላማ አፈ ጉባኤ የተከበሩ ርብቃ ካዳጋ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የኢትዮጵያ እና የዩጋንዳ ግንኘነት ታሪካዊ እና ረጅም ዘመናትን ያሰቆጠረ መሆኑን አንስተዋል። የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በኢኮኖሚ በማስተሳሰር የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ጥቅም ማሳዳግ እንደሚገባም ክብርት ካዳጋ ገልጸዋል።
ሁለቱ አገሮች በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን ያስታወሱት አፈ ጉበኤ ካዳጋ፤ ስምምነቶችን ወደ ተግባር በመለወጥ በኩል ያሉ ውስንነቶች በመቅረፍ ለተግበራዊነቱ መንቅሳቀስ እንደሚገባም አስታውሰዋል። በተለይም በንግድ፣ በኢንዱስትሪ እና በግብርናው ዘርፍ ግንኙነቱን ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚቻል እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የትራንስፖርት፣ የትምህርት፣ የባህል እና ቱሪዝም ዘርፉን በማሻሻል የሁለቱ አገር ህዝቦች በቀላሉ ማስተዋወቅ እና በትብብር እንዲሰሩ ሁኔታዎችን መማቻቸት እንደሚገባ አፈ ጉባኤ ርብቃ ካዳጋ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ አየር መንግድ በሳምንት አምስት ጊዜ ወደ ዩጋንዳ በረራ እንደሚያደርግ እና ይህም ቀጣይነት ያለውን የህዝቦች ትስስር ለማጠናከር የራሱን ከፍተኛ ሚና እየተጫወት መሆኑን አፈ ጉባአ ርብቃ በንግግራቸው አንስተዋል።
ዩጋንዳ እና ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ በትብብር በመስራት አሁን የሚታዩ የአትሌቲክስ ውጤቶችን ማሻሻል አንደሚቻልም ክብርት ካዳጋ ገልጸዋል። በቀጣይም ከካምፓላ አዲስ አበባ ቀጥታ የመንግድ ትራንስፖርት መዘርጋት የሚቻለበትን ሁኔታ አልሞ መስራት እንደሚገባም አፈ ጉባኤ ካዳጋ አንሰተዋል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች አባቶቻችንን ህልም እውን ለማድረግ በዚህ ዘመን የሚገኘው ትውልድ የራሱን ሚና መወጣት እንደሚኖርበት ነው አፈ ጉባኤ ርብቃ ካዳጋ የገለጹት።
የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ዩጋንዳ ኢንቴቤ ከደረሱ ጊዜ ጀምሮ ለራሳቸው እና ለልኡካን በድኑ ስለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል። የዩጋንዳ ህዝብ እና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ስላለው ቁርጠኝነትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ሁለቱ አገሮች የፓርላማ ጉድኝትን ጨምሮ በርካታ የሁለትዮሸ ስምምነቶች ያላቸው መሆኑን በማሰታውስ ይህንን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገበም አቶ ታገሰ ገልጸዋል።
ዩጋንዳ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍን በማጽደቅ ወንዙን በፍትሃዊነት ለመጠቀም እንዲቻል እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴም አድንቀዋል። ሁለቱ አገሮች የናይል ወንዝን ከመጋራት ጀምሮ በህዝብ ለህዝብ እና በበርካታ ጉዳዮች በትብብር የሚሰሩባቸውና ተግባር ላይ ያልዋሉ በርካታ እድሎች መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ ታገሰ በቀጣይ የሁለቱን አገሮች የሚጠቅሙ የጋራ ጉዳዮችን ይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል። የሁለቱ አገሮች ጠንካራ የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም መጠናከር እንደሚኖርበት አቶ ታገሰ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በመግለጽ፤ ዩጋንዳም ተመሳሳይ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመላከ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ሲጠናክር የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍተሄ ሃሳቦችን ለማፈለቅ እንደሚቻልም እምነታቸው መሆኑን የተከበሩ አቶ ታገሰ ገልጸዋል። በመጨረሻም የዩጋንዳ ፓርለማ አፈ ጉባኤ የተከበሩ ርብቃ ካዳጋ ኢትዮጵያን አንዲጎበኙ ጋብዘዋል። ክብርት ካዳጋም ስለተደረገለቸው ግብዣ አመስግነው ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ቃል ገብተዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ቃል አቀባይ ጽ/ቤት
ህዳር 17 ቀን 2012 ዓ.ም