– በቂሊንጦ የንጽህና መስጫ ህንጻ ሲያስገነባ፤ በአርሲ ደግሞ የገብስ አምራች ገበሬዎችን ጎበኘ
ቂሊንጦ አካባቢ ወረዳ 9 ቀርሳ ቀጠና የተገኘኹት በሀይኒከን ኢትዮጵያ የተሰራ የህዝብ የንጽህና መስጫ ህንጻ ለማየት ነበር፡፡ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ ህንጻ ለአካባቢው ማህበረሰብ የመጸዳጃ ቤት፣ የገላ መታጠቢያ (ሻወር) ቤቶች እና የእጅ ንጽህና ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡ ተዘዋውሬ እንደተመለከትኩት በሀይኒከን ተገንብቶ ባለፈው ሐሙስ ዕለት ለነዋሪዎች በስጦታ የተላለፈው ህንጻ በውስጡ ለወንዶች እና ለሴቶች ለየብቻ አገልግሎት የሚሰጡ በድምሩ 13 መጸዳጃ ቤቶች (የቁምና የመቀመጫ)፣ 6 ሻወር ቤቶችን እና የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ቤቶችን ያካተተ ነው፡፡
አቶ ፍቃዱ በሻህ የሀይኒከን ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ሰስተነብሊቲ ሥራ አስኪያጅ ለድሬቲዩብ እንደተናገሩት በአካባቢው የመጸዳጃ ቤት እና የሻወር አገልግሎት እንዳልነበር ጠቅሰው ይህን የህብረተሰቡን ችግር ለማቃለል ሀይኒከን ኢትዮጵያ ህንጻውን ለመገንባት መነሳቱን አስታውሰዋል፡፡ ህንጻው ደረጃውን በጠበቀ መልክ መገንባቱን፣ በቀጣይ በንጽህና አገልግሎት እንዲሰጥ በወረዳው የተመለመሉ 11 ሴቶች ተደራጅተው ህንጻውን እንዲረከቡ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ለሴቶቹም ስለንጽህና አጠባበቅ ተገቢውን ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉንና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ተገዝተው እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሴቶች በአነስተኛ ክፍያ ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት የግል ኑሮአቸውን ለማሻሻል እንደሚያስችላቸውና ከህንጻው ጋር ተያይዞ የሻይ፣ የቡና የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያስችል ቦታም መኖሩ ተጨማሪ ዕድል መሆኑን አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡
በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት የሀይኒከን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢዩግን ኡባልጆሮ “ከምንም በላይ ያስደሰተኝ ህንጻው መገንባቱ ብቻ ሳይሆን ለ11 ሴቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ነው” ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለቂሊንጦ አካባቢ ማህበረሰብ በተመሳሳይ ሁኔታ ለእናቶች የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የሚውል የአምቡላንስ እና የልዩ ልዩ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡
የሥራ ዕድሉ የተፈጠረላቸው እናቶች ሀይኒከን ኢትዮጵያ ላደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የሀይኒከን ኢትዮጵያ ማኒጂንግ ዳይሬክተር ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ አመራር አባላት ያቀፈ ቡድን ሰሞኑን በአርሲ ዲገሉ በሚባል ቦታ የገብስ አምራች ገበሬዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ መጎብኘቱን አቶ ፍቃዱ በሻህ ለድሬቲዩብ ገልጸዋል፡፡
ሀይኒከን ኢትዮጵያ የገብስ አምራች ገበሬዎችን ለመደገፍ በማሰብ ለቢራ ጠመቃ የሚውል የገብስ ምርት ከባሌ እና አርሲ ገበሬዎች የሚገዛ ሲሆን ገበሬዎችን ለማበረታት የምርት ዘር አቅርቦት እና የፋይናንስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አቶ ፍቃዱ ጠቁመዋል፡፡ ይህ የሀይኒከን ፕሮጀክት ሲጀምር 1 ሺ 300 ገበሬዎች በማቀፍ ሲሆን በአሁን ሰዓት የገበሬዎቹ ቁጥር 40 ሺ መድረሱን፣ የምርት መጠኑም በሄክታር 2 ነጥብ 7 ገደማ የነበረው በአሁን ሰዓት በእጥፍ ከ 6 አስከ 8 ቶን በሄክታር ማደጉን አቶ ፍቃዱ ጠቅሰዋል፡፡
የገበሬዎቹ ገቢ ማደጉ በቤተሰባቸውና በኑሮአቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዲያገኙ እየረዳ ስለመሆኑም ከአቶ ፍቃዱ ገለጻ ለመረዳት ችለናል፡፡
የሀይኒከን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እንዳሉት ድርጅታቸው ከሀገር ውስጥ የሚጠቀመው የገብስ ምርት በአጭር ጊዜ ከ10 ወደ 16 በመቶ ማደጉንና ይህም ወደፊትም እያደገ እንዲሄድ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡
ሀይኒከን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ ከ21 ቢሊየን ብር በላይ መዋእለ ንዋይ በኢትዮጽያ ማፍሰሱን ከ1 ሺ በላይ ሰዎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል እንዲሁም 50 ሺ ለሆኑት ደግሞ ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡