በ2012 በጀት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ አምስት ድርጅቶች ከታክስ በፊት 174 ሚሊዮን ብር ማትረፋቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ ፡፡
በኤጀንሲው ሥር ያሉና በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ አምስት የልማት ድርጅቶች በተጠናቀቀው የ2012 በጀት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከታክስ በፊት ብር 233 ነጥብ 9 ሚሊዮን ለማትረፍ አቅደው በጊዚያዊ የሂሳብ መረጃ መሠረት ብር 174 ሚሊዮን ማትረፋቸውን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ተናግረዋል፡፡
ይህ ትርፍ የዕቅዳቸው 74 ነጥብ 4 በመቶ ሲሆን ድርጅቶቹ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አክሲዮን ማኅበር እና ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ናቸው ተብሏል፡፡
ድርጅቶቹ የተጠቀሰውን ትርፍ ያስመዘገቡት በሩብ ዓመቱ የተለያዩ የፋብሪካ ምርቶቻቸውን ለገበያ በማቅረብ በድምሩ 3 ነጥብ 01 ቢሊዮን ብር የሽያጭ ገቢ ለማግኘት አቅደው ብር 2 ነጥብ 27 ቢሊዮን ወይም የዕቅዳቸውን 75 ነጥብ 5 በመቶ በማግኘታቸው ነው፡፡
ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የአልኮል መጠጥ ለውጭ ገበያ ጭምር በማቅረብ 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የሽያጭ ገቢ ለማግኘት አቅዶ 23 ሺ 100 የአሜሪካን ዶላር ወይም የዕቅዱን 23 በመቶ ማግኘት ችሏል፡፡
ከአጠቃላዩ የብር 174 ነጥብ 07 ሚሊዮን ትርፍ ብር 83 ነጥብ 09 ሚሊዮን ወይም 30 ነጥብ 30 ድርሻ በመያዝ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን በብር 41.76 ሚሊዮን ትርፍ ወይም ከአጠቃላዩ 23 ነጥብ 99 ድርሻ በመያዝ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሁለተኛው ደረጃ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
ይህ ኮርፖሬሽን በባለፈው ተመሳሳይ ወቅት የብር 607.78 ሚሊዮን ኪሳራ ደርሶበት የነበረ ሲሆን፣ በዚህ የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከኪሳራ መውጣት መቻሉ አበረታች መሆኑ በግምገማው ወቅት ተገልዷል፡፡
ሶስተኛውን ደረጃ በብር 34 ነጥብ 9 ሚሊዮን ወይም በ20 በመቶ ትርፍ ድርሻ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የያዘ ሲሆን ፤የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር የልማት ድርጅቶቹ የኦፕሬሽን አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲታይ ኪሳራ ውስጥ የነበሩ ከኪሳራ መውጣትና የኪሳራ መጠንን በእጅጉ የመቀነስ፣ አትራፊ የነበሩ ደግሞ የትርፍ መጠናቸውን የማሳደግ ሁኔታ ያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው በዚህ የዕቅድ ዝግጅት ምዕራፍ ያስመዘገቡትን ውጤት አጠናክረው በቀጣይ የትግበራ ምዕራፎች አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበው የዘርፉ ግምገማ ተጠናቋል፡፡